የብሪስቶሉ ጆርጅ ሙለር
የቤተ ክርስቲያን ሕይወትና እድገት

ምዕራፍ 23 · 18 ደቂቃ ንባብ · 24 ደቂቃ ማዳመጥ

የቤተ ክርስቲያን ሕይወትና እድገት

በአቶ ሙለር የዕለት ማስታወሻ ሁሉ ውስጥ ስለ ክርስቲያናዊ ትምህርትና አኗኗር እውነተኛ መረዳት፣ ስለ ክርስቲያናዊ አገልግሎት ባሕርይና ተግባር፣ በቤተ ክርስቲያን አመራር ሊሠሩ ስለሚገባቸው መርሆች፣ ስለ አማኞች እርስ በርስ ግንኙነት፣ እንዲሁም መንፈስ ከክርስቶስ አካል፣ ከንጹሕ አምልኮ፣ ከአገልግሎትና ከምስክርነት ጋር ስላለው ግንኙነት የተበታተኑና ቍርጥራጭ ፍንጮች እናገኛለን። እነዚህ ፍንጮች እርስ በርሳቸው ያላቸው ትስስር እንዲታይ በአንድነት ቢጠቃለሉ የበለጠ ጥቅም ይኖራቸዋል።

የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶቹ መሥራች የሕዝብ አገልግሎቱን የጀመረውም የፈጸመውም በሰባኪነት ነው፤ ከስድሳ ዓመታት በላይም ከአንድ የአማኞች ማኅበር ጋር እጅግ የተቈራኘ ስለ ነበረ፣ በብሪስቶል ስለምትገኘው፣ እርሱ ከመጀመሪያዎቹ መሪዎቿ አንዱ ስለ ነበረባትና ካገለገሏት ሁሉ ረጅሙን ዘመን ስላገለገላት ቤተ ክርስቲያን በሰፊው ሳይጠቀስ የሕይወቱ ምንም ዓይነት ግምገማ ሙሉ ሊሆን አይችልም።

በብሪስቶል የቤተ ክርስቲያን ሥራው የጀመረው ወደዚያች ከተማ በመጣ ጊዜ ሲሆን የተፈጸመውም ከእርሷ ተለይቶ ወደምትኖረው ከተማና ወደ አብ ቤት በሄደ ጊዜ ብቻ ነው። እርሱና አቶ ሄንሪ ክሬክ በጋራ ያገለገሉበት አገልግሎት በየጊዜው በተከናወነው ሥርዓት መሠረት አስቀድሞ ተተርኳል፤ ነገር ግን በዚህ ሐዋርያዊ አገልግሎት ሥር የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እንዴት እንዳደገ የሚያሳየው ታሪክ ሙሉ ትምህርቱን የሚሰጠው አንድነት፣ ቀጣይነትና ሙሉነት ያለው ስሜት እንዲፈጥር ተሰብስቦ በአንድነት ሲደራጅ ብቻ ነው።

አቶ ሙለርና አቶ ክሬክ በብሪስቶል የጋራ ሥራቸውን በጀመሩ ጊዜ መሠረቱ እንደ ገና መጣል ያስፈልገው ነበር። ያገኙት የቤተ ክርስቲያን ሕይወት በበቂ ሁኔታ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ አልነበረም፤ እነርሱም ከቃሉና ከፈቃዱ ጋር ይበልጥ ሙሉ በሙሉ ለማስማማት ጥበብን እየለመኑ እግዚአብሔርን ጠበቁ። ይህ ጊዜ የሚጠይቅ ሥራ ነበር፤ ምክንያቱም አብረዋቸው ያሉት አማኞች መጽሐፍ ቅዱሳዊና መንፈሳዊ ትምህርትን ተገንዝበው ለመተባበር ይዘጋጁ ዘንድ መማር ነበረባቸው፤ ደግሞም መንጋው የእረኛውን ድምፅ እንዲሰማና እንዲታዘዝ፣ እውነተኛውንም የእረኝነት አመራር እንዲከተል የሚያዘነብለው የመተሳሰብ ማሰሪያ መፈጠር ነበረበት። እነዚህ ወንድሞች አገልግሎታቸውን ሲጀምሩ አገልግሎታቸው የሚመሠረትባቸውን አንዳንድ መርሆች በጥንቃቄ አስቀመጡ። በሜይ 23 ቀን 1832 ቤተ ክርስቲያኒቱን ሊረከቡ የሚችሉባቸውን ብቸኛ ቅድመ ሁኔታዎች በጌዴዎን ቤተ ጸሎት በግልጽ ተናገሩ፤ እነርሱም፦ የእግዚአብሔር ፈቃድ እስከ ሆነ ድረስና እርሱ በሚወደው መንገድ በመካከላቸው የሚደክሙ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ብቻ ሆነው እንዲቈጠሩ እንጂ በማንኛውም የተወሰነ ደንብ እንዳይታሰሩ፤ የመቀመጫ ኪራይ ቀርቶ በምትኩ በፈቃድ የሚሰጥ መባ እንዲሆን መፈለጋቸው፣ ወዘተ. ነበሩ።

ይሁን እንጂ ያለው የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ሙሉ በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ አብነት እንዲቀረጽ ከተፈለገ በአንዳንድ ረገድ አዲስ ጅምር የግድ አስፈላጊ መሆኑ አስቀድሞም በጽኑ ታምኖበት ነበር። እነዚህ ወንድሞች እንደሚከተሉት ያሉ አንዳንድ አስፈላጊ መለያዎችን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ለማተም ቈረጡ፦ ሐዋርያዊ ቀላልነት ያለው አምልኮ፣ ወንጌላዊ ትምህርት፣ የወንጌል ስርጭት ሥራ፣ ከዓለም መለየት፣ ሥርዓት ያለው መስጠትና በጸሎት መደገፍ። ለቃሉ ቀላል ምስክርነት ታላቅ ስፍራ ለመስጠት፣ እያንዳንዱን የሥራ ክፍል በፈቃድ በሚሰጥ መባ ለመደገፍ፣ መንፈስ ቅዱስን በቤተ ክርስቲያን ጉባኤዎች ሁሉ ላይ የሚሰለጥንና የሚያስተዳድር ብቸኛ ኃይል አድርገው ለመቀበል፣ እንዲሁም ያ መንፈስ ለአገልግሎት ለክርስቶስ አካል ብልቶች ሁሉ ባካፈላቸው መንፈሳዊ ስጦታዎች አማኞች ሁሉ በነጻነት እንዲያገለግሉ ለማድረግ ፈለጉ። በእያንዳንዱ የጌታ ቀን እንጀራ መቍረስና በመጥለቅ ማጥመቅ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንደ ሆነ ያምኑ ነበር፤ ምንም እንኳ ይህ የኋለኛው ለብዙ ዓመታት ለማዕድ ኅብረት ወይም ለአባልነት ቅድመ ሁኔታ ባይሆንም፣ ይህ የደቀ መዛሙርት ሁሉ ግዴታ መሆኑን አማኞች ሁልጊዜ በጥንቃቄ ተምረዋል።

በኦገስት 1832 እነዚህን ሁለት እረኞች ጨምሮ በአጠቃላይ ሰባት ሰዎች ለእግዚአብሔር ቃልና መንፈስ ከመታመን በቀር ምንም ዓይነት መደበኛ መሠረት ወይም ማሰሪያ ሳይኖራቸው በኅብረት ለመተባበር በቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎት እንደ ተሰበሰቡ አስቀድሞ ታይቷል። ይህ እርምጃ የተወሰደው፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አይደሉም ተብለው የታመነባቸው፣ ነገር ግን ያለ አለመግባባት ለማስቀረት አስቸጋሪ የሆኑ ቀድሞ የነበሩ ልማዶች ሳያደናቅፉ እንደ ገና ለመጀመር ነው፤ ከዚያ ቀን ጀምሮም የቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎት የአዲስ ኪዳንን የቤተ ክርስቲያን ሕይወት መሠረት አጥብቀው ለመያዝ በጽናት የፈለጉ የአማኞች ጉባኤ መኖሪያ ሆኗል።

እንዲህ ያሉት የተባረኩ ውጤቶች በአብዛኛው የተገኙት ምስክርነታቸውን ፈጽሞ ባልከለከሉት፣ ይልቁንም ከቃሉ ጋር ይቃረናል ብለው ባሰቡት ነገር ሁሉ ላይ በመመስከር ፍርሃት የለሽ ደፋሮችና በሕሊና የታመኑ በነበሩት በእነዚህ በተወደዱ የሥራ ባልደረቦች ነው። ፍቅር ይገዛ ነበር፤ ነገር ግን በትክክልና በስሕተት ጕዳዮች ከልቅነት ጋር አልተምታታም፤ በቃሉ የተማረውን ይበልጥ በግልጽ ባዩ መጠን ለጌታ ትምህርትና አመራር ፈጽመው ለመታዘዝ፣ እንዲሁም በግልም ሆነ በሕዝብ በእያንዳንዱ የግዴታ ዘርፍ ያለውን ጕዳይ ሁሉ ምንም ያህል ትንሽ ቢሆን በተገለጠው የእግዚአብሔር ፈቃድ መሠረት ለመቅረጽና ለማነጽ ፈለጉ።

በጃንዋሪ 1834 አማኞች ያልሆኑ መምህራን ሁሉ ከሰንበት ትምህርት ቤት ተሰናበቱ፤ በዶርቃ ማኅበርም ለድሆች ልብስ እንዲሰፉ የተቀበሉት አማኝ እኅቶች ብቻ ነበሩ። ምክንያቱም አማኞችንና የማያምኑትን ማቀላቀል ወይም በአንድ ቀንበር ማጣመር ጥበብ የጐደለውና ጤናማ ያልሆነ መሆኑ ስለ ታወቀ ነው።* እንዲህ ያለው ኅብረት ለመንፈሳዊ ውይይት እንቅፋት፣ ለሁለቱም ወገኖች ጐጂ ሆኖ ተገኘ፤ በማያምኑት ዘንድ የሐሰት ዋስትናን ያሳድጋል፤ በክርስቲያን ሥራ መርዳት ኢየሱስ ክርስቶስን አዳኝ አድርጎ አለመቀበልን በሆነ መንገድ ሊያስተሰርይ፣ ወይም ከእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስንና ወደ መንግሥተ ሰማያት የተከፈተ በርን ሊያስገኝ ይችላል በሚል አታላይ ተስፋም ያጠምዳቸዋል። የእግዚአብሔር ልጆች ከዓለም ልጆች ጋር ያለ ልዩነት በ«ድብልቅ ሕዝብ» ውስጥ መቀላቀላቸው ሁሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑ ጥርጥር የለውም። ዳግም ያልተወለዱ ሰዎች ከአምላኪዎችና ከሠራተኞች ጋር በመቀላቀል፣ በተለይም ወንጌልንና ተቋሞቹን ለመደገፍ በመስጠት ቢያንስ አንዳች ብቃት ያለ ይመስላቸው ዘንድ ይፈተናሉ። ዲያብሎስ እንዲህ ያሉትን ሰዎች በውጭ ለሃይማኖታዊ ሥርዓቶችና ልማዶች መገዛት፣ በውጫዊ የአገልግሎትና የመሥዋዕትነት ተግባራትም መሳተፍ በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዳለው፣ እርሱም አለማመናቸውና አለመታዘዛቸው ቢኖርም በርኅራኄ እንደሚይዛቸው ሊያሳምናቸው ይሻል። አቶ ሙለርና አቶ ክሬክ ይህ አደጋ መኖሩንና በትንንሽ ጕዳዮች እንኳ ለሚመለከታቸው ሁሉ ሲባል የመለያ መስመር ሊኖር እንደሚገባ በጥልቅ ተሰማቸው።

* 2ኛ ቆሮንቶስ 6:14-18።

በ1837 ከቤተ ሳይዳ ጉባኤ ጋር በተያያዘ፣ በተለምዶ የዝግ ማዕድ ኅብረት ጥያቄ ተብሎ የሚታወቀው፣ ማለትም አማኞች ሆነው ያልተጠመቁ ሰዎች ወደ ኅብረት ሊቀበሉ ይገባል ወይ የሚለው ጥያቄ በተነሣ ጊዜ፣ እርሱም እንደዚሁ ለአንዱ መመዘኛ፣ ለግልጹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቀረበ። አንዳንድ አማኞች በሕሊናቸው እንዲህ ያለውን መቀበል ተቃወሙ፤ ጕዳዩ ግን በመጨረሻ «ጌታችንን ኢየሱስን የሚወዱትን ሁሉ፣ ጥምቀትን ሳይመለከት፣ ወደ ሙሉ ማዕድ ኅብረት በመቀበል» በስምምነት ተፈታ፤ አቶ ሙለርም ከአርባ አራት ዓመታት በኋላ ይህን ውሳኔ መለስ ብሎ ሲያስብ ውሳኔው ፈጽሞ የመከፋፈል ምንጭ እንዳልሆነ ይመሰክራል።*

* አባሪ በ።

በሌሎቹ የቤተ ክርስቲያን ጕዳዮች ሁሉ ጸሎትና ቃሉን መመርመር፣ ቅዱሳት ቃላትን ምክር መጠየቅና ከላይ የሆነችውን ጥበብ መሻት ብቸኛው መጠጊያና የችግሮች ሁሉ መፍትሔ ነበሩ። በ1838 የጸደይ ወራት ለማስተካከል በመጠኑ ስሱና አስቸጋሪ የሆኑ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች በተነሡ ጊዜ፣ አቶ ሙለርና አቶ ክሬክ ራሳቸውን ለጸሎትና ለማሰላሰል ሰጥተው ከእግዚአብሔር የተወሰነ አመራር ለመሻት በጸጥታ ከብሪስቶል ለሁለት ሳምንታት ገለል አሉ።

በዚያን ጊዜ አከራካሪ የነበሩት ጕዳዮች፦ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትርጕሙን፣ የአመራረጡንና የአሿሿሙን ሥርዓት፣ የሥልጣኑንና የኃላፊነቱን ወሰን በተመለከተ ሽማግሌነት፤ ትክክለኛ አከባበሩን፣ ድግግሞሹን፣ ተገቢ ተካፋዮቹንና የመሳሰሉትን በተመለከተ ደግሞ የጌታ እራት፣ ነበሩ። ምንም ነገር በትክክል እስኪፈታ ድረስ በመጨረሻ አይፈታም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረት እስኪፈታ ድረስም በትክክል አይፈታም። በቤተ ክርስቲያኒቱ ፊት ከባድ አደጋ ተደቅኖ ነበር—የክርክር ብቻ ሳይሆን የመለያየትና የመከፋፈል አደጋ፤ በእንዲህ ያለ ሁኔታ ደግሞ ተራ ውይይት ብዙ ጊዜ የጠቡን ፍም ያራግባል፣ ተስፋ በሌለው መራራቅም ይደመደማል። እነዚህ መንፈሳውያን እረኞች ጕዳዩን ሁሉ የእምነትና የአኗኗር ብቸኛ ደንብ ወደ ሆኑት ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት፣ በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚመራው ሕልውና ወደ ሆነው ወደ መንፈስ ቅዱስም በማቅረብ ሐዋርያዊውን ዘዴ ተከተሉ፤ የጌታን ሐሳብ ዐውቀው በዚያው መሠረት ይሠሩ ዘንድም ከአንደበት ክርክርና ከሚጋጩ የሰው አስተያየቶች ሆን ብለው ገለል አሉ። ውጤቱም አስቀድሞ እንደሚጠበቀው ለራሳቸው ከላይ የመጣ ግልጽ ብርሃን፣ በወንድሞችም መካከል የአንድነት ፍርድ ሆነ፤ ከዚህም በላይ እግዚአብሔር የእምነትን ድፍረት ከክርስቶስ የዋህነትና ገርነት ጋር አጣምረው ደመናዎች ሁሉ እስኪበተኑና ሰላም እስኪመለስ ድረስ የሚሠሩበትን ጥበብ ሰጣቸው።*

* አባሪ ተ።

ለስምንት ዓመታት ያህል በሁለቱም፣ በጌዴዎንና በቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎቶች አገልግሎት ይካሄድ ነበር፤ ነገር ግን በኤፕሪል 19 ቀን 1840 አቶ ሙለርና አቶ ክሬክ የመሩት የመጨረሻው አገልግሎት በጌዴዎን ተካሄደ፤—ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ቤተ ሳይዳ ዋናው የመሰብሰቢያ ስፍራ ሆነ። የዚህ እርምጃ ምክንያቶች በግምት የሚከተሉት ነበሩ፦

እነዚህ የጋራ እረኞች ከሌሎች አንዳንዶች ጋር በጌዴዎን ቤተ ጸሎት ከሚሰበሰቡት አማኞች ጥቂት የማይባሉት ለቤተ ክርስቲያንም ለዓለምም ሊሰጥ ለሚገባው ግልጽ፣ ቍርጥና የተባበረ ምስክርነት እንቅፋት እንደ ሆኑ በጽኑ ተሰማቸው፤ በዚህም ምክንያት የእግዚአብሔርን ሐሳብ ለማወቅ እየፈለጉ ከብዙ የጸሎትና የምክክር ስብሰባዎች በኋላ ጌዴዎንን የአምልኮ ስፍራ አድርጎ መያዝ ለመተው ተወሰነ። ጕዳዩ የሐዋርያዊውን አምልኮ ንጽሕናና ቀላልነት መጠበቅን፣ በዚህም የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ከአዲስ ኪዳን አብነት ጋር መስማማቱን የሚነካ ነበር። እነዚህ በአንድ ቀንበር በሚገባ የተጣመሩ እረኞች በሚያገለግሏቸው ቅዱሳን መካከል ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆች፣ ትእዛዛትና ልማዶች ጋር ፈጽሞ የማይስማማ ምንም ነገር ስፍራ እንዳያገኝ ለሠራዊት ጌታ ለእግዚአብሔር እጅግ ቀንተው ነበር።

ምናልባት የመደጋገም ስጋት ቢኖርም፣ መንፈሳዊ ውድቀትን ሁልጊዜ የሚያመጡትን አዳዲስ ልማዶች ለማስወገድ ሊተከሉና ሊጠበቁ የሚገባቸው ጠባቂዎች ወይም የወሰን ምልክቶች አድርገው አቶ ሙለርና የሥራ ባልደረባው ያጸኗቸው የነበሩትን መርሆች እዚህ መመዝገብ መልካም ሳይሆን አይቀርም።

1. አማኞች የቤተ እምነት ድንበሮችን፣ ስሞችን ወይም ልዩነቶችን ሳይመለከቱ እንዲያው አማኞች ሆነው ብቻ መሰብሰብ አለባቸው፤ ይህም የወገንተኝነት ማስተካከያና መከላከያ ነው።

2. ቅዱሳት መጻሕፍትን የትምህርት፣ የጠባይና የሥነ ሥርዓት መለኮታዊ ደንብና መመዘኛ አድርገው በጽናት መያዝ አለባቸው።

3. ጌታ ለሁሉም ማነጽ በመንፈሱ ሊሰጥ የሚወድደውን ማንኛውንም መንፈሳዊ ስጦታ በነጻነት መጠቀምን ማበረታታት አለባቸው።

4. በጌታ ቀን የሚደረጉ ጉባኤዎች በዋነኝነት ለአማኞች፣ እንጀራ ለመቍረስና ለአምልኮ መሆን አለባቸው፤ የማያምኑ ሰዎች ከቅዱሳን ጋር ተቀላቅለው ቢቀመጡ ለእንዲህ ያለው ዓላማ የመሰብሰብን መልክ ያደናቅፋሉ፣ አለዚያም በሌሎቹ የአገልግሎቱ ክፍሎችና በጌታ እራት መካከል ዕረፍት እንዲደረግ ያስገድዳሉ።

5. የመቀመጫ ኪራይ ሥርዓት የመደብ መንፈስን፣ ወይም ቢያንስ በድሆችና በሀብታሞች መካከል ያለ የሐሰት ልዩነትን ውጫዊ መልክ ስለሚያስፋፋ መቅረት አለበት፤ በተለይም የመቀመጫ ተከራዮች መቀመጫዎቻቸውን በተለምዶ እንደ ግል ንብረት ስለሚመለከቱ ነው።

6. ለእረኞች ድጋፍ፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥራና በአገር ውስጥና በውጭ ለሚካሄዱ የሚስዮን ሥራዎች የሚዋጣው ገንዘብ ሁሉ በፈቃድ በሚሰጥ መባ መሆን አለበት።

ከእነዚህና ከሌሎች መሰል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሆች አንዳንዶቹ አቶ ሙለርና አቶ ክሬክ ኃላፊነቱን ከመረከባቸው በፊት በጌዴዎን ቤተ ጸሎት በነበሩ ልማዶች አደጋ ላይ እንደ ወደቁ ወይም እንደ ተጣሱ ስለ ታሰበ፣ በአጠቃላይ ያን ቤተ ጸሎት የአምልኮ ስፍራ አድርጎ መያዝ መተው የተሻለ መሰለ። በዚያ የነበሩ አንዳንድ ልማዶች ከእነርሱ በፊት የቆዩ ስለ ነበሩ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ ብለው ያሰቡትን ነገር እንዲተው ቢጠይቁ አላስፈላጊ ዕንቅፋት ሊፈጥርና መራራ ሥር ሊሆን እንደሚችል ለእነዚህ እግዚአብሔርን ለሚፈሩ ወንድሞች ታያቸው፤ ስለዚህ በዚያ ከስምንት ዓመታት ድካም በኋላ የጌዴዎንን ቤተ ጸሎት መተው፣ ከወገንተኝነት ሥርዓት ሁሉ ለመለየትና እያንዳንዱ መንፈሳዊ ስጦታ በነጻነት በሚሠራበት፣ የአዲስ ኪዳን ዘዴዎችም ይበልጥ ሙሉ በሙሉ በሚከተሉበት ስፍራ ለአምልኮ ለመሰብሰብ የተጠሩ መስሎ የተሰማቸውን ሰዎችም ቀድሞ የሚያደናቅፉ ሁኔታዎች ባልነበሩበት በቤተ ሳይዳ ከሌሎች አማኞች ጋር እንዲሰበሰቡ መጋበዝ የፍቅር መንገድ መሰላቸው።

አቶ ሙለር ከቤተ ሳይዳና ከእርሷ ከወጡት ልዩ ልዩ ቅርንጫፎች ጋር ለብዙ ዓመታት እንደ ዋና እረኛ ወይም ሽማግሌ ሆኖ እጅግ የቀረበ ግንኙነት ነበረው፤—ምንም እንኳ እርሱ ፕሪሙስ ኢንተር ፓሬስ፣ ማለትም ከእኩዮች መካከል መሪ ብቻ ቢሆንም። የእነዚህን አብያተ ክርስቲያናት ታሪክ በመቅረጽ እጅግ ብዙ አስተዋጽኦ ያደረጉት ስለ አገልግሎት ሥራና ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት አመራር ያሉት አስተያየቶቹ ስለዚህ የቤተ ክርስቲያን ሕይወት እድገት ለሚተርከው ለዚህ አጭር ታሪክ አስፈላጊ ክፍል ናቸው።

በቃሉ አገልግሎትና በነፍሳት እንክብካቤ ለሚያገለግሉት ወንድሞቹ በተደጋጋሚ እንዲናገር በልቡ ተጭኖበት ነበር። በዓለም ሁሉ በየትም ስፍራ በመድረክና በእረኝነት ውጤታማ አገልግሎት ስለሚገኝባቸው ወሳኝ ምስጢሮች ያለውን ጥልቅ እምነት ሊያስጨብጣቸው ከሚችል ብዙም ይሁኑ ጥቂት ሰዎች ጋር የመገናኘት ዕድሎችን በደስታ ይቀበል ነበር። በረጅሙ ዕድሜው ከአገልጋይ ወንድሞች ጋር ያደረጋቸው እንዲህ ያሉ ስብሰባዎች በመቶዎች ምናልባትም በሺዎች የሚቆጠሩ ነበሩ፤ ምስክርነቱም በሁሉም አጋጣሚ በመሠረቱ አንድ ዓይነት ስለ ነበረ፣ አንድ ንግግር የሁሉም ምሳሌ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል። በአሜሪካ ጕዞዎቹ ወቅት የአንድ ሰዓት ንግግር አደረገ፤ ንግግሩም ተዘግቦ ታትሞ ስለ ነበረ ፍሬ ነገሩ እዚህ ሊቀርብ ይችላል።

በመጀመሪያ ደረጃ በመለወጥ አስፈላጊነት ላይ ታላቅ ትኵረት አደረገ። አንድ ሰው በእውነት ወደ እግዚአብሔር እስካልተመለሰና ይህ ለውጥ በራሱ ላይ መደረጉን እርግጠኛ እስካልሆነ ድረስ ሌሎችን ለመመለስ ብቁ አይደለም። አገልግሎት የሰው ሙያ ሳይሆን መለኮታዊ ጥሪ ነው። እውነተኛው ሰባኪ አዋጅ ነጋሪም ምስክርም ነው፤ ስለዚህ መልእክቱን ከተሞክሮው በሚገኝ የግል ምስክርነቱ መደገፍ አለበት።

ነገር ግን መለወጥ እንኳ በቂ አይደለም፤ ጌታ ኢየሱስን በቅርበት ማወቅ ያስፈልጋል። ሰው ጌታን ወደ ራሱ እንደሚቀርብ አድርጎ ማወቅ፣ በየሰዓቱ ወደ እርሱ በመቅረብ የሚገኘውን ደስታና ብርታትም ማወቅ አለበት። በምንም መንገድ ይሁን፣ በማንኛውም ዋጋ፣ የክርስቶስ አገልጋይ ወደዚህ የቅርብ ግንኙነት መድረስ አለበት። ለሰላምና ለኃይል ፍጹም አስፈላጊ ነውና።

ቀጥሎም በደስታና በፍቅር ማደግ እጅግ ጐልቶ ቀረበ። ራሱን ፈጽሞ በእግዚአብሔር ላይ የሚጥል፣ ራሱን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር የሚያስገዛ፣ ለቃሉም ጥልቅ ፍቅርን ከእርሱም ጋር ቅዱስ ቅርበትን የሚንከባከብ ማንኛውም አማኝ ለሚኖረው ተሞክሮ ወሰን መስጠት አይቻልም። የየማለዳው የመጀመሪያ ሥራ በእግዚአብሔር ደስታን ማግኘት መሆን አለበት።

ሌሎችን የሚመግብ ሰው የራሱን ነፍስ በጥንቃቄ መመገብ አለበት። ቅዱሳት መጻሕፍትን በየዕለቱ ማንበብና ማጥናት፣ ከብዙ ጸሎት ጋር፣ በተለይም በማለዳ ሰዓታት፣ አጥብቆ ተመከረ። በእግዚአብሔር ፊት ጸጥ ማለት አእምሮን እያረጋጋና ከሌላ ጭንቀት ነጻ እያወጣ በልማድ ሊዳብር ይገባል። ቃሉን በቅደም ተከተል ያለማቋረጥ ማንበብ በአጠቃላዩ የቃሉ ትምህርት ላይ ብርሃን ይፈነጥቃል፤ የእግዚአብሔርንም ሐሳቦች በብዝኀነታቸውና በትስስራቸው ይገልጣል፤ የተሳሳቱ አመለካከቶችንም ለማረም ብዙ ይረዳል።

ቅድስና ዋናው ግብ መሆን አለበት፦ ለታወቀው እውነት ሁሉ ፈጥኖ መታዘዝ፣ እግዚአብሔርን በማገልገል ቅን ዓይን፣ ለክብሩም መቅናት። እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኙ የልብ ልማዶች ስለ ተዘነጉ ብዙ ሕይወት በመጠኑም ቢሆን ከሽፏል። ራሷን ከማታውቀው ከትሕትና ጸጋ ይበልጥ የጸጋዎች ዘውድ የሆነ ምንም ነገር የለም። የሰው ውዳሴ ሁሉ እግዚአብሔርን የራሱን ክብር ይሰርቀዋል። ስለዚህ ትሑታን እንሁን፤ ዓይንንም ሁሉ ወደ እግዚአብሔር እንመልስ።

ከኃይል ጋር እንዲሆን መልእክቱ ከእግዚአብሔር መገኘት አለበት። አቶ ሙለር እንዲህ አለ፦ «እግዚአብሔርን ለምኑት፤ ልብም እስኪያርፍ ድረስ አትርኩ። ጥቅሱ ሲገኝ በእርሱ ላይ ለማሰላሰል ተጨማሪ አመራርን ለምኑ፤ በጕዳዩ የእግዚአብሔርን ሐሳብ፣ በአቀራረቡም እርዳታውን ታገኙ ዘንድ የማያቋርጥ ኅብረት ያዙ። ከዚያም ሥራው ከተፈጸመ በኋላ፣ አስቀድማችሁም እንደ ጸለያችሁ፣ ለበረከት እጅግ ጸልዩ።» ከዚያም ከብዙ ዓመታት በፊት ስለ ተዘራ፣ ነገር ግን አሁንም ለጸሎት መልስ ሆኖ ፍሬ ስለሚያፈራ ዘር አንዳንድ አስደናቂ እውነታዎችን ተናገረ።

እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስን በማብራራት ላይ ልዩ ትኵረት አደረገ። የእግዚአብሔር ቃል የስብከት ሁሉ ዋና ምግብ ነው፤ ክርስቶስ እንጂ ሌላ ምንም አይደለም የእውነተኛው የቃሉ አገልግሎት ሁሉ ማእከል። ክርስቶስን በታማኝነትና ያለማቋረጥ የሚሰብክ ሁሉ የእግዚአብሔር ቃል በከንቱ ወደ እርሱ እንደማይመለስ ያገኛል። በቀላሉ ስበኩ። የሉተር ደንብ አንዲት ያልተማረች ሠራተኛ ገረድ እንድትረዳ አድርጎ መናገር ነበር፤ እርሷ ከተረዳች የተማረው ፕሮፌሰር በእርግጥ ይረዳል፤ ነገር ግን ጠቢባን የሚረዱትን ሁሉ የዋሆች ይረዳሉ ማለት እውነት አይሆንም።

አቶ ሙለር ለአገልጋይ ወንድሞቹ ሲናገር ስለ ቤተ ክርስቲያን ሕይወት አመራር በመጠኑም ቢሆን ምክር ሳይሰጥ የቀረበት ጊዜ እምብዛም ነበር፤ ያልዳኑ ዘማሪዎችንና የመዘምራን ቡድኖችን፣ ገንዘብ ለማሰባሰብ የሚደረጉ ዓለማዊ ዘዴዎችን፣ በጸሎት ቤት ውስጥ የመቀመጫ ኪራይንና የመደብ ልዩነትን፣ ወዘተ. በመሳሰሉ እንቅፋቶች ላይ ግልጽ ምስክርነት ይሰጥ ነበር፤ እንደ ጠያቂዎች ስብሰባ፣ የእረኝነት ጕብኝትና ከሁሉም በላይ የእምነት ጸሎት ያሉትን ረዳቶችም ያበረታታ ነበር። የተወሰነ ጸሎትና የማይሰለች ጸሎት እንዲጸለይ አሳሰበ፤ ሰይጣን በመጨረሻ ተስፋ አስቈርጦን ዋጋ እንደሌለው ቈጥረን ጸሎትን እንድናቆም ማድረግ ከቻለ፣ ለጥቂት ቀናት፣ ሳምንታት፣ አልፎ ተርፎም ወራት በጸሎት ብንደክም ግድ እንደማይሰጠው ተናገረ።

ስለ ቀድሞ ዘር መዝራት ስለሚደረግ ጸሎት፣ ወደ እግዚአብሔር በሚያቀርበው ልመና ሁሉ ወደ ፊት ብቻ ሳይሆን ወደ ኋላም እንዴት ይመለከት እንደ ነበር ለዚህ ታሪክ ጸሐፊ ነገረው። ከብዙ ጊዜ በፊት ተዘርቶ ግን ፍሬ ያላፈራ የሚመስለውን ዘር ጌታ ይባርክ ዘንድ እንዲፈቅድ መለመን ልማዱ ነበር፤ ለእነዚህም ጸሎቶች መልስ ሆኖ፣ ከብዙ ዘመን በፊት ያደረገውን የእምነት ሥራውንና የፍቅር ድካሙን እግዚአብሔር በፍቅር እንዳስታወሰ እስከዚያች ቀን ድረስ ማስረጃ እንዳገኘ ተናገረ። ለእግዚአብሔር የተሰጡ መልእክቶች፣ የተበተኑ ትራክቶችና ሌሎች የአገልግሎት መንገዶች ከአምስት፣ ከአሥር፣ ከሃያ፣ አልፎ ተርፎም ከስድሳ ዓመታት በኋላ በመጨረሻ መከር እንዳስገኙ ለማወቅ ተፈቅዶለታል። ስለዚህም በአንድ ወቅት በእንክብካቤያቸው ሥር በነበሩት ሰዎች ልብ ውስጥ እግዚአብሔር በብርቱ እንዲሠራና በፊታቸው የቀረበላቸውን እውነት እንዲያሳስባቸው ያለማቋረጥ እንዲጸልዩ የሥራ ባልደረቦቹን አጥብቆ ይመክር ነበር።

አቶ ሙለር ያዘዘውን ትሕትና ራሱ ተግብሮታል። ሁልጊዜ የጌታ አገልጋይ ብቻ ነበር። አቶ ስፐርጀን በአንዱ ስብከቱ፣ በጨለማው ምክንያት መብራት አብሪውን ሳያየው መብራቶቹ አንዱ በሌላው ተከትሎ በእሳት ሲበሩ ባየ ጊዜ በለንደን ድልድይ ላይ የተፈጠረውን አስደናቂ ትዕይንት ይገልጻል፤ ጆርጅ ሙለርም ራሱ ሳይታይ፣ ሳይስተዋልና ሳይታወቅ ለመቅረት ረክቶ ብዙ ብርሃንን አበራ። የራሱን ክብር በቅንነት አልፈለገም፤ ይልቁንም ለኢየሱስ ክርስቶስ አገልጋይ የሚገባውን የዋህና ዝግተኛ መንፈስ ነበረው።

አቶ ሄንሪ ክሬክ በጌታ ለሠላሳ አራት ዓመታት አብሮ ከደከመ በኋላ በ1866 መሞቱ አቶ ሙለርን እጥፍ በሆነ የኃላፊነት ሸክም በአንጻራዊነት ብቻውን አስቀረው፤ ነገር ግን እምነቱ ለችግሩ የሚበቃ ነበር፤ ሰላሙም ሳይናጋ ቀረ። በዚያን ጊዜ ብሪስቶልን ይጐበኝ የነበረ አንድ የተወደደ ወንድም በቤተ ሳይዳ በሕዝብ የተጨናነቁ አገልግሎቶችን ከመራ በኋላ ከተማዋን ሊለቅ ሲል አቶ ሙለርን «አቶ ክሬክ ስለ ሞተ ሕዝቡን አጽንታችሁ ለመያዝና እንዳይበተኑ ለመከላከል አሁን ምን ልታደርጉ ነው?» ብሎ ጠየቀው። የተረጋጋው መልስም «የተወደድህ ወንድሜ፣ ሁልጊዜ ያደረግነውን እናደርጋለን፤ ወደ ጌታ ብቻ እንመለከታለን።» የሚል ነበር።

ይህ አምላክ ዘወትር ረዳት ሆኗል። አቶ ሙለር ከ1875 እስከ 1892 ባሉት በሚስዮናዊ ጕዞዎቹ አሥራ ሰባት ዓመታት፣ በረጃጅም ጕዞዎቹና የባሕር ጕዞዎቹ መካከል ባሉት ዕረፍቶች በብሪስቶል የሚቆየው ጥቂት ሳምንታት ወይም ወራት ብቻ በነበረበት ጊዜ፣ ከሥራው ከሞላ ጎደል ፈጽሞ ገለል አለ። ይህም የአማኞቹን ጉባኤ በታላቁ የነፍሳት እረኛና ጠባቂ ላይ ይበልጥ እንዲደገፍ አደረገው። ነገር ግን ቤተ ሳይዳ በአንድ መልኩ በብቸኛ እውቅና ያገኙ መሪዎች አድርጎ በአንድ ወይም በሁለት ሰዎች ተወስና አታውቅም፤ እነዚያ ሰባት አማኞች በ1832 በጌታ ማዕድ ዙሪያ ከተሰበሰቡበት ጊዜ ጀምሮ አማኞች በመብትም በግዴታም እኩል ናቸው የሚለው የአዲስ ኪዳን መረዳት ተጠብቋል። ብቸኛው ልዕለ መሪ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ ከእርሱም በታች እርሱ የሚጠራቸውና ብቁ የሚያደርጋቸው ናቸው። እነዚህ ወንድሞች ከተቀበሏቸው መሠረታዊ መርሆች አንዱ የእግዚአብሔር መንፈስ በቅዱሳን ጉባኤዎች ውስጥ እንደሚያስተዳድር ነው፤ ብልቶቹን እያንዳንዳቸውን በአካል ውስጥ እንደ ወደደ እንደሚያደርጋቸው፣ ለአካሉም አገልግሎት የሚሆኑ ስጦታዎችን እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እንደሚያካፍል፤ እውነተኛው ሹመት የእርሱ ሹመት ብቻ እንደ ሆነ፣ የስጦታዎቹም መገለጥ ወንድሞችን ለአንድ ሹመት ወይም ተግባር ብቁ እንደ ሆኑ ለመቀበል በቂ መሠረት እንደ ሆነ፣ መንፈሳዊ ስጦታዎች መኖራቸውም እነርሱን ለመጠቀም በቂ ሥልጣን እንደ ሆነ ነው። የክርስቶስ አካልም እንደ ሰው አካል ነው፦ ዓይን ለማየት፣ ጆሮ ለመስማት፣ እጅና እግር ለመያዝና ለመሄድ እንደ ተሠሩ ግልጽ ነው፤ ይህም መስማማት የእግዚአብሔርን ንድፍም በሰውነቱ ውስጥ ያላቸውን ስፍራም ያሳያል። ስለዚህም ከስድሳ ዓመታት በላይ በጉባኤው ውስጥ የሚያስፈልጉትን አስተማሪዎች፣ ረዳቶችና መሪዎች ሁሉ እንዲያቀርብና ብቁ እንዲያደርግ መንፈስ ቅዱስ ያለ ስጋት ታምኖበታል። በመንፈስ በግልጽ ወደ ተጠሩባቸው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ዘርፎች ለመሰማራት ብቁና ፈቃደኛ የሆኑ ቍጥራቸው ቀላል የማይባል ወንድሞችና እኅቶች ሁልጊዜ ነበሩ፤ ስለዚህም ማንም ሰው የግድ አስፈላጊ አልሆነም። ልዩ ልዩ ወንድሞች ለስብከት፣ ለጕብኝትና ቤተ ክርስቲያንን ለመምራት ብዙም ይሁን ጥቂት ጊዜና ጕልበት ለመስጠት ችለዋል፤ እንደ ጳውሎስ፣ እንደ ጵርስቅላና እንደ አቂላ ድንኳን ሰፊዎች ልዩ ልዩ የንግድ ሥራዎቻቸው ያሏቸውና በዚያም «በእግዚአብሔር ዘንድ ይኑር» የሚለውን ለመፈጸም የሚሹ ሌሎች በብዙ የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከተለመደው ሥራቸው ጋር በሚስማሙ በሌሎች የአገልግሎት ዓይነቶች ጌታ እንደሚመራቸው ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። ስለዚህ የጉባኤው ብልጽግና፣ እድገቱ፣ አመራሩና መታነጹ በእግዚአብሔር ላይ ብቻ የተመሠረተ ሆኗል፤ እርሱም አንዱን ሠራተኛ ከሌላው በኋላ ሲወስድ በምትካቸው ሌሎችን አቅርቧል፤ እንዲሁም ማድረጉን ቀጥሏል።

እንዲህ ያለው ትምህርትና እንዲህ ያለው አኗኗር በቤተ ክርስቲያን ሕይወት ያፈራውን ፍሬ በተገቢው ለመረዳት ቢያንስ በቤተ ሳይዳ ከሚደረጉት የሰኞ ምሽት የጸሎት ስብሰባዎች ወደ አንዱ መግባት ያስፈልጋል። በቀላልነቱ ጥንታዊና ሐዋርያዊ ነው። ከማይታየው የእግዚአብሔር መንፈስ በቀር ማንም አይመራውም። አንድ ወንድም መዝሙር ያቀርባል፤ ከዚያም የጸሎት ጥያቄዎች ይነበባሉ፤ ብዙውን ጊዜም ልመና የጠየቁትና የሚለመንላቸው ሰዎች ስም በግልጽ ይጠቀሳል። ከዚያም ስለ ርእሱ፣ ስለ ቅደም ተከተሉ ወይም ስለሚሳተፉት ሰዎች ምንም ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ ጸሎት፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፣ ዝማሬና ምክር ይከተላሉ። በመንፈስ አመራር ሥር ለመሥራት ሙሉ ነጻነት ይበረታታል፤ የዚህም አመራር መኖር በጸሎትና በዝማሬ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ንባብና በአስተያየቶች ልዩ በሆነ አንድነት፣ እንዲሁም በሚታየው የተስማማ ኅብረት ብዙ ጊዜ በሚያስደንቅ ሁኔታ ይገለጣል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ በኋላም እነዚህ የሰኞ ምሽት የጸሎት አገልግሎቶች አሁንም የተቀደሰ የመሳቢያ ማእከል፣ የልመና መሰባሰቢያና የአገልግሎት መፍለቂያ ናቸው፤ የሚመሩበትም ዘዴ ሳይለወጥ ቀጥሏል።

የመጀመሪያው ጉባኤ እንደ ወገኑ ዘሩ በራሱ ያለበት ዛፍ ሆኖ ተገኝቷል። አቶ ሙለር በሞተበት ጊዜ እነዚያ ሰባት አማኞች ቤተ ክርስቲያን ለመመሥረት ከተገናኙበት ከዚያ የማይረሳ የ1832 ምሽት ወዲህ ስድሳ ስድስት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ቀርቶት ነበር፤ በቤተ ሳይዳ ይሰበሰብ የነበረው የመጀመሪያው የደቀ መዛሙርት ማኅበርም ወደ አሥር አድጎ ነበር፤ ከእነዚህም ስድስቱ አሁን ከእናት ቤተ ክርስቲያን ነጻ ናቸው፤ አራቱ ደግሞ አሁንም በቅርብ ትስስር ቀርተው፣ በቤተ ሳይዳ፣ በአልማ ሮድ፣ በስቶክስ ክሮፍትና በቶተርዳውን ቤተ ጸሎቶች ቢሰበሰቡም በእውነት አንዲት ቤተ ክርስቲያን ናቸው። በአንድ መልኩ ከቤተ ሳይዳ የወጡ ቅርንጫፎች የሆኑት የሌሎቹ አብያተ ክርስቲያናት ስሞች የሚከተሉት ናቸው፦ ዩኒቲ፣ ቢሾፕስተን፣ ከምበርላንድ ሆል፣ ቻርልተን ሆል፣ ኒኮላስ ሮድና ቤድሚንስተር።

አቶ ሙለር በሞተበት ጊዜ የአራቱ ተዛማጅ ጉባኤዎች ጠቅላላ አባላት ከአንድ ሺህ ሁለት መቶ በላይ ነበሩ።

በዚህ አጭር ስፍራ እርሱ እጅግ ይወድደው ስለ ነበረው፣ ለረጅም ጊዜም ስለ ጠበቀውና ስለ ጸለየለት የቤተ ክርስቲያን ሕይወትና ሥራ ሙሉ ገለጻ ሊሰጥ አይችልም። ይህች ቤተ ክርስቲያን የሚስዮን ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤ አሁንም ናት። በማርች 1 ቀን 1836 አቶና ወይዘሮ ግሮቭስ ከአሥር ረዳቶች ጋር በምሥራቅ ሕንድ የሚስዮን ሥራ ለማካሄድ ብሪስቶልን በለቀቁ ጊዜ፣ አቶ ሙለር የሚያገለግለው የደቀ መዛሙርት ማኅበር ከራሱ አባላት መካከል ለሰፊው የዓለም እርሻ ሠራተኞችን እንዲልክ ለመጸለይ በጥልቅ ተነሣሣ። ያ ጸሎት በእግዚአብሔር ፊት አልተረሳም፤ በዚያን ጊዜ ከለመነውና ካሰበው ሁሉ እጅግ አብልጦም አስቀድሞ ተመልሷል። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ስድሳ ያህል ሰዎች በወንጌል ለመድከም ወደ ሩቅ አገሮች ወጥተዋል፤ አቶ ሙለር በሞተበት ጊዜም በልዩ ልዩ የዓለም ክፍሎች ቢያንስ ሃያ ሰዎች በሥራ ላይ ነበሩ፤ እነርሱም የብሪስቶል ወንድሞቻቸው በፈቃድ በሚሰጡት መባ ይረዳሉ።

አቶ ሙለር በ1874 የ«ትረካ»ውን ሦስተኛ ጥራዝ ሲያጠናቅቅ፣ ከአርባ ሁለት ዓመታት በላይ በፊት በብሪስቶል ሥራ በጀመረ ጊዜ በከተማዋ ይኖሩ ከነበሩት ከብዙዎቹ ከመንግሥት ቤተ ክርስቲያን ውጭ የሆኑ የወንጌል አገልጋዮች መካከል አንድም አልቀረም፤ ሁሉም ወደ ሌላ ስፍራ ተዛውረዋል ወይም ሞተዋል፤ ከመንግሥት ቤተ ክርስቲያን ወንጌላውያን ካህናትም ሁሉ በሕይወት የቀረው አንድ ብቻ ነበር የሚለውን ትኵረት የሚስብ እውነታ መዘገበ። እርሱ ራሱ ግን በሕመም ምክንያት እጅግ አልፎ አልፎ ብቻ እየተስተጓጐለ በአእምሮም በሥጋም ጤናና ብርታት እየሰበከና እየደከመ እንዲቀጥል ተፈቅዶለት ነበር፤ በሦስት ልዩ ልዩ ቤተ ጸሎቶች የሚሰበሰቡ ከአንድ ሺህ በላይ አማኞች አስቀድሞ በእረኝነት ቍጥጥሩ ሥር ነበሩ፤ ከሦስት ሺህ በላይ ደግሞ ወደ ኅብረት ተቀብለው ነበር።

አቶ ሙለር በማርች 22 ቀን 1896 ጠዋት በቤተ ሳይዳ ቤተ ጸሎት ሲሰብክ መስማት ለዚህ ጸሐፊ መብት ነበር። ዘጠና አንደኛ ዓመቱ ላይ ነበር፤ ነገር ግን በስብከቱ ውስጥ የኃይል መድከምን ምንም የማያሳይ አዲስነት፣ ብርታትና አጭርነት ነበረ፤ እንዲያውም የእግዚአብሔርን ሐሳቦች ለመግለጽና ለማስጨበጥ ከዚያ ይበልጥ ብቁ መስሎ ታይቶ አያውቅም።

ርእሱ ሰባ ሰባተኛው መዝሙር ነበር፤ እርሱም ለሚወድደው ርእሰ ጕዳይ—ለጸሎት—ሰፊ ዕድል ሰጠው። መዝሙሩን ቍጥር በቍጥር በግልጽ፣ በርኅራኄና በውጤታማነት አብራራ፤ የአቀራረቡም ዝርዝር በትዝታዬ ላይ በብርቱ ተቀርጾ ስለ ቀረ እዚህ እንደ ገና ቀርቧል።

«በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ።» ጸሎት ድምፅን ትሻለች—ራሷን በቃላት ለመግለጽ፤ ምኞቶቻችንን በቋንቋ ለማልበስ የምናደርገው ጥረት ለምኞቶቻችን ግልጽነትን ይሰጣል፣ ትኵረታችንንም በጸሎቱ ጕዳዮች ላይ ያቆያል።

«በመከራዬ ቀን።» መዝሙረኛው በመከራ ውስጥ ነበር፤ ምናልባት በአእምሮው ብቻ ሳይሆን በሥጋውም ላይ አንዳች ጭንቀት ነበረበት፤ ይህም ሌሊትና ቀን የማያቋርጥ ሸክም ነበር።

«ነፍሴ መጽናናትን እንቢ አለች።» «ቍስሌ በሌሊት ፈሰሰ» የሚለው ቃል «እጄ ተዘረጋች» ተብሎ ሊተረጐም ይችላል፤ ይህም በጸሎት ማለት ነው። ነገር ግን አለማመን አሸነፈ፤ ነፍሱም መጽናናትን ሁሉ፥ የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃሎች መጽናናት እንኳ፥ እንቢ አለች። መከራው እምነቱን ጋረደው፤ የእግዚአብሔርንም ራእይ ከለለበት።

«እግዚአብሔርን አሰብሁ ደነገጥሁም።» የእግዚአብሔር ሐሳብ እንኳ ሰላምን በማምጣት ፈንታ ጭንቀትን አመጣ፤ ማጕረምረሙን ከማስታገስ ይልቅ አበዛው፤ መንፈሱም ተዋጠ። ይህም ደግሞ የአለማመን የተረጋገጠ ምልክት ነው። በመከራ ጊዜ የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎችና የእግዚአብሔር ሐሳብ ዕረፍት ካልሰጡ፥ ተጨማሪ ሸክም ብቻ ይሆናሉ።

«ዓይኖቼን እንዲተጉ አደረግሃቸው።» ዕረፍትም ሰላምም ስላልነበረ እንቅልፍ አልነበረም። ጭንቀት እንቅልፍን ያሳጣል። ሥጋት የዕረፍት ጠላት ነው። መንፈሱ የማያምን ስለ ነበረ ዓመፀኛም ነበር። እግዚአብሔርን በቃሉ አላመነውም።

«የቀድሞውን ዘመን አሰብሁ።» አሁን ትዝታ መሥራት ጀመረ። ቀድሞ ያሳለፋቸውን የመከራና የመዳን ልምዶች ያስታውሳል። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔርን ፈልጎ ተሰምቶለትና ተረድቶ ነበር፤ ታዲያ አሁን ለምን አይሆንም? በልምዱ መዛግብት መካከል በትጋት ሲመረምርና የእግዚአብሔርን ግልጥና ብዙ ጣልቃ ገብነቶች ሁሉ ሲያስታውስ፥ እግዚአብሔር ተለዋዋጭና ወላዋይ ይሆን እንደ ሆነ፥ ምሕረቱ አልቆ የተስፋ ቃሉ ተሰብስቦ እንደ ሆነ፥ የጸጋ ኪዳኑን ረስቶ የፍቅሩን ምንጮች ዘግቶ እንደ ሆነ መጠየቅ ጀመረ።

እንዲህ ዘማሪውን በስድስት የአለማመን ደረጃዎች እንከተለዋለን፦

1. የእግዚአብሔር ሐሳብ በረከት በመሆን ፈንታ ሸክም ይሆናል።

2. በእግዚአብሔር ላይ የሚያጕረመርመው መንፈስ እየበዛ ይሄዳል።

3. መንፈሱ ከመረጋጋትና ከመጽናናት ይልቅ ይታወካል።

4. እንቅልፍ ይርቃል፤ ሥጋትም የልብን ዕረፍት ይከለክላል።

5. መከራው እየጠለቀ ብቻ ይሄዳል፤ እግዚአብሔርም የራቀ ይመስላል።

6. ትዝታ የእግዚአብሔርን ምሕረቶች ያስታውሳል፤ ነገር ግን አለመታመንን ለመቀስቀስ ብቻ ነው።

በመጨረሻም በመዝሙሩ ውስጥ ወዳለው የመዞሪያ ነጥብ እንደርሳለን፤ የቀድሞውን ልምዱን እየመረመረ፦ ልዩነቱ የት ላይ ነው? ለውጡ በእግዚአብሔር ነው ወይስ በእኔ? ብሎ ይጠይቃል። «ሴላ» የሚለው ቃል፥ ይህ ቆም ማለት በክርክሩ ወይም በልምዱ ውስጥ ያለውን ይህን የመዞሪያ ነጥብ ያመለክታል።

«እኔም፦ ይህ ድካሜ ነው አልሁ።» በሌላ አነጋገር «ሞኝ ሆኛለሁ!» ማለቱ ነው። እግዚአብሔር ታማኝ ነው። ፈጽሞ አይጥልም። ልጆቹ ሁልጊዜ በእርሱ ዘንድ የተወደዱ ናቸው። ጸጋው የማያልቅ፥ የተስፋ ቃሉም የማይታጠፍ ነው። ዓይኖቹን በመከራው ላይ በማተኰር ፈንታ አሁን አሳቡን ሁሉ በእግዚአብሔር ላይ ያተኵራል። ሥራውን ያስታውሳል፤ ያሰላስለውማል፤ የራሱን ፈተናዎች ከመደጋገም ይልቅ ስለ እርሱ ሥራዎች ይናገራል። አሁን የሚዋጠው በመከራው ታላቅነት ሳይሆን በረዳቱ ታላቅነት ነው። የኀይሉንና የፍቅሩን ተአምራት ያስባል፤ የብርቱ ሥራዎቹን ምሥጢር ያስታውሳል፤ በባሕር ውስጥ ያለውን መንገዱን፥ እንግዳ የሆነውን አያያዙንና አመራሩን፥ የእነዚህንም ጸጋ የተሞላ ፍሬ ያስባል፤ እንዲህም እምነት እንደ ገና ድል ያደርጋል።

ታዲያ መደምደሚያው፥ የተግባር ትምህርቱ ምንድር ነው?

አለማመን ሞኝነት ነው። እግዚአብሔርን በስንፍና ይከሳል። ድካምና ውድቀት የሰው ናቸው እንጂ ፈጽሞ የእግዚአብሔር አይደሉም። እምነቴ ሊጐድል ይችላል፤ ኀይሉ ግን አይጐድልም። ትዝታና ማሰላሰል በትክክል ሲመሩ አለማመንን ያርማሉ። እግዚአብሔር ራሱን ታላቅ አድርጎ ገልጧል። ሁልጊዜም ድንቅ ሥራዎችን አድርጓል። የማያምንና የሚያጕረመርም ሕዝብን እንኳ ከግብፅ አውጥቶ አርባ ዓመት በምድረ በዳ መራ፤ የኀይሉና የፍቅሩ ተአምራትም አስደናቂ ነበሩ።

መዝሙሩ ታላቅ ትምህርት ይዟል። መከራ የማይቀር ነው። የእኛ ድርሻ ግን ልጆቹን የማይተዋቸውን አብን ፈጽሞ ከዓይናችን አለማጣት ነው። ሸክምን ሁሉ በእርሱ ላይ ጥለን በትዕግሥት ልንጠብቅ ይገባናል፤ መዳንም የተረጋገጠ ነው። እርሱ ከመጋረጃው በስተ ጀርባ የፍቅሩን ዕቅድ ይፈጽማል፤ ፈጽሞ አይረሳንም፤ ሁልጊዜም ለገዛ ወገኖቹ ይጠነቀቃል። አያያዙን ልንከታተል አንችልም፤ ፍለጋው መንገድ በሌለው ባሕር ውስጥ ነውና፤ ለእኛም የማይታወቅ ነው። ነገር ግን እርሱ በእርግጥ እየመራ ነው፤ ያለማቋረጥም እየወደደ ነው። እንግዲህ ሞኞች አንሁን፤ ይልቁንም ወደ ታማኙ አምላክ በእምነት እንጸልይ።

የዚያ ማለዳ ማብራሪያ ፍሬ ነገር ይህ ነው፤ በዚህ የቀረበው እጅግ በጐደለ ሁኔታ እንደ ሆነ እውነት ነው፤ ቢሆንም አቶ ሙለር ቃሉን የሚያብራራበትንና በሕይወት ላይ የሚያውልበትን መንገድ ከማሳየቱም በላይ፥ የዚህ መዝሙር ማብራሪያ የሕይወቱም መግለጫ ዓይነት ነው። የጸሎት ልማዶቹን፥ ከአለማመን ጋር ያደረገውን ትግል፥ እግዚአብሔርን ላለመታመን ከሚመጡ ፈተናዎችም እንዴት መዳንን እንዳገኘ ይገልጣል፤ ስለዚህም ለምናጠናው የሕይወት ታሪክ በልምድ ላይ የተመሠረተ ማብራሪያ በመሆኑ ለእኛ እጥፍ ዋጋ አለው።

ጨርሰዋል፦ የቤተ ክርስቲያን ሕይወትና እድገት

ቀዳሚ ቀጣይ