ምዕራፍ 17 · 20 ደቂቃ ንባብ · 26 ደቂቃ ማዳመጥ
ልዩ ልዩ የሆነው የእግዚአብሔር ጸጋ
አንድ ሰው በሃያ ሦስተኛው መዝሙር ላይ አስተያየት ሲሰጥ በሚያስገርም አነጋገር፣ «የጌታ ቅዱሳን የሚሳፈሩበት ሰረገላ ነጂ ብቻ ሳይሆን ሁለት አጃቢ አገልጋዮችም አሉት» ብሏል—«ቸርነትና ምሕረት ይከተሉኛል።»
በእርግጥም እነዚህ ሁለት የጌታ አጃቢዎች ሰማያዊውን የጸጋ መለዮ ለብሰው ጆርጅ ሙለርን በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ተከትለውታል። በአሽሊ ዳውን ላይ የተሠሩት የእነዚያ አምስት የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶች ታሪክ ድንቅ ቢሆንም፣ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምሕረት ከዚያ ባልተናነሰ ሁኔታ ያሳዩ ሌሎች ብዙ ክስተቶችና ገጠመኞች ነበሩ፤ የቸርነት አያያዙን ምንም እንኳ ፍጹም ባልሆነ መንገድ ቢሆን ልንከታተል ከፈለግን፣ እነዚህም በዚህ መጽሐፍ ገጾች ሳይመዘገቡ ሊቀሩ አይገባም። የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ቤቶች ታሪክ በአንድ ሰፊ ዕይታ ከቃኘን በኋላ፣ ከእነዚህ ቤቶች የመጀመሪያው ወደ ታቀደበት ዓመት ተመልሰን፣ በሌላ ጎዳና በመጓዝ የአቶ ሙለርን የግልና የቤተሰብ ሕይወት ልንመለከት እንችላለን።
እርሱ ራሱ የጌታን ቸርነትና ምሕረት መከታተል ይወድ ነበር፤ እነዚህም እንደ ተከተሉት የሚያሳዩ ብዙ ማስረጃዎችን አየ። ከተለያዩ የሕይወት ገጠመኞች የተወሰዱ ጥቂት ምሳሌዎች እንደ ናሙና ሊቀርቡ ይችላሉ።
የጌታ ርኅሩኅ ጥንቃቄ በተወደደችው ልጁ በሊድያ ጉዳይ ተገለጠ። በ1843 ለእናቲቱ ዕረፍት እንዲሆንና ለልጅቱም እንዲጠቅም ሊድያ ከቤት ይልቅ በሌላ ስፍራ ብትማር እንደሚሻል ግልጽ ሆነ፤ አባቷም ለጸሎቱ መልስ ሆኖ በእግዚአብሔር ምሪት ወደ አንዲት ክርስቲያን እኅት ተመራ፤ ይህች እኅት ልጆችን በማስተማርና በማሳደግ ረገድ የነበራት ልዩ ስጦታ ለአማኞች ሁሉ ለእያንዳንዳቸው እንደ ፈቃዱ ከሚያካፍለው ከመንፈስ የተገኘ መሆኑ በግልጽ ይታይ ነበር። የሊድያን ትምህርት የመቈጣጠርን ኃላፊነት የተሞላበት ተግባር እንድትረከብ እግዚአብሔር የመረጣት ሴት ትመስል ነበር። አቶ ሙለር ለእንዲህ ያለው ትምህርት ለመክፈል ጠብቆም ፈልጎም ነበር፤ ሒሳቡንም ጠየቀ፤ በመጀመሪያውም ጊዜ ከፈለ፤ ነገር ግን ልክ ያው ገንዘብ ስሙን ባልገለጠ ሰው በኩል ተመለሰለት፤ ልጁ በዚያ በቆየችባቸው በቀሩት ስድስት ዓመታትም ለትምህርቷ ሌላ ምንም የክፍያ ሒሳብ ሊያገኝ አልቻለም። በዚህም ሁኔታ እግዚአብሔር ለዚህች ብቸኛ ልጅ ምግብና ትምህርት አዘጋጀ፤ ይህም ለወላጆቿ ያለ ምንም ወጪ ብቻ ሳይሆን፣ በእውነተኛው «በጌታ ምክርና በተግሣጽ» እያደገች ስለ ነበረች ፍጹም እርካታ የሰጣቸው ነበር፤ በዚህ ትምህርት ቤት ሳለች፣ በኤፕሪል 1846፣ ሊድያ በማመን ሰላምን አገኘች፤ ከዚያም በኋላ ለአርባ አራት ዓመታት የእርሱን መልክ በልዩ ሁኔታ ያንጸባረቀውን ያንን በጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን ውብ ሕይወት ጀመረች።
ብዙ ክርስቲያን ወላጆች የልጆቻቸውን ትምህርት መንፈሳዊ ሳይሆን የአእምሮ ብቻ ስጦታ ላላቸው፣ በእጃቸው የተሰጡትንም ታዳጊ ተማሪዎች ወደ ሃይማኖት የለሽ ወይም ወደ ከሓዲ ሕይወት፣ ቢያንስ ደግሞ ወደ ተራ ምሁራዊነትና ዓለማዊ ምኞት ለሚያስቱ ሰዎች በአደራ በመስጠት ገዳይ ስሕተት ሠርተዋል። በጥቂት ባልሆኑ ሁኔታዎች እግዚአብሔርን የሚፈራ ቤት ያሳደረው ተጽዕኖ ሁሉ በአንድ ትምህርት ቤት ድባብ ተሽሯል፤ ያ ትምህርት ቤት ከእግዚአብሔር የራቀ ባይሆን እንኳ፣ ጠባይ ለዘላለም በሚቀረጽበት በዚያ ለስላሳ የዕድሜ ዘመን ስሜታቸው ቶሎ የሚነካ ልጆችን በእውነት ለማሳደግ የግድ አስፈላጊ የሆነው የመንፈሳዊ ተመስጦና የመቀደስ መዓዛ የጐደለው ነበር!
አቶ ሙለርና ወይዘሮ ሙለር በ1845 በጀርመን በቆዩበት ጊዜ፣ ይኸውም ከጁላይ 19 እስከ ኦክቶበር 11 ባሉት ሦስት ወራት ገደማ፣ ቸርነትና ምሕረት በግልጽ ተከተሏቸው።
እግዚአብሔር ወንድሞች በከባድ ስሕተት ወድቀው እንደ ገና የረዳት እጅ ወደሚያስፈልጋቸው ወደ ሽቱትጋርት በግልጽ መራ። አቶ ሙለር ወደ አውሮፓ ምድር ከመነሣቱ ከሁለት ወር በላይ አስቀድሞ፣ ለተወሰነ ጊዜ ወደዚያ መመለስ እንዳለበት ብርቱ ስሜት ባደረበት ጊዜ፣ በሜይ 3 ለጉዞው የሚሆን ገንዘብ እንዲሰጠው በተለይ መጸለይ ጀመረ፤ ከዚያም ከሩብ ሰዓት በኋላ አምስት መቶ ፓውንድ ደረሰ፤ ሰጪውም ገንዘቡ ለታቀደው ለዚህ ጉዞ «ከጉዞው በፊት ለሚያስፈልገውና ከጉዞው ጋር ለሚያያዘው» ወጪ ሁሉ የተሰጠ መሆኑን ገለጸ። እርሱ በውጭ አገር ሳለም ያው ቸርነትና ምሕረት እርምጃውን ሁሉ ተከተሉ። ከተማዋ ባልተለመደ ሁኔታ በሕዝብ በተጨናነቀችበት ወቅት፣ እግዚአብሔር በራሱ ድንቅ መንገድ በሽቱትጋርት ተስማሚ ማረፊያ አዘጋጀ፤ ከዚያ በፊት ክፍሎችን አከራይቶ የማያውቅ አንድ ጡረታ የወጣ ባለጠጋ የቀዶ ጥገና ሐኪም እንዲያከራይ ልቡ ተነሣሣ። የአቶ ሙለር ድካም ሁሉ በበረከት የታጀበ ነበር፤ በከፊሉ ጊዜ በሳምንት እስከ ስምንት ስብሰባዎች ያካሂድ ነበር፤ በጀርመንኛ አሥራ አንድ ትራክቶችን ለማሳተም፣ ከእነርሱም ከሁለት መቶ ሃያ ሺህ በላይ፣ እንዲሁም ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ «ትረካ» መጻሕፍቱን በጥበብ ለማሰራጨት ቻለ፤ ይህን ሁሉ ሲያደርግም የፖሊስን ጣልቃ ገብነት አመለጠ።
በዚህ በውጭ አገር ቆይታ ከተከሰቱት ገጠመኞች አንዱ፣ ለሌሎች አመለካከት በፍቅር ስለ መቻቻልና ከሁኔታዎች ጋር በፍቅር ስለ መስማማት ለሚያስተምረው ትምህርት በተለይ ሊጠቀስ ይገባዋል። ከመንግሥት ቤተ ክርስቲያን አባላት መካከል ወደ አንድ መቶ ሃምሳ የሚሆኑትን በሚያሰባስቡ ስብሰባዎች ላይ ለመናገር በእግዚአብሔር አሠራር በር ተከፈተለት። በእርሱ አመለካከት የእንዲህ ያሉ ጉባኤዎች ባሕርይ ሙሉ በሙሉ ከመጽሐፍ ቅዱስ ሥርዓት ጋር የተስማማ አልነበረም፤ ስለዚህም ሙሉ በሙሉ አልተቀበለውም ነበር፤ ነገር ግን ስለ እውነት ሲል ምስክርነት ለመስጠትና ስለ ፍቅር ሲል በዋና ዋና ነገሮች ላይ ክርስቲያናዊ አንድነትን ለማሳየት እንዲህ ያለ ዕድል ስለ ተገኘ፣ በዚህ በተከፈተ በር መግባቱ ከጌታ እንደ ሆነ ወሰነ። አቶ ሙለርን በጥቂቱ ብቻ የሚያውቁት፣ ነገር ግን የጸና እምነቱንና ለእምነቱ ያለውን የማያወላውል ታማኝነት የሚያውቁ ሰዎች፣ ጥቃቅን ስሕተቶችን እንኳ ብዙም እንደማይታገሥና በእነዚያ ስሕተቶች ለተጠመዱት ሰዎች ራሱን ለማስማማት ከጽኑ የማይታጠፍ አቋሙ ዝቅ እንደማይል ሊጠረጥሩ ይችሉ ነበር። እርሱን ይበልጥ የሚያውቁት ግን እርሱ የ«ጤናማ ቃል ምሳሌ»ን «በክርስቶስ ኢየሱስ ባለ እምነትና ፍቅር» አጥብቆ እንደ ያዘ አዩ። ጳውሎስ «በሁሉ መንገድ አንዳንዶችን አድን ዘንድ፥ ከሁሉ ጋር በሁሉ ነገር እንደ እነርሱ ሆንሁ» እንዳለ፣ እርሱም እንደ ጳውሎስ ለዚህ ዘወትር የተዘጋጀ ነበር፤ በጠባዩና በአካሄዱ ሁሉ ከፍቅር ይበልጥ በውበት ያበራ ምንም ነገር አልነበረም። ሌሎችን ከፍ ማድረግ የሚሻ ሰው እነርሱን ለመያዝ ራሱን ዝቅ ማድረግ እንዳለበት ተሰማው፤ ወንድሞችን ለመርዳት እነርሱን መታገሥ እንዳለብንና አነስተኛ ክብደት ያላቸውን ጉዳዮች ዋናና መሠረታዊ እንደ ሆኑ አድርገን አጥብቀን መሟገት እንደሌለብን ተገነዘበ። ስለዚህም አካሄዱ ያለ አግባብ የሚያርቅ ከመሆን ይልቅ በርኅራኄ የሚያቀራርብ ነበር፤ የእውነትና የግዴታ አመለካከቶቹን በዚያ ያህል ጽናትና ጥብቀት ይዞ ሳለ፣ የጠባብነት አለመቻቻል በፍቅር ትዕግሥት በመተካቱ፣ ጌታ ሲመራውና ሁኔታዎች ሲጠይቁ የእምነቱን ቍርጠኝነትም ሆነ የምስክርነቱን ቅንነት ሳያጐድል ትክክለኛነታቸውን ለሚጠራጠራቸው ልማዶች ለጊዜው መገዛት መቻሉ የጸጋ ጉልህ ምልክት ነበር።
ለእርሱ የሚሆኑ የልግስና ነገሮች በታሰቡ ቍጥር እግዚአብሔር እንዲህ ያሉትን ምኞቶች ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ገንዘብ በልግስና በመስጠት መመለሱ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምሕረት ያሳያል። ይህም በወላጅ አልባ ሕፃናቱ ሥራ ብቻ ሳይሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም ታሪክም በብዛት ታይቷል፤ በዚያ ለብዙ ዓመታት የዚህ ሥራ የተለያዩ ቅርንጫፎች ሙሉ ዕድገታቸው ላይ እስኪደርሱ ድረስ እጅግ በፍጥነት አደጉ። በአንዳንድ ዘርፎች ከመስፋፋት በኋላ መኰማተር እንዲመጣ እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘበት ጊዜ በእርግጥ መጣ፤ ነገር ግን በዚህም እንኳ ቸርነት ገዛ፤ ይህ የሆነው ሌሎች ወንድሞች እንዲህ ያሉትን የጌታን ሥራ ቅርንጫፎች እንዲይዙ ስለ ተመሩ መሆኑ በኋላ ታይቷልና፤ በእነዚህ ዕድገቶች ሁሉ አቶ ሙለር በእግዚአብሔር የተከበረው የራሱ ብቻ ሥራ እንደ ሆነ ያህል በእውነት ደስ አለው።
በሚስዮን መስኮች ያሉ ወንድሞችን መርዳት በልቡ እየተወደደ ሄደ፤ ይህንንም ራስ ወዳድነት የሌለበትን ምኞቱን ለመፈጸም የሚያስችለው ገንዘብ እጅግ ስለ በዛ፣ በ1846 የጌታን አያያዝ ታሪክ መለስ ብሎ ሲመረምር፣ በቅርብ ዓመታት ከቀድሞው ሰባት እጥፍ ያህል ለማውጣት እንደ ተቻለው አገኘ። እዚህ ላይ እንደ ገና አስቀድመን እንጥቀስ፤ ከአሥራ ዘጠኝ ዓመታት በኋላ፣ በ1865፣ ይረዳቸው ለነበሩት በጌታ ለሚደክሙ ሠራተኞች ለእያንዳንዳቸው ሊልክላቸው የሚገባውን ገንዘብ ለመደልደል በተቀመጠ ጊዜ፣ የእንዲህ ያሉ አንድ መቶ ሃያ ሁለት ሰዎችን ስም በፊቱ አገኘ! በእርግጥም ቸርነትና ምሕረት! ይህ የሥራው አንድ ቅርንጫፍ ብቻ ነበር፤ ሆኖም እስከ ምን ያህል መጠንና ፍሬያማነት አድጎ ነበር! የመደበላቸውን ለመሙላት አራት መቶ ስድሳ ስድስት ፓውንድ ያስፈልገው ነበር፤ ከዚህም መጠን ዘጠና ሁለቱ ጐደለው። ጕድለቱን ወደ ጌታ አቀረበ፤ በዚያው ምሽት አምስት ፓውንድ፣ በማግሥቱም ጠዋት ሌላ መቶ፣ በተጨማሪም ሃምሳ የሆነ «የልደት ቀን መታሰቢያ» ተቀበለ፤ በዚህም በአጠቃላይ ከጠየቀው በላይ ሠላሳ ሰባት ተረፈው።
በሥራው ምክንያት የሚመጡበትን ከባድ የጭንቀት ሸክሞች ለመሸከም ዘወትር በነበረው ብርታት ምንኛ ቸርነትና ምሕረት ተከተሉት! የጌታ ሰረገላ እርሱንና ሸክሞቹን አብሮ ተሸከመ። ምንም እንኳ በሽታ ወደዚህ ትልቅ ቤተሰብ ቢገባ፣ ለሚወጡት ወላጅ አልባ ልጆች ተስማሚ ቤትና ሥራ፣ ለሚገቡትም ተስማሚ እንክብካቤና ሥልጠና መገኘት ቢያስፈልግ፣ ቀውሶች ያለማቋረጥ ቢነሡና አዳዲስ ፍላጎቶች ደጋግመው ቢመጡ፣ ከባድ ጉዳዮች በየቀኑ ጸሎትንና ንቃትን ቢጠይቁ፣ የማያቋርጥ ትጋትና ጥንቃቄም ቢያስፈልግ፣ ቸሩ ጌታው ዕለት ዕለት ሰላሙን ሳይናጋ ጠበቀለት፤ ጌታ ረዳቱ ነበርና፣ ሸክሞቹንም ሁሉ ተሸከመለት።
በ1846-7 የብርድ ወራት የተለየ የእጥረት ወቅት ነበር። የእግዚአብሔር ቸርነትና ምሕረት ይጐድሉ ይሆን? ከግማሽ በላይ ባለማመን እየተመለከቱ፣ ለሌሎች ባይሆንም ለራሳቸው «አሁን አቶ ሙለርና ወላጅ አልባ ልጆቹ እንዴት ይሆኑ ይሆን! እንደ ቀድሞው አሁንም ሊያቀርብላቸው ከቻለ ምንም አንልም» የሚሉ ሰዎች ነበሩ። ነገር ግን በዚህ ሰፊ የችግር ወቅት ሁሉ ምስክርነቱ «ምንም አላጣንም፤ እግዚአብሔር ይረዳናል» የሚል ነበር። መንገዱ ለዓይን እጅግ በጨለመ ጊዜ እምነት መራ፤ እንዲያውም መንገዱ በጨለመ ቍጥር ዕውሮችን በማያውቁት መንገድ የሚመራው እጅ ይበልጥ ይሰማ ነበር። ከሥራው መጀመሪያ ጀምሮ እንዳሳለፉት እንደ ማንኛውም የብርድ ወቅት ያንንም በቀላሉ አሳለፉት!
ሥራው የእምነትና የጸሎት ሥራ መሆኑን ፈጽሞ አለማቆሙ የእግዚአብሔር «አጃቢዎች» ጆርጅ ሙለርን እንደ ተከተሉት የሚያሳይ ምልክት አይደለምን? ምንም ዓይነት ችግር ወይም ተስፋ መቍረጥ፣ ምንም ዓይነት ስኬት ወይም ድል፣ ሥራው ከተመሠረተባቸው ታላላቅና መሠረታዊ መርሖች ለአንድ ሰዓት እንኳ ፈቀቅ እንዲል ወይም ከተገነባለት ዓላማ ዘወር እንዲል አለማድረጉስ?
በእግዚአብሔር እጅግ የተከበረ አንድ ወንድም የእምነት ሥራ ከጀመረ በኋላ፣ ሥራው በበለጠ መጠን ባደገ ጊዜ መሠረቱን ወደ ንግድ ዕቅድ የለወጠ መስሎ እንደ ታየ ሲነገር ሰምተናል። በ1834 በብሪስቶል የተተከለው ቅዱስ ድርጅት በእነዚህ ሁሉ ዓመታት በዋና ባሕርያቱ እንዲህ ያለ ለውጥ አለማወቁ እግዚአብሔርን እንዴት ያከብረዋል! ሥራው፣ ከእርሱም ጋር ፍላጎቶቹ፣ እያደጉ ሄደው ወጪዎቹ የመጀመሪያው የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት በዊልሰን ጎዳና በተከፈተ ጊዜ ከነበረው ሁለት እጥፍ፣ ሦስት እጥፍ፣ አራት እጥፍ፣ በመጨረሻም ሰባ እጥፍ ቢሆኑም፣ የመሠረት ለውጥ አልነበረም፤ ለደጋፊነት ወይም ለድጋፍ ወደ ሰው መመልከት፣ በቋሚ ገቢ ወይም በተወሰነ ርስት መደገፍ ፈጽሞ አልነበረም። እግዚአብሔር በእነዚህ ሁሉ ዓመታት እንደ መጀመሪያው ብቸኛ ደጋፊና መታመኛ ሆኗል። የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም በገንዘብ ውድቀት ዓለት ላይ ተሰብሮ አልጠፋም፤ በእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች አስተማማኝ የመልሕቅ መጣያ ላይ ከታሰረበት ከመጀመሪያው መቆሚያው እንኳ ተንሳፎ አልራቀም።
ጆርጅ ሙለርን ታማኝ ብቻ ሳይሆን ዘወትር አመስጋኝም አድርጎ የጠበቀው ቸርነትና ምሕረት አልነበረምን! የእምነትና የጸሎት አስፈላጊነት የተሰማውን ያህል፣ በደስታና በምስጋና የመትረፍረፍ ግዴታውና መብቱም ዘወትር ይሰማው ነበር። አንዳንዶች ከእንዲህ ያሉ የጸሎት መልሶች ተሞክሮ በኋላ፣ የእንዲህ ያሉ ጣልቃ ገብነቶች አዲስነት በተደጋጋሚነታቸው ውስጥ ስለሚጠፋ፣ ሰው በእነርሱ እየቀነሰ እየቀነሰ ይነካል ብለው ያስቡ ይሆናል። ነገር ግን እንዲህ አልነበረም። በጁን 1853፣ በከባድ የችግር ጊዜ፣ ጌታ በአንድ ጊዜ ሦስት መቶ ፓውንድ በላከ ጊዜ፣ በእግዚአብሔር ያገኘውን የድል ደስታ መቈጣጠር አቃተው። ልቡም ዓይኖቹም እየፈሰሱ፣ አፉ በሳቅ ድምፁም በዝማሬ ተሞልቶ፣ ለሚያገለግለው ታማኝ ጌታ ራሱን እንደ ገና እየሰጠ በክፍሉ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ወዲያና ወዲህ ተመላለሰ። የእግዚአብሔር በረከቶች ለእርሱ ሁልጊዜ አዲስና ትኩስ ነበሩ። የጸሎት መልሶች የአዲስነት ውበታቸውን ፈጽሞ አላጡም፤ ከእግዚአብሔር አትክልት ቦታዎች በየሰዓቱ ትኩስ ሆነው እንደሚቀጠፉ አበቦች ውበታቸውንና ሰማያዊ መዓዛቸውን አንዳች ሳያጡ ፈጽሞ አልጠወለጉም።
መልሶች እንደ በረዶ ቅንጣት በፍጥነትና በብዛት የሚመጡ በመሰሉ ጊዜም ሆነ፣ ሰማያት የተዘጉ መስለው እምነት በትዕግሥት ለረጅም ጊዜ መጠበቅ ባስፈለገው ጊዜ፣ የጸሎት ትጋትና ትዕግሥት ጽናታቸውን እንዲያላሉ ፈጽሞ ያልፈቀደው ምንኛ ያለ ቸርነትና ምሕረት ነበር! እያንዳንዱ ቀን በጸሎት ለመጽናት አዳዲስ ጥያቄዎችን አመጣ። እንዲያውም፣ አቶ ሙለር እንደሚመሰክረው፣ በኋለኞቹና በቀደሙት ዘመናት መካከል የነበረው ብቸኛ ልዩነት ሥራው በሰፋ መጠን ችግሮቹም መብዛታቸው ነበር። ነገር ግን ይህ የሚጠበቅ እንደ ነበረ ይጨምራል፤ ጌታ እምነትን የሚሰጠው ለራሱ ስም ክብርና እምነቱ ላለው ሰው ጥቅም እምነቱን ለመፈተን ዓላማ ነውና፤ መታመንም የድሉን ምሥጢር የሚማረው በእነዚህ ፈተናዎች ነው።
ቸርነትና ምሕረት ይህን የእግዚአብሔር አገልጋይ የመሩት ብቻ ሳይሆኑ ጠበቁትም። የእግዚአብሔር አጃቢዎች ዘወትር በላዩ የነበረ የመከላከያ ጋሻ ይዘው ነበር። በሺዎች ከሚቆጠሩ ከማይታዩ አደጋዎች መካከል አልፎ አልፎ አንዳንድ አደጋ ይታወቅ ነበር፤ ብዙውን ጊዜ ግን የሚታወቀው ካለፈ በኋላ ነበር። ለምሳሌ በ1847 በኬስዊክ እያገለገለ ሳለ፣ በዚያው ቤት ያርፍ የነበረ አንድ ሰው በአእምሮ ሕመም ተይዞ ራሱን በጥይት ገደለ። ይህ ሰው አቶ ሙለር ሕይወቱን ሊያጠፋ እንዳሰበ ያስብ እንደ ነበረ በኋላ ታወቀ፤ በዚህ የእብደት ጥቃት ወቅት አቶ ሙለርን አግኝቶት ቢሆን ኖሮ፣ በሰውነቱ ይዞት በሚዞረው በተጐረሰ ሽጉጥ ምናልባት ተኵሶ ይገድለው ነበር።
የዚህ የእግዚአብሔር ሰው መንገድ አንዳንድ ጊዜ በጥልቅ የመከራ ውኆች ውስጥ ያልፍ ነበር፤ ቸርነትና ምሕረት ግን አሁንም ተከትለው ደግፈው ያዙት። በ1852 መጸው፣ የሚወደው የሚስቱ ወንድም አቶ ኤ. ኤን. ግሮቭስ እጅግ ታሞ ከምሥራቅ ሕንድ ተመለሰ፤ በሚቀጥለውም ዓመት በሜይ፣ ለእግዚአብሔር የተባረከ ምስክርነት ከሰጠ በኋላ፣ በአቶ ሙለር ቤት አንቀላፋ። አቶ ሙለር በ1829 በድካሙ መጀመሪያ ላይ በጸጋ ለእርሱ ብዙ ባለ ዕዳ ነበር። አቶ ግሮቭስ በዓመት አሥራ አምስት መቶ ፓውንድ ገደማ የሚያስገኝለትን ትርፋማ ሙያ ትቶ፣ ምንም የሚታይ ድጋፍ ሳይኖረው ወይም ከማንኛውም የሚስዮን ማኅበር ጋር ግንኙነት ሳይኖረው፣ በዚያ ሩቅ መስክ የሚስዮን ሥራ ለመሥራት ከሚስቱና ከልጆቹ ጋር ወደ ባግዳድ በሄደ ጊዜ፣ በእርሱ ምሳሌ የአቶ ሙለር እምነት ተነቃቅቶና ተረድቶ ነበር። በእነዚህ ሰዎች መካከል የነበረው ትስስር እጅግ የቀረበና ርኅሩኅ ነበር፤ የዚህ የሚስቱ ወንድም ሞትም ብርቱ ሐዘን አመጣ።
በዚያው ዓመት በጁላይ፣ አቶ ሙለርና ወይዘሮ ሙለር ከዚህም የከፋ ፈተና አለፉ። የተወደደችው ልጃቸውና ብቸኛ ልጃቸው ሊድያ፣—በ1832 የተወለደችው፣ በ1846 ዳግመኛ የተወለደችው፣ በዚያን ጊዜም ሃያ ዓመት የሆናትና በዋጋ የማትተመን ሀብት የነበረችው፣—በጁን መጨረሻ ታመመች፤ ሕመሙም ወደ አደገኛ ታይፎይድ ተለውጦ ከሁለት ሳምንት በኋላ እስከ ሞት ደጅ አደረሳት። እነዚህ ወላጆች ያለ ልጅ የመቅረትን ዕድል መጋፈጥ ነበረባቸው። ነገር ግን እምነት አሸነፈ፤ ጸሎትም ሠመረ። የሚወዷት ሊድያ ለብዙ ዓመታት ለእነርሱና ለወደፊቱ ባሏ ብቻ ሳይሆን በሰፊ የተጽዕኖ ክበብ ውስጥ ላሉ ለብዙ ሌሎችም ከቃል በላይ በረከት እንድትሆን ተረፈች። አቶ ሙለር በዚህ ፈተና ውስጥ የእግዚአብሔርን ቸርነትና ምሕረት የሚያሳይ ልዩ ማስረጃ አገኘ፤ ይህንንም በምስጋና መዝግቦታል፤ ይኸውም በጸጋ ማደጉ ነው፤ ይህ ዕድገት እንዲህ ያለ ጥፋት በፊቱ የተደቀነ መስሎ ሳለ እንኳ ለአብ ፈቃድ ሙሉ በሙሉና በደስታ በመገዛቱ፣ እግዚአብሔርም «ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ» እንደሚያደርግ ያለው መታመን ባለመናወጡ ታየ። ይህን የእርጋታ ተሞክሮ ከሃያ አንድ ዓመት በፊት፣ በኦገስት 1831፣ ተመሳሳይ ፈተና ሲገጥመው ከነበረው ከተናጋው ሰላምና ከአጕረምራሚው መንፈስ ጋር ከማነጻጸር ሊቆጠብ አልቻለም። ማግኔት በብረት ብናኝ መካከል እንደሚሆን፣ አመስጋኝ ልብ ምሕረቶችን አግኝቶ ከሐዘንና ከመከራ ጥቁር አቧራ ውስጥ እንዴት ለቅሞ ያወጣቸዋል!
የአቶ ሙለር «ትረካ» ሁለተኛው ጥራዝ የሚደመደመው፣ ተአምር አድራጊ ነኝ የሚል ከፍተኛ ማዕረግን ሁሉ እንደ ድፍረት የተሞላበት ትዕቢትና ማስመሰል በይፋ በሚያስተባብልበትና፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የተስፋ ቃሎች ላይ የተመሠረተና ቀላል በሆነው የእምነትና የጸሎት መንገድ የተገነባ ማንኛውም ሥራ እንደ ልዩ ክስተት ወይም እንደ አክራሪነት መቈጠሩ እንዳሳዘነው በሚመዘግብበት አንቀጽ ነው።
የሥራውን ስኬት ለማስረዳት የሚቀርቡት የተለመዱ መንገዶች በሚያሳዝን ሁኔታ የማያምኑ ባይሆኑ ኖሮ እጅግ የሚያስቁና የሚያዝናኑ በሆኑ ነበር። ስለ እምነት ልምምድም ሆነ ስለ እግዚአብሔር ታማኝነት ተሞክሮ ጥቂት ወይም ምንም የማያውቁ ሰዎች፣ ስለ ሥራው እግዚአብሔርን እጅግ የሚያዋርዱ ማብራሪያዎችን አቀረቡ። አንዳንዶች «አቶ ሙለር የውጭ አገር ሰው ነው፤ ዘዴዎቹም ትኵረት እስኪስቡ ድረስ አዲስ ናቸው» አሉ። ሌሎች «ዓመታዊ ሪፖርቶቹ ገንዘቡን ያመጣሉ» ብለው አሰቡ፤ ወይም «ምሥጢራዊ ግምጃ ቤት» እንዳለው ጠቈሙ። እርሱም በእርጋታ እንዲህ ሲል መለሰ፤ የውጭ አገር ሰው መሆኑ መታመንን ከመሳብ ይልቅ የማራቅ ዕድሉ ይበልጣል፤ አዲስነቱም ከሃያ ዓመታት በላይ ካለፈ በኋላ ብዙም ሊጠቅመው አይችልም፤ ሪፖርቶችን የሚያወጡ ሌሎች ተቋማት ከችግርና ከዕዳ ሁልጊዜ አያመልጡም፤ ሊደርስበት ይችላል ተብሎ ስለ ታሰበው ምሥጢራዊ ግምጃ ቤት ግን በዚያ ግምት ውስጥ ተቃዋሚዎቹ ከሚያውቁት በላይ እውነት እንዳለ ለመመስከር ተገደደ። በእርግጥም የማያልቅ ግምጃ ቤት ነበረው—ለዘላለም በማይለወጥ ታማኝ አምላክ የተስፋ ቃሎች ውስጥ—በ1856 ቀደም ሲል ለሃያ ሁለት ዓመታት ከዚያ ሲቀዳ እንደ ቆየና በአጠቃላይ ከአንድ መቶ አሥራ ሦስት ሺህ ፓውንድ በላይ እንደ ቀዳ ይናገራል። ስለ ሪፖርቶቹም፣ በሕይወቱ ዘመን ሁሉ ለሕዝብ ስለ አንድ ችግር ያስታወቀው አንድ ጊዜ ብቻ እንደ ሆነ፣ ያም የተጨማሪ ወላጅ አልባ ሕፃናት ፍላጎት እንደ ነበረ ልብ ማለት ይጠቅማል—በጌታ ስም የሚንከባከባቸው ተጨማሪ ልጆች—ይህም ገቢውን ሳይሆን ወጪውን ለመጨመር የፈለገበት ብቸኛና ያልተለመደ የማስታወቂያ ሁኔታ ነበር—ሕዝቡ ችግረኞችን ለመደገፍ እንዲረዳው ሳይሆን የሚያወጣበትን ምክንያት እንዲያበዛለት የጠየቀበት!
የማያምነው ዓለም ሊያስበው በሚችለው በእንዲህ ያሉ የገቢ ምንጮች ላይ ከመደገፍ እጅግ የራቀ ስለ ነበረ፣ ለእምነቱና ለእግዚአብሔር ኃይል ዕድል ያገኘው እንዲህ ያሉት መስመሮች ሁሉ በደረቁ ጊዜ ነበር። የሚታየው ግምጃ ብዙ ጊዜ እጅግ ትንሽ ከመሆኑ የተነሣ እስከ ምንም ይደርስ ነበር፤ የማይታየው ግምጃ ግን በክብር ያለው የእግዚአብሔር ባለ ጠግነት ነበር፤ ያለ ገደብም ሊቀዳ ይችል ነበር። ብቻውን የተመለከተው ወደዚህ ነበር፤ በዚህም ፈጽሞ ሊደርቅ የማይችል የአቅርቦት ወንዝ እንዳለው ተሰማው።*
* አባሪ ሸ።
የወላጅ አልባ ሕፃናቱ ሥራ ለአቶ ሙለር ይበልጥ እየገባበት በሄደ ቍጥር እያደጉ የሄዱ ብዙ መስሕቦች ነበሩት። ዋናው ተስፋው ለእነዚህ ልጆች የመንፈሳዊ ጤንነት መሣሪያ መሆን ቢሆንም፣ እግዚአብሔር እነዚህን ቤቶች ለሥጋዊ ደኅንነታቸውም፣ በጥቂት ባልሆኑ ሁኔታዎችም ደካማና የታመመ ሰውነታቸውን ፈጽሞ ለማደስ እንዴት እንደ ተጠቀመባቸው የማየት ደስታ አገኘ። አብዛኞቹ ወላጅ አልባ የሆኑት ያ ታላቅ አጥፊ በሆነው በሳንባ ነቀርሳ ምክንያት እንደ ነበረ ማስታወስ ያስፈልጋል። ልጆች ብዙ ጊዜ ወደ ወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቤቶች የሚመጡት የተበከለ ደም መርዝ ሰውነታቸውን ሁሉ አዳርሶ፣ ለበሽታ የተጋለጡ ሆነው፣ አንዳንድ ጊዜም ተገቢ ምግብም ሆነ የሕክምና እንክብካቤ ስላላገኙ ከስተውና በግማሽ ተርበው ነበር።
ለምሳሌ በ1855 ጸደይ፣ ዕድሜያቸው ከአምስት እስከ ዘጠኝ ዓመት የሆነ፣ ከአንድ ቤተሰብ የተገኙ አራት ልጆች ወደ ወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቤት ገቡ፤ ሁሉም በእንክብካቤና በምግብ እጦት በአሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነበሩ። እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች ተቋሙን ወደ ሆስፒታል የመለወጥና ከመጠን ያለፈ እንክብካቤና ጊዜ የመውሰድ ዝንባሌ ስለ ነበራቸው፣ ጨርሶ ሊቀበሏቸው ይገባ እንደ ሆነ ከባድ ጥያቄ ነበር። ነገር ግን እነርሱን መመለስ ከሞላ ጎደል ኢሰብአዊ፣ በእርግጥም ርኅራኄ የጐደለው መስሎ ታየ። ስለዚህ በእግዚአብሔር በመታመን ተቀበሏቸው፤ በወላጅ ፍቅርም ተንከባከቧቸው። ከጥቂት ሳምንታት በኋላ የጤናቸው መሻሻል እጅግ ፈጣን ስለ ነበረ እነዚህ ልጆች በአካል የማይታወቁ ሆኑ፤ በእግዚአብሔርም በረከት የሚቈፈሩ መቃብሮች ምናልባት በአራት ቀነሱ።
ይሁን እንጂ ከወላጅ አልባ ሕፃናቱ የሥነ ምግባርና የመንፈሳዊ ሁኔታ የተነሣ የሚመጡት ፈተናዎች ከሕመምና ከድካም ከሚመጡት ይልቅ የበረቱ ነበሩ። ልጆች ሊታረሙ የማይችሉ ክፉዎች ሆነው ሲገኙ ሌሎችን እንዳያበላሹ ይባረሩ ነበር፤ ተቋሙ የማረሚያ ቤት አልነበረምና፣ ልክ ሆስፒታል እንዳልነበረ። በ1849 ዕድሜው ከስምንት ዓመት ያነሰ አንድ ልጅ የሌሎችን ልጆች ንብረት ይዞ ሁለት ጊዜ ስለ ኰበለለና በልጅነት ወንጀሎቹ ስለ ተመካ፣ ሥር የሰደደ ውሸታምና ሌባ ሆኖ መሰናበት ነበረበት። ነገር ግን በእርሱ ጉዳይ እንኳ የተደረገው ትዕግሥት በሚያስደንቅ ሁኔታ እግዚአብሔርን የሚመስል ነበር፤ ከአምስት ዓመት በላይ በግል ምክርና በጸሎት፣ በሌሎችም የማቅኛ መንገዶች ሁሉ ሲያዝ ቆይቶ ነበርና፤ መባረር የመጨረሻ አማራጭ በሆነ ጊዜም፣ ይህ እርምጃ ቢቻል ለእርሱ መድኃኒት፣ ለሌሎችም ማስጠንቀቂያ ሆኖ ድርብ በረከት እንዲሆን፣ በሌሎቹ ሁሉ ፊት በከበረ ሥርዓትና በጸሎት ከወላጅ አልባ ሕፃናቱ ቤት ተሰናበተ፤ ያኔም እንኳ ይህ በኃጢአት የተለማመደ ታዳጊ በመባረሩ ጊዜ በፍቅር ልመና ተሸኘ።
በኖቬምበር 1857 መጨረሻ ገደማ፣ በቍጥር 1 ቤት የማሞቂያ መሣሪያ ቦይለር ውስጥ የተከሰተ ከባድ ፍሳሽ ወዲያውኑ ጥገና እንደሚያስፈልገው ታወቀ፤ ቦይለሮቹም በጡብ የተሸፈኑ ስለ ነበሩና አዲስ ቦይለር ሊያስፈልግ ስለሚችል እንዲህ ያለው ጥገና ጊዜ መውሰዱ አይቀርም ነበር። እስከዚያው ድረስ አንዳንዶቹ እጅግ ትንንሽና ለስላሳ የሆኑ ሦስት መቶ ልጆች እንዴት ሊሞቁ ይችላሉ? ለጊዜው የጋዝ ምድጃዎች ቢተከሉ እንኳ የተበከለውን አየር የሚያስወጡ የጭስ መውጫዎች ያስፈልጉ ነበር፤ የብርድን አደጋ ለመከላከል መቶ ፓውንድ ቢወጣ እንኳ በጥገናው ወቅት ምንም የማሞቂያ መንገድ አልነበረም። አቶ ሙለር እንደ ገና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ዞረ፤ በእርሱም ታምኖ ጥገናው እንዲጀመር ወሰነ። እሳቱ መጥፋት ከነበረበት ቀን አንድ ቀን ገደማ አስቀድሞ ቀዝቃዛ የሰሜን ነፋስ መንፈስ ጀመረ። ሥራው ከዚያ በላይ ሊዘገይ አይችልም ነበር፤ ሆኖም ለወቅቱ ያለ ጊዜው የቀዘቀዘው አየር እነዚህን በመቶዎች የሚቆጠሩ ልጆች ለጎጂ ብርድ እንደሚያጋልጥ አሰጋ። ጌታ በድፍረት ተለመነ፦ «ጌታ ሆይ፥ እነዚህ የአንተ ወላጅ አልባ ልጆች ናቸው፤ ይህን የሰሜን ነፋስ ወደ ደቡብ ነፋስ ትለውጥ ዘንድ፣ ሥራውም ፈጥኖ እንዲጠናቀቅ ለሠራተኞቹ የመሥራት ልብ ትሰጥ ዘንድ ፈቃድህ ይሁን።»
ጥገናው በትክክል ከመጀመሩ በፊት በነበረው ምሽት ቀዝቃዛው ነፋስ ገና እየነፈሰ ነበር፤ ነገር ግን በዚያ ቀን የደቡብ ነፋስ ነፈሰ፤ አየሩም እሳት እስከማያስፈልግ ድረስ ለዘብተኛ ሆነ! ይህም ብቻ ሳይሆን፣ አቶ ሙለር ጥገናው በምንም መንገድ ሊፋጠን ይችል እንደ ሆነ ለማየት ከሥራው ተቈጣጣሪ ጋር ወደ ምድር ቤቱ በገባ ጊዜ፣ ተቈጣጣሪው ሠራተኞቹ እየሰሙ «ዛሬ ምሽት እስከ ሌሊት ይሠራሉ፤ ነገም በጣም ማልደው ይመጣሉ» ሲል ሰማው። «ጌታዬ፣ ይልቁንስ» ብለው መለሱ፤ «ሌሊቱን ሙሉ እንሥራ።» በዚህም በሠላሳ ሰዓት ገደማ ውስጥ በቦይለሩ ያለውን ውኃ ለማሞቅ እሳቱ እንደ ገና ይነድ ነበር፤ መሣሪያው እንደ ገና እስኪስተካከልም ድረስ ያ ርኅሩኅ ለስላሳ የደቡብ ነፋስ መንፈሱን ቀጠለ። ቸርነትና ምሕረት ትሑቱን የጌታ አገልጋይ ይከተሉት ነበር፤ ይህም በልዩ ፈተናና ችግር ቀውሶች ይበልጥ ጎልቶ ታየ።
እያንዳንዱ አዲስ ችግር አዲስ ጸሎትን አስነሣ፣ አዲስ እምነትንም ቀሰቀሰ። በ1862 ብዙ ወንዶች ልጆች የሙያ ተለማማጅ ለመሆን ተዘጋጅተው፣ የሚፈለገው ዓይነት ማመልከቻ ባልመጣ ጊዜ፣ ማስታወቂያ ማውጣት ለክፍያው ሲሉ ተለማማጆችን ከሚፈልጉ አሠሪዎች ማመልከቻ ሊያመጣ ስለሚችል ብቸኛው መፍትሔ ጸሎት ነበር። ነገር ግን ከአሥራ ስምንቱ ልጆች እያንዳንዱ ሥራው ተስማሚ ለሆነና ልጁን በገዛ ቤተሰቡ ውስጥ ለሚቀበል ለአንድ ክርስቲያን አሠሪ በአግባቡ በውል ተሰጠ።
በዚያው ጊዜ ገደማ ከመሬት በታች አሥራ አንድ ጫማ ገደማ ጥልቀት ከሚያልፉት የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎች አንዱ ተዘጋ። ሦስት ጉድጓዶች ተቈፍረው በቱቦው ላይ ሦስት ስፍራዎች በከንቱ ከተከፈቱ በኋላ፣ በአራተኛው ጊዜ ሠራተኞቹ መዘጋቱ ወዳለበት ትክክለኛ ስፍራ እንዲመሩ ጸሎት ቀረበ—ልመናውም ቃል በቃል ተመለሰ።
ከሜይ 26 ቀን 1864 ጀምሮ እስከ 1865 ተመሳሳይ ቀን ድረስ ባለው ዓመት ውስጥ፣ ለጸሎት መልስ ሆነው የተገኙ ሦስት ጉልህ የመዳን ሁኔታዎች በተለይ ተመዝግበዋል፤ እነዚህም ቢያንስ ሳይጠቀሱ ሊታለፉ አይገባም።
የመጀመሪያው፣ በ1864 የበጋ ወራት በነበረው ታላቅ ድርቅ፣ በሦስቱ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶች ያሉት አሥራ አምስቱ ትላልቅ የውኃ ማጠራቀሚያዎች ባዶ በሆኑበት፣ ዘጠኙ ጥልቅ ጕድጓዶችና ከዚያ በፊት ደርቆ የማያውቀው መልካሙ ምንጭ እንኳ ከሞላ ጎደል ሁሉም በደረቁበት ጊዜ ነበር። በየቀኑ ሁለት ወይም ሦስት ሺህ ጋሎን ውኃ ያስፈልግ ነበር፤ ለዝናብ አምላክም በየዕለቱ ጸሎት ይቀርብ ነበር። ከላይ የሚመጣውን አቅርቦት መከልከል ደስ ባሰኘው ጊዜ እግዚአብሔር እንዴት እንደ አዘጋጀ ተመልከቱ! በአቅራቢያው ያለ አንድ ገበሬ ከትላልቅ ጕድጓዶቹ ከሚያስፈልገው ውኃ ግማሹን ያህል አቀረበ፤ የቀረውም በአሽሊ ዳውን ግማሽ በደረቁ ጕድጓዶች ተሟላ፤ እርሱ ከዚያ በላይ ውኃ መስጠት ባልቻለ ጊዜ፣ አንድ ቀን እንኳ ሳይቋረጥ፣ ሌላ ገበሬ በእርሻዎቹ መካከል ከሚያልፍ ጅረት ውኃ ለማቅረብ ቃል ገባ፤ በዚህም ዝናቡ የውኃ ማጠራቀሚያዎቹንና ጕድጓዶቹን እስኪሞላ ድረስ ውኃ በብዛት ነበረ።*
* ከሃያ ዓመት ገደማ በኋላ የብሪስቶል የውኃ ሥራዎች ኩባንያ ቱቦዎችን ዘረጋ፤ በዚህም ቋሚና የማይቋረጥ አቅርቦት ተገኘ።
ሁለተኛው፣ ለሦስት ዓመታት የቀይ ትኩሳትና የታይፈስ ትኩሳት እንዲሁም ፈንጣጣ በብሪስቶልና በአካባቢዋ ተስፋፍተው ወላጅ አልባ ሕፃናቱን ባሰጉ ጊዜ፣ የዝናብ ብቻ ሳይሆን የጤናም አምላክ ለሆነው እንደ ገና ጸሎት ቀረበ። በዚያ ጊዜ ሁሉ አንድም የቀይ ትኩሳት ወይም የታይፈስ ሕመም አልተከሰተም፤ ፈንጣጣ ግን ከወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶች ወደ ትንሹ እንዲገባ ተፈቀደ። ጸሎት አሁንም ብቸኛው መጠጊያ ነበር። በሽታው ወደ ሌሎቹ ቤቶች ተዛመተ፤ በአንድ ወቅትም አሥራ አምስት ልጆች በእርሱ ታመው ነበር። ሆኖም ሕመሞቹ በምሕረት ቀላል ነበሩ፤ ጌታም ወረርሽኙ ከዚያ በላይ እንዳይዛመት ተለመነ። ሌላ አንድም ልጅ አልተያዘም፤ ከዘጠኝ ወራትም በኋላ በሽታው ፈጽሞ በጠፋ ጊዜ በእርሱ የሞተ አንድም ልጅ አልነበረም፤ ከመምህራን ወይም ከአዋቂዎች መካከልም የታመመው አንድ ብቻ ነበር፤ ያም እጅግ ቀላል ነበር። በሽታው በኋላ በ1872 እንደ ተስፋፋው ያኔ ተስፋፍቶ ቢሆን ኖሮ፣ በእነዚህ የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶች በሚኖሩት አሥራ ሁለት መቶ ሰዎች መካከል ምን ያህል ጥፋት ባደረሰ ነበር!
ሦስተኛ፣ በጃንዋሪ 1865 ብርቱ አውሎ ነፋሳት ብሪስቶልንና አካባቢዋን መቱ። የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶቹ ጣሪያዎች ቢያንስ በሃያ ቦታዎች ተገልጠው እስኪከፈቱ ድረስ ተጐዱ፤ ትልልቅ የመስታወት ሰሌዳዎችም ተሰበሩ። ዕለቱ ቅዳሜ ነበር፤ እስከ ሰኞም ድረስ መስታወት ገጣሚም ሆነ ጣሪያ ሠሪ ሊገኝ አልቻለም። ስለዚህ በዚያ መካከል ባለው ጊዜ ለአደጋ የተጋለጠውን ንብረት እንዲጠብቅ የነፋስና የአየር ጠባይ ጌታ ተለመነ። ነፋሱ ጸጥ አለ፤ ዝናቡም እስከ ረቡዕ እኩለ ቀን ድረስ ተከለከለ፤ በዚያን ጊዜ ጥገናው ሊጠናቀቅ ተቃርቦ ነበር፤ ነገር ግን ኃይለኛ ዝናብ ጣሪያ ሠሪዎቹን ከጣሪያው ላይ አባረራቸው። አንድ ክፍት ቦታ ገና ሳይጠገን ቀርቶ ነበር፤ ብዙ ጉዳትም ያሰጋ ነበር፤ ነገር ግን ለጸሎት መልስ ሆኖ ዝናቡ ቆመ፤ ሥራውም እንደ ገና ቀጠለ። ያ የመጨረሻው ክፍት ቦታ ሳይጠገን በቆየበት ጊዜ ምንም ጉዳት አልደረሰም፤ ምክንያቱም ያ ክፍት ቦታ ሕንፃውን በደቡብ በኩል፣ ክፍት አድርጎት ነበር፤ ዝናቡ ግን የመጣው ከሰሜን ነበር።
አቶ ሙለር እነዚህን ሁኔታዎች እንደ ልማዱ በዝርዝር ይመዘግባቸዋል፤ ይህንም የሚያደርገው ለሕያው እግዚአብሔርና በቅርብና ያለማቋረጥ ይከተሉት ለነበሩት ቸርነትና ምሕረት የሚሰጠው ምስክርነት አካል አድርጎ ነው።
በቀጣዩ ዓመት፣ በ1865-6፣ በወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያው ውስጥ የቀይ ትኩሳት በሽታ ተከሠተ። በአጠቃላይ ሠላሳ ዘጠኝ ልጆች ታመሙ፤ ሁሉም ግን ዳኑ። ትክትክ ሳልም ደግሞ ታየ፤ ይሁን እንጂ በዚያ ወቅት በብሪስቶል በሽታው በጣም የተስፋፋ ብቻ ሳይሆን እጅግ አደገኛም የነበረ ቢሆንም፣ በሦስቱም ቤቶች ውስጥ የተያዙት አሥራ ሰባት ብቻ ነበሩ፤ የሞተችውም በተፈጥሮዋ ሳንባዋ ደካማ የነበረች አንዲት ትንሽ ልጅ ብቻ ነበረች።
ይሁን እንጂ በዚሁ ዓመት፣ ባለፈው ዓመት በወንዶቹ ልጆች መካከል እንደ ሠራ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ በሴቶቹ ልጆች መካከል በኃይል ሠራ፤ ከመቶ የሚበልጡትም መዳንን ከልብ አጥብቀው የሚፈልጉ ሆኑ፤ እንዲሁም በመከራ ውስጥ እንኳ መጽናናት በክርስቶስ በዛ። አቶ ሙለርና ባለቤቱ፣ ረዳቶቹም፣ እግዚአብሔር ይህን የመንፈሱን ሥራ እንዲያጠልቅና እንዲያሰፋ አሁን ተማጸኑት። በሜይ 1866 በተጠናቀቀው ዓመት መገባደጃ ላይ፣ ኤማ ባን የተባለች የአሥራ ሰባት ዓመት ወላጅ አልባ ልጃገረድ በሳንባ ነቀርሳ ተያዘች። ለአሥራ አራት ዓመታት በአቶ ሙለር እንክብካቤ ሥር የቆየች ብትሆንም፣ በዚህ አደገኛ ሕመም ውስጥ ሳለች እንኳ ግድ የለሽና ደንታ ቢስ ነበረች፤ ወደ ሞት በቀረበችም ጊዜ ሁኔታዋ እንደ ቀድሞው ተስፋ የሌለው ሆኖ ቀጠለ። ስለ እርሷ ያለማቋረጥ ይጸለይ ነበር፤ እግዚአብሔርም ድንገት ክርስቶስን አዳኟ አድርጎ ሊገልጥላት ወደደ። ወዲያውም በቀድሞው ግድ የለሽነት ፈንታ ታላቅ ራስን መጸየፍ፣ በቀድሞው የሕሊና ድንዛዜ ፈንታ የኃጢአት መናዘዝ፣ በቀድሞው ደንታ ቢስነትና ቅዝቃዜ ፈንታም በጌታ የማይነገር ደስታ ተተካ። ይህ መንፈሳዊ ተአምር ነበር — ይህች ልጃገረድ ድንገት ተለውጣ ስላለፈው ኃጢአቷ ጥልቅ መወቀስንና ለሌሎች ልባዊ አሳቢነትን የምታሳይ የእግዚአብሔር ምስክር ሆነች። የቀድሞው ግድ የለሽና ቸልተኛ ሁኔታዋ በሚገባ የታወቀ ስለ ነበር፣ መለወጧና በሞት አፋፍ ላይ ሳለች የተናገረቻቸው መልእክቶች ጌታ እስከዚያ ጊዜ ድረስ በወላጅ አልባ ሕፃናቱ መካከል ከተሠራው ሥራ ሁሉ እጅግ የሰፋውንና እግዚአብሔርን እጅግ ያከበረውን ሥራ የሠራባቸው መሣሪያዎች ሆኑ። በአንዱ ቤት ብቻ ሦስት መቶ ሃምሳ ልጆች በማመን ሰላምን እንዲፈልጉ ተመሩ።
በእነዚህ ድርጊቶች ውስጥ ፈቃደኛ የሆነ ተመልካች ሁሉ ሊያነብባቸው የሚችሉ ምን ያህል ትምህርቶች ተሰውረዋል — እንዲያውም በግልጽ ላዩ ላይ ተቀምጠዋል! ጸሎት ደንዳና ልብን እንኳ ሊሰብር ይችላል፤ በመጽሐፍ ቅዱስ እውነትና በቅዱስ ትምህርት የተሞላ ትውስታ፣ አንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ጸጋ ልብን ሲያለሰልስና አንደበትን ሲፈታ፣ በጸጋ ለግል ማደግም ሆነ ለሌሎች ሰፊ አገልግሎት ለመስጠት ለሚያስችል ብቃት ምንጭ ይሆናል። ሁላችንም በተግባር ልጆችን ስለ ማሠልጠን እጅግ ቸልተኞች፣ አዲስ የተለወጡትንም እጅግ የምንጠራጠር ነን። አቶ ሙለር ገና በዘጠኝ ወይም በአሥር ዓመት ለጋ ዕድሜያቸው ተለውጠው የመጀመሪያ እምነታቸውን እስከ መጨረሻው አጽንተው በጠበቁ ልጆች ላይ በታየው የእግዚአብሔር ጸጋ ድል ይበልጥ እየተደነቀ ሄደ።
እንደ እፍኝ እህል ከሰፊ መስክ የተለቀሙት እነዚህ እውነታዎችና ልምምዶች የተዘራውን ዘርና ከዚያ ዘር የታጨደውን መከር ምንነት ያሳያሉ።
ደግሞም በ1866 በእንግሊዝ ኮሌራ በተነሣ ጊዜ፣ ለልዩ ጸሎት መልስ ሆኖ በወላጅ አልባ ሕፃናት ቤቶቹ ውስጥ በዚህ በሽታ የተያዘ አንድም ሰው አልታወቀም፤ በዚያው በልግም ትክትክ ሳልና ኩፍኝ በተከሠቱ ጊዜ፣ ስምንት ልጆችን ትክትክ ሳል፣ ሁለት መቶ ስድሳ ሁለቱን ደግሞ ኩፍኝ ቢይዛቸውም፣ አንድም ልጅ አልሞተም፤ ከበሽታውም በኋላ የደከመ አልነበረም። ከሜይ 1866 እስከ ሜይ 1867 ድረስ በእንክብካቤ ሥር ከነበሩት ከአንድ ሺህ ሦስት መቶ የሚበልጡ ልጆች መካከል የሞቱት አሥራ አንድ ብቻ ነበሩ፤ ይህም ከአንድ በመቶ እጅግ ያነሰ ነው።
ከባድና ተላላፊ በሽታ ጨርሶ ወደ ወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያዎቹ መግባቱ የእግዚአብሔርን ታማኝነት በሚታየው ነገር ለሚመዝኑ ሰዎች እንግዳ ነገር ሊመስላቸው ይችላል፤ ነገር ግን ለእንደዚህ ያሉ ፈተናዎች የተሰጡት ካሳዎች ብዙ ነበሩ። በእነርሱ አማካይነት የልጆቹ ልብ ብዙ ጊዜ ወደ እግዚአብሔር መመለሱ ብቻ ሳይሆን፣ በተቋሙ ውስጥ የነበሩት ረዳቶች ልብም ይበልጥ ሩኅሩኅና ለስላሳ ሆነ፤ በአጠቃላይም የእግዚአብሔር ሕዝብ ልብ በተግባርና በሥርዓት እንዲረዱ ተነሣሣ። እግዚአብሔር እንደነዚህ ያሉትን መከራ የሚመስሉ ነገሮች ለሥራው «ማስታወቂያዎች» አድርጎ ይጠቀምባቸዋል፤ ስለ ተቋሙ ያልሰሙ ወይም የሰሙትም ነገር ብዙም ያልነካቸው ብዙ ሰዎች፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሕፃናት ለአንዳች ክፉና አደገኛ ወረርሽኝ ጥፋት በተጋለጡበት የወላጅ አልባ ሕፃናት ማሳደጊያ ጉዳይ ጥልቅ ትኩረት እንዲሰጡ ተመሩ።
አቶ ሙለር በ1865፣ ከሠላሳ አንድ ዓመታት በኋላ፣ እስከዚያ ድረስ ለጌታ የተሠራውን ሥራ መለስ ብሎ ሲመለከት፣ በዚያ ዘመን ሁሉ ሥራው በማርች 5 ቀን 1834 የተመሠረተባቸውን የመጀመሪያ መርሆዎች አጥብቆ እንዲይዝ እንደ ተቻለው በምስጋና ይመዘግባል። አንድም ጊዜ ዕዳ ውስጥ ገብቶ አያውቅም፤ ለተቋሙ ከሕያው እግዚአብሔር በቀር ሌላ ደጋፊ አልፈለገም፤ ለሥራው ንቁ ረዳቶችን በፈለገበት ሁሉ በአማኞችና በማያምኑ መካከል ያለውን የመለያ መስመር ጠብቋል።
ከመጀመሪያው አንሥቶ በድካሙ ሁሉ የነበረው ታላቅ ዓላማ፣ በሰው ላይ ምንም ሳይደገፉ በጸሎትና በእምነት ምን ሊደረግ እንደሚችል በማሳየት የእግዚአብሔርን ክብር መግለጥ ስለ ነበረ፣ የማያሻማ ምስክርነቱ ይህ ነው፦ «እስከዚህ ድረስ እግዚአብሔር ረዳን።» ለአምስት ዓመታት ያህል ከሞላ ጎደል በየዕለቱ በማያቋርጥ የእምነት ፈተና ውስጥ የነበሩ ቢሆንም፣ የእርሱን ታማኝነትም እንዲሁ ያለማቋረጥ ይለማመዱ ነበር። ሥራው ግዙፍ መጠን እስኪይዝ ድረስ በፍጥነት አደገ፤ የእግዚአብሔርም ርዳታ ከዕድገቱ ፍላጎቶችና ጥያቄዎች ሁሉ ጋር እኩል ይራመድ ነበር።
በጃንዋሪ 1866፣ ለሠላሳ ስድስት ዓመታት የአቶ ሙለር ውድ ወዳጅ፣ ከ1832 ጀምሮም በብሪስቶል የሥራ ባልደረባው የነበረው አቶ ሄንሪ ክሬክ ለሰባት ወራት ከታመመ በኋላ አንቀላፋ። እነዚህ ሁለት ወንድሞች በመጀመሪያ የተዋወቁት በዴቨንሻየር ነበር፤ ከዚያም በኋላ ትውውቃቸው በጋራ ድካምና ፈተና ዓመታት አልፎ በሰዎች መካከል እምብዛም ወደማይገኝ ፍቅር አደገ። ዕድሜያቸው ተቀራራቢ ነበር፤ አቶ ክሬክ በሞተ ጊዜ ሁለቱም ከስድሳ ዓመት ጥቂት አልፈው ነበር። በሕይወት የቀረው ሰው የዘላለምን ክንዶች ከበታቹ ባያውቅና ባይሰማ ኖሮ፣ ጉዳቱ በትዕግሥትና በእርጋታ ሊሸከሙት የማይቻል እጅግ ከባድ በሆነ ነበር። በአንድ በኩል ሲታይ ሊተካ የማይችል ጉዳት የነበረው ይህ ሐዘን እንኳ የእግዚአብሔር ፍቅር ሌላ ማረጋገጫ ብቻ እንደ ሆነ ታየ። ወደ ፊት ያለው ዕይታ ጨለማ፣ መንገዱም ባድማና አደገኛም ሊሆን ይችል ነበር፤ ነገር ግን ቸርነትና ምሕረት አሁንም በቅርብ ከኋላው ይከተሉት ነበር፤ በእያንዳንዱም አዲስ የአደጋ ወይም የችግር ስፍራ አስቸጋሪውን ቦታ እንዲሻገር ለመርዳትና በሌሊት ጊዜ መጽናናትንና ብርታትን ለመስጠት በአጠገቡ ይገኙ ነበር።