የብሪስቶሉ ጆርጅ ሙለር
የእምነት ፈተናዎችና የእምነት ረዳቶች

ምዕራፍ 13 · 16 ደቂቃ ንባብ · 20 ደቂቃ ማዳመጥ

የእምነት ፈተናዎችና የእምነት ረዳቶች

እግዚአብሔር የራሱ የሆነ ሒሳብ አለው፤ የእንጀራውና የዓሣው ተአምር ለዚህ ምስክር ነው። ጌታችን ደቀ መዛሙርቱን፦ «እናንተ የሚበሉትን ስጡአቸው» አላቸው፤ እነርሱ ሲያካፍሉ እርሱ ያችን ጥቂት ስንቅ አበዛት፤ እነርሱ ከእርስዋ ሲቀንሱ እርሱ ይጨምርባት ነበር፤ እነርሱ በማደል ሲያጎድሉአት እርሱ ደግሞ እንድትታደል አበዛት። ስለ ቅዱስ ሽርክና ሁሉ፣ በጋራ የተሸከሙት ሐዘን ይካፈላል፣ በጋራ የተቀበሉት ደስታ ግን ይባዛል ተብሎ በሚያምር ሁኔታ ተነግሮአል።

የጸሎቱ ክበብ እንዴት እንደ ሰፋ አስቀድመን አይተናል። የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ሥራ የመሠረተው ሰው በመጀመሪያ ተባባሪው እግዚአብሔር ብቻ ነበር፤ የራሱንም ሆነ የሥራውን ጕድለት ለእርሱ ብቻ ይነግር ነበር። ከጊዜ በኋላ ሚስቱን፣ አቶ ክሬክንና አንድ ወይም ሁለት ረዳቶችን ጨምሮ እጅግ ጥቂት ሰዎች የገንዘቡንና የስንቁን ሁኔታ እንዲያውቁ ተፈቀደላቸው። ከዚያም ቀጥሎ፣ በ1838 መጸው፣ በጌታ ሥራ ለተባበሩት ጓደኞቹ የልቡን ምሥጢር በር ይበልጥ መክፈት እንደሚገባው ይሰማው ጀመረ። በድካሙ የተካፈሉት በጸሎቱም፣ ስለዚህም ጸሎት ሊያሟላው የሚገባውን ፍላጎት በማወቅም ሊካፈሉ ይገባቸው ነበር፤ አለዚያ በእምነቱ፣ በሥራውና በዋጋው እንዴት ሙሉ ተካፋዮች ሊሆኑ ይችላሉ? ወይስ ደግሞ በጸሎት መልስ የእግዚአብሔርን መገኘትና ኃይል በሙላት እንዴት ሊያረጋግጡ፣ እንዲህ ያሉ መልሶች የሚያነሣሡትን የጌታን ደስታ እንዴት ሊያውቁ፣ ወይም እነዚህ መልሶች ስለሚገልጡት መታደግ እንዴት ሊያመሰግኑት ይችላሉ? ለእግዚአብሔር ታላቅ ክብር፣ የችግሩን ጥልቀትና እግዚአብሔር ያወጣቸውን የጕድለት ጽንፍ ሊያውቁ፣ ከዚያም ክብርንና ምስጋናን ሁሉ ለስሙ ሊሰጡ እንደሚገባቸው ግልጽ መስሎ ታየ።

ስለዚህ አቶ ሙለር በሥራው አመራር ከእርሱ ጋር የተቈራኙትን የተወደዱ ወንድሞችንና እኅቶችን ሁሉ በአንድነት ጠርቶ ምንም ሳይደብቅ ጉዳዩን በሙላት አስረዳቸው። ያሉበትን ጭንቀት አሳያቸው፤ ርዳታ በቅርብ እንዳለ የራሱን መተማመን እያረጋገጠላቸውም እንዲጽናኑ አደፋፈራቸው፤ ከዚያም ከራሱና ቀደም ብሎ ከነበረው ከትንሹ የጸሎት ክበብ ጋር አንድ አድርጎ ወደ ይሖዋ ይርኤ በልመና አቀረባቸው።

እንዲህ የተወሰደው እርምጃ ለሚመለከታቸው ሁሉ ቀላል ያልሆነ አስፈላጊነት ነበረው። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ቀንና ሌሊት ለእግዚአብሔር ዕረፍት በማይሰጡት የአማላጆች ቡድን ላይ ቍጥራቸው ብዙ የሆነ የሚጸልዩ አማኞች ተጨመሩ። አቶ ሙለር ሥራው ስለ ደረሰበት ጭንቀት ምንም ሐቅ ባይሸሽግም፣ ለጌታ ሥራ አመራር የማይለወጡ ሕጎች ሆነው አልፎ አልፎ የሚደጋገሙ አንዳንድ መመሪያዎችን አስቀመጠ። ለምሳሌ፣ ችግሩ የቱንም ያህል ቢከፋ፣ የሚከፈልበት ገንዘብ በእጅ ያልተገኘለት ምንም ነገር መገዛት አልነበረበትም፤ ሆኖም ልጆቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንዳያጡ ማድረግም እንዲሁ የጸና መመሪያ መሆን ነበረበት፤ ምክንያቱም በስም ብቻ ቤት በሆነና በእውነት ግን በረሀብ ወይም በዕራቁትነት በሚሠቃዩበት ስፍራ ከሚቀመጡ፣ ሥራው ቢቆምና ወላጅ አልባዎቹ ቢሰናበቱ ይሻል ነበር።

ደግሞም ለርዳታ እንደ ቀረበ ልመና እንዳይቈጠር፣ ስላለው ችግር ለውጭ ሰዎች ምንም ነገር ፈጽሞ መገለጥ አልነበረበትም፤ መጠጊያው ሕያው እግዚአብሔር ብቻ መሆን ነበረበት። በብሪስቶል የተመሠረቱት ተቋማት ዋነኛ ዓላማ የእግዚአብሔርን ታማኝነትና በተስፋ ቃሎቹ ብቻ መታመን ፍጹም አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ እንደ ሆነ ረዳቶቹ ብዙ ጊዜ ይታሰብላቸው ነበር፤ ስለዚህ ለእርሱ ያላቸው ቅንዓት ርዳታን ከሰው የመጠበቅን ዝንባሌ ሁሉ ሊገታ ይገባ ነበር። ከዚህም በላይ የራሳቸው አለማመንና አለመታዘዝ በጸሎት ያላቸውን ኃይል ወይም ለጋራ ልመና በመካከላቸው የሚያስፈልገውን ስምምነት አደጋ ላይ እንዳይጥል፣ በየዕለቱና በየሰዓቱ ከእግዚአብሔር ጋር በኅብረት እንዲኖሩ በብርቱ ተለመኑ። አንድ የማይስማማ ድምፅ የኅብረት ጸሎትን የተዋሐደ ዜማ ሊያበላሽ፣ በዚያው መጠንም እንዲህ ያለው ጸሎት በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዳያገኝ ሊያሰናክል ይችላል።

እንዲህ ተረድተውና ተመክረው፣ እነዚህ ራሳቸውን የሰጡ የሥራ ባልደረቦች ከተወደደው የወላጅ አልባ ሕፃናት ሥራ መሥራች ጋር ሆነው ቀውሱን በማስተዋል ተጋፈጡት። ገንዘብ ባልነበረ ጊዜ በሰው ላይ መደገፍም ሆነ ዕዳ መግባት የማይገባ ከሆነ፣ ሆኖም ምንም ጕድለት እንዲኖር የማይፈቀድ ከሆነ፣ ብቸኛው መጠጊያ ወይም መፍትሔ የማይታየውን አምላክ በትዕግሥት መጠበቅ እንደ ሆነ ግልጽ ነው፤ ስለዚህ በእነዚህ ጭንቀቶችና በተከታዩ ቀውስ ሁሉ ወደ እርሱ ብቻ ሄዱ። ወላጅ አልባዎቹ ራሳቸው ስላለው ችግር ፈጽሞ አልተነገራቸውም፤ እንዴት እንደ ሆነ ባያውቁም ፍላጎታቸው ሁልጊዜ ተሟላ። የዱቄቱ ማድጋ ባዶ ሊሆን ይችል ነበር፤ ነገር ግን ሲያስፈልግ ሁልጊዜ አንድ እፍኝ ይገኝ ነበር፤ የዘይቱም ማሰሮ እፍኙን ዱቄት ለማርጠብ ጥቂት ጠብታዎች እስከማይቀሩበት ድረስ ፈጽሞ አልተሟጠጠም። ራብና ድርቅ የብሪስቶልን የወላጅ አልባ ሕፃናት ቤት ፈጽሞ አልደረሱበትም፤ ስንቁ በዝግታና ለአንድ ቀን ብቻ የሚበቃ ሆኖ ሊመጣ ይችል ነበር፤ ነገር ግን ችግሩ አጣዳፊ በሆነና ከዚህ በላይ መጠበቅ ባልተቻለ ጊዜ፣ እንደ ምንም ሆኖ በቂ ነገር ይገኝ ነበር—ምንም እንኳ ፍላጎቱን ለማሟላት በጭንቅ የሚበቃ ቢሆንም።

ይህን የ«ትረካ»ውን ክፍል ለማሟላት እዚህ ላይ መጨመር የሚገባው፣ በኦገስት 1840 በቀን ትምህርት ቤቶች የሚደክሙት ወንድሞችና እኅቶች ወደዚሁ የቅርብ ኅብረትና ልመና እንዲገቡ በማድረግ ይህ የጸሎት ክበብ ይበልጥ መስፋቱ ነው፤ ሊነሡ የሚችሉትን ቀውሶች ለውጭ ሰዎች እንዳይገልጡ የተሰጡት እነዚያው ጽኑ ትእዛዞች ለእነርሱም ተደገሙላቸው።

የጉዳዮቹን ሁኔታ ለዚህን ያህል ለሰፋ የረዳቶች ቡድን ማሳወቅ በሁሉም መንገድ ታላቅ በረከትን አመጣ፤ በተለይም ለረዳቶቹ ራሳቸው። በዚህም ልባዊ፣ የእምነትና የማያቋርጥ ጸሎታቸው ተቀሰቀሰ፤ ከዚያ በኋላ የሥራው እድገት ምን ያህሉ በእምነታቸው፣ በልመናቸውና ራሳቸውን በመካዳቸው እንደ ሆነ የሚያውቅ እግዚአብሔር ብቻ ነው። ስለ ጋራ ሕይወታቸው ችግሮች ያገኙት ተግባራዊ ዕውቀት ራስ ወዳድነት የሌለበትን መንፈስ ወለደ፤ ይህም መንፈስ ሰዋዊ መዝገብ ወይም የተጻፈ ታሪክ የሌላቸውን ቍጥር የሌላቸው የጀግንነት መሥዋዕቶች አነሣሣ፤ እነዚህም ሊታወቁ የሚችሉት የተሰወሩ ነገሮች ወደ ብርሃን በሚወጡበት ቀን፣ የጌታ የራሱ ማስታወሻ ገጾች በተሰበሰበው ፍጥረት ሁሉ ፊት በሚነበቡበት ጊዜ ብቻ ነው። አቶ ሙለር ከዚህ ዓለም ከተለየ ወዲህ ከተቀበሉት ስጦታዎች ምን ያህል ታላቅ ድርሻ ከእርሱ የመጣ እንደ ሆነ ታውቋል፤ ነገር ግን በዚህ በተቀደሰ የጸሎት ክበብ ውስጥ የነበሩት የሥራ ባልደረቦቹ በስውር የሰጡትን ስጦታ ጠቅላላ መጠን የምናረጋግጥበት መንገድ የለም።

ይሁን እንጂ ምንም እንኳ ሠራዊቱን የሚመራው እርሱ ቢሆንም፣ ራሱን ክዶ የሚሰጥ አቶ ሙለር ብቻ እንዳልነበረ እናውቃለን። እውነተኞቹ የቀንበር ባልንጀሮቹ ትንሽ ቢሆንም ውድ በሆነው በራሳቸው መባ ብዙ ጊዜ ቀውሱን ለወጡት! በስጦታቸው ያለውን ችግር ለማቃለል እግዚአብሔር እንደ መሣሪያ ተጠቀመባቸው፤ ምክንያቱም «የድህነታቸው ጥልቅነት የልግስናቸውን ባለ ጠግነት አብዝቶአል»። የሰጡት ገንዘብ አንዳንድ ጊዜ እንደ መበለቲቱ ሁለት ሳንቲሞች—ያላቸው ትዳር ሁሉ ነበር፤ የመጨረሻዋ ፔኒ ብቻ ሳትሆን ጌጣጌጦች፣ ዕንቍዎች፣ ከአባቶች የተወረሱ ቅርሶች፣ ለረጅም ጊዜ ተጠብቀው የተወደዱ ሀብቶች፣ በኢየሱስ እግር ላይ እንደ ተሰበረው የሽቱ የአልባስጥሮስ ቢልቃጥ፣ በፈቃድ እንደሚቀርብ መሥዋዕት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ ተቀመጡ። በእግዚአብሔር ቤት መብል እንዲኖርና ለታናናሾቹ እንጀራ ወይም ሌላ የሚያስፈልግ ስንቅ እንዳይጎድል፣ የሚተርፋቸውን ሁሉ፣ ብዙ ጊዜም ሊያጡት የማይችሉትን ሰጡ። በከፍተኛ ትርጕም ይህ ሥራ የአቶ ሙለር ብቻ ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ለእነዚህ ቤት ለሌላቸው ምስኪኖች ዕቅዱን ሊያራምድ በመረጠበት፣ ከእርሱ ጋር በጸሎትና በእንባ፣ በጭንቀትና በድካም፣ ራስን በመካድና ራስን በማቅረብ የተካፈሉት የእነርሱም ጭምር ነበር! እነዚህ ረዳቶች ሁሉ በጸሎት አዲስ ኃይልን፣ መተማመንንና በረከትን ያገኙት እንዲህ በመስጠት ነበር፤ ከእነርሱ አንዱ እንዳለው፣ «ያለውን ሳይሰጥ መጸለይ ብዙም ቅንነት አይሆንም» ብሎ ተሰምቶት ነበርና።*

* «ትረካ»፣ 1: 246።

ወደ አቶ ሙለር ምሥጢር እንዲህ የገቡት ረዳቶች ከእርሱና ከሥራው ጋር ይበልጥ ንቁ በሆነ ኅብረተ ስሜት ተቀራረቡ፤ ከዚያው መንፈስም እየጨመሩ ተካፈሉ። ከዚህም ጥቂት ማሳያዎችና ምሳሌዎች በማስታወሻው ውስጥ ተመዝግበዋል።

አንድ ጨዋ ሰውና አንዳንድ ሴቶች የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ቤቶች ሲጎበኙ፣ እንክብካቤ የሚያስፈልጋቸውን የታናናሾቹን ብዛት አዩ። ከሴቶቹ አንዲቱ የወንዶች ልጆች ቤት ኃላፊን፦ «በእርግጥ እነዚህን ተቋማት ጥሩ የገንዘብ ክምችት ሳይኖራችሁ ልታካሂዱ አትችሉም» አለቻት፤ ጨዋውም ሰው፦ «ጥሩ ክምችት አላችሁ?» ብሎ ጨመረ። ጸጥ ያለው መልስ፦ «ገንዘባችን የተቀመጠው ሊከስር በማይችል ባንክ ውስጥ ነው» የሚል ነበር። መልሱ ከሴቲቱ ዓይኖች እንባን፣ ከጨዋው ሰው ኪስ ደግሞ የአምስት ፓውንድ ስጦታን አወጣ—ይህም በዚያን ጊዜ በእጃቸው አንዲት ፔኒ እንኳ ስላልነበረ እጅግ ወቅቱን የጠበቀ ስጦታ ነበር።

ለራሳቸው ምንም ያልለመኑ፣ ነገር ግን ለራሳቸው ስንቅ በደስታ ወደ ጌታ የተመለከቱ፣ በችግርም ሰዓት የራሳቸውን ገንዘብ ወይም ንብረት በፈቃዳቸው የሰጡ እንደነዚህ ያሉ የሥራ ባልደረቦች የአቶ ሙለርን ልብ ለእግዚአብሔር በምስጋና ሞሉት፤ አሮንና ሖር የሙሴን እጆች እንደ ደገፉ፣ የሕይወቱ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ እጆቹን ደገፉ። በኃላፊነቱ ዘመን ሁሉ እነዚህ ለእምነቱና ለድፍረቱ ዋነኛ ሰዋዊ ድጋፍ ነበሩ። በየዕለቱ ከእርሱ ጋር ለጸሎት ይሰበሰቡ ነበር፤ በታላላቅ የእምነት ፈተናዎች ወቅት የጌታን ሥራ ምሥጢር በመካከላቸው በታማኝነት ጠበቁ፤ የድል ሰዓት በመጣ ጊዜም ሰዎች ሁሉ ፍቅሩንና ታማኝነቱን አውቀው ክብርን ለእርሱ እንዲሰጡ፣ በዓመታዊው ሪፖርት መታደጋቸውን ማወጅና በእግዚአብሔር መመካት ግዴታም መብትም እንደ ሆነ ተሰማቸው።

ከሥራው አስተዳደር ጋር በተያያዘ አልፎ አልፎ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ተነሡ፤ እነዚህም በሁሉም የክርስቲያን አገልግሎት ዘርፎች ላይ ሰፊ ተዛምዶ አላቸው፤ ምክንያቱም መፍትሔያቸው የጌታ ሥራ ሥነ ምግባርና ምጣኔ ሀብት ሊባል ከሚችለው ጋር ይገናኛል። ከእነዚህ ጥቂቶቹን በአጭሩ እንመልከት።

ጌታ በየዕለቱ ይይዛቸው ስለ ነበረ፣ በየዕለቱ መኖር እንደሚገባቸው ግልጽ መሰለ። ከተለመደው ሳምንታዊ የእንጀራ፣ የወተትና የሌሎችም አቅርቦት በተፈጥሮ የሚጠራቀሙት እንኳ ቢሆኑ ምንም ዓይነት ዕዳ እንዲከማች መፈቀድ አልነበረበትም። ስለዚህ ከሴፕቴምበር 1838 አጋማሽ ጀምሮ የሚገዛው ዕቃ ሁሉ በዚያው ጊዜ እንዲከፈል ተወሰነ።

ደግሞም ኪራይ በተወሰነ መጠንና በተወሰነ ጊዜ ይደርስ ነበር። ስለዚህ ይህ ፍላጎት ያልተጠበቀ አልነበረም፤ ከአንድ አንጻር ሲታይም ኪራዩ በረዘመ ጊዜ ልዩነት ቢሰበሰብም በየዕለቱ ወይም በየሳምንቱ የሚደርስ ዕዳ ነበር። ምንም ዕዳ ውስጥ መግባት የለበትም የሚለው መመሪያ ከተቀመጠ በኋላ፣ ይህ መመሪያ ለኪራይ የሚገባው መጠን በዚያን ጊዜ የሚከፈል ባይሆንም እንኳ በየዕለቱ ወይም ቢያንስ በየሳምንቱ ተለይቶ መቀመጥ እንዳለበት የሚያመለክት ሆኖ ተቈጠረ። ይህ ደንብ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ተቀባይነት አገኘ፤ በዚህ መንገድ ተለይቶ የተቀመጠ ገንዘብ ለዚያው ዓላማ የተቀደሰ እንደ ሆነና ለጊዜውም ቢሆን ለሌላ ለማንኛውም ነገር እንዳይወሰድ በመረዳት ነበር።

እንዲህ ያለ ሕሊናዊ ጥንቃቄና ጽናት ቢኖርም የእምነትና የትዕግሥት ፈተና ቀጠለ። ገንዘብ የሚገባው በትንሽ በትንሹ ብቻ ነበር፤ በጠበቀ ቍጠባም የእያንዳንዱን ቀን ፍላጎት ለማሟላት በጭንቅ ይበቃ ነበር። ሁኔታው ብዙ ጊዜ እጅግ የጨለመ፣ የወደፊቱም እጅግ አስፈሪ ነበር፤ ነገር ግን አንድም እውነተኛ ፍላጎት ሳይሟላ አልቀረም፦ ስለዚህ ምስጋና ሁልጊዜ ከጸሎት ጋር ተቀላቀለ፤ የምስጋና ዕጣን የልመናውን ነበልባል መዓዛ ያለው አደረገው። የእግዚአብሔር ጣልቃ የሚገባ ኃይልና ፍቅር ሊጠረጠር አልቻለም፤ ርዳታ ብዙ ጊዜ በጭንቁ ጽንፍ ሰዓት፣ በሚያስፈልገውም ትክክለኛ ዓይነት ወይም መጠን ይመጣ ስለ ነበረ፣ እንደማያጠራጥሩ ሐቆች ይበልጥ ጥልቅ ስሜት አሳደረ። ስንቁ ፈጽሞ ከማለቁ በፊት አዲስ ስንቅ ወይም መግዣ ገንዘብ ይመጣ ነበር፤ ስለዚህ እነዚህ ብዙ አፎች ሁልጊዜ ተመገቡ፣ እነዚህ ብዙ ሰውነቶችም ሁልጊዜ ለበሱ።

የተቀመጡትን እንዲህ ያሉ መመሪያዎች ጠብቆ መኖር በማያቋርጥና ሕያው በሆነ ልምምድ የሚጠበቅ እምነት ከሌለ የማይቻል ነበር። ለምሳሌ በ1838 የመጨረሻዎቹ ወራት በእርሱ ብቻ በእውነት ይታመኑ እንደ ሆነ ወይም እንዳልሆነ እግዚአብሔር ሆን ብሎ በብርቱ ፈተና የሚፈትናቸው መሰለ። የወላጅ አልባ ሕፃናቱ ሥራ በማያቋርጥ ጭንቀት ውስጥ ነበር፤ አንዳንድ ጊዜ በሦስቱ ቤቶች ኃላፊዎች እጅ ግማሽ ፔኒ እንኳ አልነበረም። ነገር ግን እንዲህ ያሉ ሐቆች ፈጽሞ እንዲወጡ፣ ወይም ስለ ከባዱ ችግር ለውጭ ሰዎች ምንም ፍንጭ እንዲሰጥ አልተፈቀደም ብቻ ሳይሆን፣ ለመርዳት አስበው የጠየቁት እንኳ አልተነገራቸውም።

አንድ ምሽት አንድ ወንድም የሚቀጥለው ሒሳብ ሲዘጋ ቀሪ ሒሳቡ እንዴት እንደሚሆን፣ የቀድሞው የሒሳብ ሰነድ ሲዘጋጅ እንደ ነበረው ለወላጅ አልባዎቹ የሚጠቅም ያህል ታላቅ ይሆን እንደ ሆነ ለመጠየቅ ደፈረ። የአቶ ሙለር የተረጋጋ ነገር ግን ቀጥተኛ ያልሆነ መልስ፦ «ጌታ የወደደውን ያህል ታላቅ ይሆናል» የሚል ነበር። ይህ ሆን ተብሎ የተደረገ ንቀት አልነበረም። ከዚህ በላይ መናገር ከአንዱ ረዳት ዘወር ብሎ ቢያንስ በተዘዋዋሪ ርዳታን ከሰው መለመን ይሆን ነበር፤ ያ አንድ ታላቅ ዓላማ—በሕያው እግዚአብሔር ብቻ መታመን ለሰዎች ሁሉ አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ—ከዓይን እንዳይሰወር እንዲህ ያለው ወጥመድ ሁሉ በጥንቃቄ ተወገደ።

አቶ ሙለር የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም ሥራ በሙሉ ብዙ ጊዜ የገባበትን የጭንቀት ክብደት እያመነ፣ እነዚህ ጭንቀቶች ፈጽሞ ያልጠበቃቸው ድንገተኛ ነገሮች እንዳልነበሩ፣ በገንዘብ ረገድም የነበረው ተስፋ እንዳልከሸፈ፣ ይልቁንም የተገላቢጦሽ እንደ ሆነ አንባቢዎቹን ለማረጋገጥ ይጥራል። ጸሎትን ለሚሰማ አምላክ ለሚሰጠው ሙሉ ምስክርነት ታላላቅ ጭንቀቶች አስፈላጊ እንደ ሆኑ አስቀድሞ ይጠብቃቸው ነበር። ማንኛውም ሰዋዊ ርዳታ እስከ ተፈለገ ወይም በዓይን እስከ ታየ ድረስ ሁሉን የሚችለው እጅ በግልጽ ሊታይ ፈጽሞ አይችልም። ወደ ሕያው እግዚአብሔር በሙላት እንመለስ ዘንድ ከሌላው ሁሉ ፈጽመን ፊታችንን ማዞር አለብን። መታደጉ ጎልቶ የሚታየው አደጋው በከበደበት መጠን ብቻ ነው፤ ትርጕሙም ከፍ የሚለው ያለ እግዚአብሔር ፍጹም ተስፋ መቍረጥ በሚገጥመን ጊዜ ነው። ስለዚህ ሥራው በዋነኝነት የተጀመረበት ዓላማ ሊደረስበት የሚችለው በእንዲህ ያሉ የጽንፍ ሁኔታዎችና በጽንፍ ጊዜ እግዚአብሔር ጣልቃ በሚገባባቸው ልምምዶች ብቻ ነበር።

የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ሥራ ውስጣዊ ታሪክ በጥቂቱ ብቻ የሚያውቁ አንዳንዶች፣ ስለ ሥራው በአፍ፣ በተለይም በታተሙት ዓመታዊ ሪፖርቶች በብዕር የተነገሩት ይፋዊ መግለጫዎች የርዳታ ልመናዎች ሆነዋል ብለው በመገመት የስንቁን መደበኛነት በተፈጥሮ ሁኔታ አብራርተውታል። አለማመን የእግዚአብሔርን ሥራ ሁሉ፣ የቱንም ያህል አስደናቂ ቢሆን፣ በ«የተፈጥሮ ሕጎች» ይተረጕማል፤ ሥጋዊ አእምሮም በእግዚአብሔር ኃይል መገለጦች ውስጥ ከተፈጥሮ በላይ የሆነ ኃይል ሲሠራ ለማየት እምቢ ብሎ፣ «የጸሎት ተአምራትን» ሁሉ እንዲህ እያብራራ ለማስተባበል ይጸናል።

እግዚአብሔር ለእነዚህ ወላጅ አልባ ሕፃናት ሁሉ፣ እንዲሁም ለሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ዕውቀት ተቋም የሥራ ዘርፎች በየዕለቱ ባቀረበባቸው አስደናቂ መንገዶች ርኅሩኆችና አዛኝ ልቦች በብርቱ እንደ ተነኩ ጥርጥር የለውም፤ አማኝ ነፍሳትም እንዲህ ለሚመራ ሥራ ፍቅርና ልባዊ ኅብረተ ስሜት እንዲኖራቸው ተስበው ረዳቶቹ እንዲሆኑ ተመርተዋል። እግዚአብሔር እንዲህ ያለውን ውጤት ለማስገኘት እነዚህን ዓመታዊ ሪፖርቶች እንደ ተጠቀመባቸው የታወቀ ሐቅ ነው። ቢሆንም እነዚህ ሪፖርቶች የርዳታ ልመና እንዲሆኑ ፈጽሞ እንዳልታሰቡና እንዳልወጡ፣ ወቅታዊ ርዳታን ለማግኘትም በእነርሱ ላይ ምንም መደገፍ እንዳልተደረገ እውነት ሆኖ ይኖራል። ደግሞም ምንም ያህል ተደጋግመው ቢወጡ፣ በሰፊው ቢሰራጩ ወይም ታላቅ ተጽዕኖ ቢኖራቸው፣ የፍላጎቶች ሁሉ ስንቅ መደበኛነትና ብዛት በሌላ መንገድ ሊብራራ እንደሚገባው የማይካድ ነው።

ይፋዊ ስብሰባዎች ከተደረጉ ወይም የታተሙ ሪፖርቶች ከወጡ ከጥቂት ቀናት በኋላ ብቻ ገንዘቡ ብዙ ጊዜ እጅግ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ይወርድ ነበር። አቶ ሙለርና ረዳቶቹ በእንዲህ ያሉ ቀጥተኛ ባልሆኑ ልመናዎች ላይ ያለአግባብ ከመደገፍ ሁሉ በሚያስደንቅ ሁኔታ ተጠበቁ፤ በእንዲህ ያሉ መንገዶች ገንዘብ እንዲገባ ወደ መጠበቅ ፈጽሞ እንዳይተዉ እግዚአብሔርን ደጋግመውና በግልጽ ለመኑት። ጌታ ከእነርሱ ጋር ያደረገው አያያዝ በብዙ ምክንያት እንዲታወቅ ተደረገ፤ የእንዲህ ያለው ይፋነት ዋነኛ ዓላማ ግን ሁልጊዜ ለእግዚአብሔር ታማኝነት ምስክርነት ነበር። አቶ ሙለር ይህን ታላቅ ዓላማ ሁልጊዜ በፊት አስቀደመው፤ እግዚአብሔር ለተስፋ ቃሎቹ ስላለው ታማኝነትና እያንዳንዱን አዲስ ፍላጎት ስላሟላበት መንገድ በሚቀርቡ እንዲህ ያሉ መዛግብትና መገለጦች፣ ባሪያው በእርሱ እንደ ሕያው አምላክ የሚታመንን እምነት ሊያነቃ፣ ሊያነሣሣና ሊያበረታታ እንዲችል ተስፋ አደረገ፣ ጸለየም። ለሰዋዊ ርዳታ የሚቀርብ ልመናም ሆነ ለወላጅ አልባዎቹ ርኅራኄንና ሐዘኔታን ለማነሣሣት የሚደረግ ሙከራ በግልጽ እንደሌለባቸው ለማየት እነዚህን ሪፖርቶች ማንበብ ብቻ ይበቃል። የእያንዳንዱ ሪፖርት ዋና መልእክት አንባቢው ራሱን ፈጽሞ ለእግዚአብሔር አሳልፎ እንዲሰጥ፣ እግዚአብሔር ቸር እንደ ሆነ ቀምሶ እንዲያይ፣ በእርሱ የሚታመኑ ሁሉ ምንኛ ብፁዓን እንደ ሆኑም ለራሱ እንዲያገኝ ማነሣሣት ነው። እነዚህን የእምነት ሕይወት መዛግብት በማስተዋልና በግልጽ ልናነብባቸው የምንችለው በዚህ ታላቅ ዓላማ ብርሃን ብቻ ነው።

በ1839 መጸው የሰውነት ድካም እንደ ገና ለጊዜው ከንቁ ሥራ እንዲያርፍ አስገደደው፤ አቶ ሙለርም ወደ ትሮውብሪጅና ወደ ኤክሰተር፣ ወደ ቲንማውዝና ወደ ፕሊመዝ ሄደ። እግዚአብሔር በመከራ ትምህርት ቤት ውስጥ በተሻለ ሊያስተምረው የሚችላቸው ውድ ትምህርቶች ነበሩት።

አቶ ሙለር በፕሊመዝ ሳለ ለአምልኮታዊ ኅብረት ሲል በማለዳ የመነሣትን ግፊት እንደ ገና ተሰማው። በሃሌ ሳለ በትምህርት የላቀ ለመሆን ባለው ቅንዓት ተገፋፍቶ በማለዳ የሚነሣ ሰው ነበር። ከዚያ በኋላ ግን ደካማው ራሱና የደከሙት ነርቮቹ ተጨማሪ እንቅልፍ የሚያስፈልጋቸው በመሰሉ ጊዜ፣ ዘግይቶ ቢነሣ እንኳ ቀኑ ያቺን ጥቂት የብርታት ክምችቱን ለመጨረስ በቂ ርዝመት እንደሚኖረው አሰበ፤ ስለዚህ በአራት ሰዓት ከመነሣት ይልቅ ብዙ ጊዜ እስከ ስድስት ወይም እስከ ሰባት ሰዓት (በአውሮፓውያን አቈጣጠር) ድረስ በአልጋው ላይ ይተኛ ነበር፤ ከምሳ በኋላም ለሩብ ሰዓት ያንቀላፋ ነበር። አሁን ግን በመንፈሳዊ ብርታት እየከሰረ እንደ ሆነና በዚህ አዲስ ሥርዓት ሥር የነፍሱ ጤንነት እየቀነሰ እንደ ሄደ እየተሰማው መጣ። ሥራው አሁን ቃሉን በሚገባ እንዳያነብብ እስኪከለክለውና ለስውር ጸሎት የሚሆነውን ጊዜ እስኪነጥቀው ድረስ አጣበቀው።

በፕሊመዝ ተቀምጦበት በነበረው ቤት ያለው ወንድም የተናገረው «በአጋጣሚ የተነገረ ቃል»—በአማኝ ሕይወት ውስጥ አጋጣሚ የሚባል የለም!—በጥልቅ ነካው። ስለ ዘሌዋውያን መሥዋዕቶች እየተናገረ፣ የእንስሶቹ ተረፈ ምርት ፈጽሞ በመሠዊያው ላይ እንደማይቀርብ፣ ነገር ግን ምርጡ ክፍልና ስቡ ብቻ እንደሚቀርብ፣ እንዲሁ የጊዜያችንና የኃይላችን ምርጡ፣ የቀናችንም ምርጥ ክፍል በተለይ በአምልኮና በኅብረት ለጌታ ሊሰጥ ይገባዋል አለ። ጆርጅ ሙለር በዚህ ላይ ብዙ አሰላሰለ፤ የሰውነቱን ጤና ሊጎዳ የሚችልበት አደጋ ቢኖርም እንኳ ምርጥ ሰዓቶቹን ከእንግዲህ በአልጋ ላይ እንዳያሳልፍ ቆረጠ። ከዚያ ወዲህ ለራሱ የሰባት ሰዓት እንቅልፍ ብቻ ፈቀደ፤ ከምሳ በኋላ የሚያደርገውንም ዕረፍት ተወ። እንደ ገና በማለዳ መነሣቱ፣ ከቍርስና ከተከታዮቹ የማይቀሩ መቋረጦች በፊት፣ በጸሎትና ቅዱሳት መጻሕፍትን በማሰላሰል ከእግዚአብሔር ጋር ያልተቋረጡ ረጅም የመገናኛ ጊዜያትን አስገኘለት። በሥጋ እንዳልከፋው ይልቁንም እንደ ተሻለው አገኘ፤ እንደ ቀድሞው በአልጋ ላይ ረዘም ላለ ጊዜ መተኛቱ ነርቮቹን ደካሞች አድርጎ ያቈያቸው እንደ ነበረም አመነ፤ በመንፈሳዊ ሕይወትም ረገድ፣ ሌሎች ተኝተው ሳሉ እንዲህ እግዚአብሔርን በመጠበቁ እጅግ አዲስ ሕያውነትና ብርታት ስለ ተገኘ፣ ይህ ልማድ በቀረው ዕድሜው ሁሉ ጸና።

በኖቬምበር 1839 ፍላጎቱ እንደ ገና ታላቅ፣ ስንቁም እጅግ ጥቂት በሆነ ጊዜ፣ በሰላም ተጠበቀ፦ «በዚያን ጊዜ የምመለከተው በእጄ ያለውን ጥቂቱን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ሙላት ነበር» ይላል።

ከላይ ርዳታን ለመለመን ይበልጥ ድፍረት እንዲኖረው ያለውን ሁሉ ከራሱ ማራገፍ ልማዱ ነበር። ገበያ ከተገኘላቸው የማያስፈልጉ ዕቃዎች ሁሉ ይሸጡ ነበር። ነገር ግን በጌታ ሥራ ጠቃሚ የሆነውን እንደማያስፈልግ አልቈጠረውም፤ አብ ፍላጎቱን ያውቃልና ሊሸጠው ትክክል እንደ ሆነም አላሰበም። ከሥራ ባልደረቦቹ አንዱ ለኪራይ ተለይቶ ተቀምጦ ለጊዜው ግን ተወስዶ የነበረው ገንዘብ እንዲመለስ ዋስትና አድርጎ ውድ ሰዓቱን አቅርቦ ነበር፤ ሆኖም ሰዓቱ ለጌታ አገልግሎት ከሚያስፈልጉና ከሚጠቅሙ ዕቃዎች መካከል ሊቈጠር ስለሚችል፣ ይህም ዘዴ እንኳ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መስሎ አልታየም፤ እንዲህ ያሉ ዘዴዎች ፈጽመው ቢተዉ ደግሞ መታደጉ ከጌታ እንደ ሆነ ይበልጥ ግልጽ ይሆናል። ስለዚህ በአንዱና በብቸኛው ረዳት ላይ ያለውን ሙሉ መታመንና ብቸኛ መደገፍ አደጋ ላይ ሊጥሉ የሚችሉ መጠጊያዎች ሁሉ አንድ በአንድ ተተዉ።

የአቅማቸው ድህነት እጅግ ያስጨነቀ በመሰለ ጊዜ እንኳ፣ አቶ ሙለር እግዚአብሔር እንዳልረሳና በየዕለቱም «የሚያስፈልጋቸውን እንጀራ» እንደሚመግባቸው በሚያሳየው በዕለታዊው ማስረጃ ራሱን ያጽናና ነበር። ብዙ ጊዜም ለራሱ፦ «የሰው ችግር የእግዚአብሔር አጋጣሚ ነው» የሚለው የዓለም ምሳሌ እንኳ ከሆነ፣ የእግዚአብሔር የራሱ ውድ ልጆች በታላቅ ችግራቸው ጊዜ ጽንፍ ጭንቀታቸውን ፍቅሩንና ኃይሉን የሚገልጥበት ተገቢ ጊዜ እንዲያደርገው ወደ እርሱ ለመመልከት እንዴት ይበልጥ ይችሉ ይሆን! ይል ነበር።

በፌብሩዋሪ 1840 ሌላ የሕመም ጥቃት ወደ ጀርመን ከተደረገ የአገልግሎት ጕዞ ጋር ተዳምሮ አቶ ሙለርን ለአምስት ሳምንታት ወደ አውሮፓ ምድር ወሰደው። ሃይመርስሌበን በደረሰ ጊዜ አባቱን በከባድ ሳል ደክሞ አገኘው፤ በዚያም በጸሎት፣ ቃሉን በማንበብና ጌታን በመመስከር አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈባቸው ሁለቱ ክፍሎች፣ ከሃያ ዓመት ገደማ በፊት ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር ያልታረቀ ኃጢአተኛ ሆኖ አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈባቸው እነዚያው ክፍሎች ነበሩ። ከዚያም በቮልፈንቢውተል በ1821 ዕዳ ውስጥ ሆኖ የሸሸበትን የእንግዳ ማረፊያ ቤት አየ። ከአባቱ ጋር እንደ ገና ሲሰናበት ይህ የመጨረሻ ስንብቱ ይሆናል ብሎ ፈርቶ በብርቱ ሥቃይ ተወጋ፤ አባቱም አሁን ያልተለመደ ርኅራኄና ፍቅር አሳየው፤ ሙለርም አባቱ በውጫዊና በሥርዓታዊ ሃይማኖተኛነት ላይ ሳይደገፍ፣ ወይም የጸሎትንና የቅዱሳት መጻሕፍትን ንባብ ከውስጣዊ የክርስቶስ መምሰል ፋንታ ሳያደርግ፣ በጌታ በኢየሱስ ውስጥ በደኅንነት እንዳለ ለማወቅ ይበልጥ እየናፈቀ ሄደ። ይህ የመጨረሻው ግንኙነታቸው ሆነ፤ አባቱ በዚያው ዓመት በማርች 30 ሞቷልና።

የዚህ የጀርመን ጕዞ ዋነኛ ዓላማ ተጨማሪ ሚስዮናውያንን ወደ ምሥራቅ መላክ ነበር። አቶ ሙለር በዛንደርስሌበን ወዳጁን አቶ ሽታልሽሚትን አገኘ፤ ፖሊስን ለማምለጥ በስውር የሚሰበሰቡ ጥቂት ደቀ መዛሙርትንም አገኘ። ሁልጊዜ የሃይማኖት ነጻነትን አየር የተነፈሱ ሰዎች በዚያ በስም ብቻ ክርስቲያን በሆነ አገር የአምልኮን ነጻነት ሁሉ ያፈነውን እንዲህ ያለውን አለመቻቻል ብዙም አያውቁም። ከአሥራ አንድ ዓመት በፊት የአቶ ሽታልሽሚት አገልጋይ ወደዚህ ስፍራ በመጣ ጊዜ ከጌታው በቀር አንድም እውነተኛ ደቀ መዝሙር ማግኘት አልቻለም ነበር። የመጀመሪያዎቹ ስብሰባዎች በእውነት የሁለት ወይም የሦስት ሰዎች ብቻ ነበሩ፤ ጥቂት በሰፉ ጊዜም አቶ ክሮል ወደ ዳኞች ፊት ተጠርቶ፣ በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያ ዘመን እንደ ነበሩት ሐዋርያት፣ በስሙ እንዳይናገር ተከለከለ። ነገር ግን እንደ ገና እንደ እነዚያው የጥንት ደቀ መዛሙርት፣ «ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል» ብለው በማመን፣ ያ የአማኞች ቡድን እጅግ የሚረብሹ የፖሊስ ወረራዎችና እጅግ ከባድ የመንግሥት ቅጣቶች ቢኖሩም መሰብሰቡን ቀጠለ። ሆኖም ስብሰባዎቻቸው እጅግ ስውር ከመሆናቸው የተነሣ የተወሰነ ስፍራም ሆነ መደበኛ ጊዜ አልነበራቸውም።

ጆርጅ ሙለር እነዚህን የተሰደዱ አማኞች አንድ ወንበር ብቻ በነበረበት በአንድ ትሑት ሸማኔ ክፍል ውስጥ ተሰብስበው አገኛቸው። በዚያ የነበሩት ሃያ አምስት ወይም ሠላሳ ሰዎች ራሱ የቦታውን እኩሌታ በሞላው የሽመና መሣሪያ ውስጥና ዙሪያ እንደ ተመቻቸላቸው የሚቀመጡበት ወይም የሚቆሙበት ስፍራ አገኙ።

አቶ ሙለር በሃልበርሽታት እውነተኛ የመለወጥ ማስረጃ ያሳየ አንድም ቄስ የሌለባቸው ሰባት ታላላቅ የፕሮቴስታንት አብያተ ክርስቲያናትን አገኘ፤ በዚያ የነበሩት ጥቂት እውነተኛ ደቀ መዛሙርትም እንዲሁ በአንድነት እንዳይሰበሰቡ ተከልክለው ነበር።

በጀርመን ካሳለፋቸው ጥቂት ሳምንታት ወደ ብሪስቶል ከተመለሰ ከጥቂት ቀናት በኋላ፣ በሥራው ታላቅ የገንዘብ ጭንቀት በነበረበት ጊዜ፣ ቀደም ብሎ ብዙ ጊዜ ገንዘብ ከሰጠ አንድ ወንድም እንዲህ የሚል ደብዳቤ ደረሰው፦

«በእርስዎ ጥበቃ ሥር ላለው ተቋም አሁን የሚያስፈልግ ነገር አለ? ሥራውን ከሚሠሩለት ከእርሱ በቀር እንደማይለምኑ አውቃለሁ፤ ነገር ግን ሲጠየቁ መመለስ ሌላ ነገር፣ ደግሞም ትክክለኛ ነገር ይመስላል። ለሚያገለግሏቸው ዓላማዎች ያለዎትን የአሁኑን የገንዘብ ሁኔታ ለማወቅ የምፈልግበት ምክንያት አለኝ፤ ይኸውም፣ እርስዎ ፍላጎት ባይኖርዎ፣ ሌሎች የጌታ ሥራ ዘርፎች ወይም ሌሎች የጌታ ሰዎች ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። ስለዚህ እባክዎ ያሳውቁኝ፤ በምን ያህል መጠንም፣ ማለትም አሁን ምን ያህል እንደሚያስፈልግዎ ወይም በጥቅም ላይ ሊያውሉ እንደሚችሉ።»

ለአብዛኞቹ ሰዎች፣ የእምነትና የጸሎት ሥራ ለሚያካሂዱትም እንኳ፣ እንዲህ ያለው ደብዳቤ ቢያንስ ፈተና በሆነ ነበር። አቶ ሙለር ግን አልተወላወለም። የሥራውን ትክክለኛ ፍላጎት ለጠያቂ እንኳ ማሳወቅ፣ በእርሱ አስተያየት፣ ሁለት ከባድ አደጋዎችን ያስከትላል፦

1. የራሱን ዓይኖች ከእግዚአብሔር ወደ ሰው ያዞራል፤

2. የቅዱሳንን አእምሮ በእርሱ ብቻ ከመደገፍ ያርቃል።

ይህ የእግዚአብሔር ሰው ሁሉን ነገር በአንድ ታላቅ ሙከራ ላይ አስደግፎ ነበር—ወደ እግዚአብሔር ብቻ የሚጠጋ ጸሎት፣ እግዚአብሔር እንደ ማቃለያና እንደ ርዳታ መንገድ የሚጠቀምባቸው ሕዝቡ ቀውሱን ባያውቁት እንኳ፣ በማንኛውም ቀውስ ርዳታን እንደሚያመጣ ለማረጋገጥ ቆርጦ ተነሥቶ ነበር።

በዚህ ጊዜ በመቶዎች የሚቈጠሩ ወላጅ አልባ ሕፃናትን ፍላጎት ለማሟላት በእጅ የቀረው በአጠቃላይ ሃያ ሰባት ፔንስ ተኩል ብቻ ነበር። ቢሆንም ለደብዳቤው የተሰጠው መልስ ይህ ነበር፦

«ስለ ፍቅርዎ እያመሰገንኩዎ፣ በአጠቃላይ ሲታይም ገንዘብ በመለመንና ሲጠየቁ በመመለስ መካከል ልዩነት እንዳለ ከእርስዎ ጋር እየተስማማሁ፣ በእኛ ጉዳይ ግን ስለ ገንዘባችን ሁኔታ ለመናገር ነጻነት አይሰማኝም፤ ምክንያቱም በእጄ ያለው ሥራ ዋነኛ ዓላማ በእምነት የደከሙትን ከእግዚአብሔር ጋር በሚደረግ አያያዝ እውነተኛነት እንዳለ እንዲያዩ መምራት ነው—ከእርሱ ጋር ብቻ።»

ሆኖም ከአቋሙ ጋር በሚስማማ ሁኔታ፣ መልሱ በፖስታ እንደ ተላከ ወዲያውኑ ልመናው ወደ ሕያው እግዚአብሔር ወጣ፦ «ጌታ ሆይ፣ ስለ አንተ ብዬ ለዚህ ወንድም ስለ ችግራችን እንዳልነገርሁት አንተ ታውቃለህ። አሁንም፣ ጌታ ሆይ፣ ስለ ችግራችን ለአንተ ብቻ መናገር እውነተኛ እንደ ሆነ እንደ ገና አሳይ፤ ስለዚህም ይረዳን ዘንድ ለዚህ ወንድም ተናገረው።» ለዚህም መልስ፣ እግዚአብሔር ይህን የጠየቀውን ወንድም አንድ መቶ ፓውንድ እንዲልክ አነሣሣው፤ ይህም የደረሰው በእጃቸው አንዲት ፔኒ እንኳ ባልነበረበት ጊዜ ነበር።

ለረጅም ጊዜ የተፈተነው የእምነት መተማመን እየጨመረ የሚሄድ ዋጋውን አገኘ፤ በተሞክሮም እየጸና ሄደ። በጁላይ 1845 አቶ ሙለር እነዚያኑ የፈተና ዓመታት መለስ ብሎ በማየት ይህን ምስክርነት ሰጠ፦

«ለሰባት ዓመታት ያህል ገንዘባችን እጅግ ተሟጦ ስለ ነበር፣ የወላጅ አልባ ሕፃናቱን ፍላጎት ለሦስት ቀናት በተከታታይ የሚያሟላ ገንዘብ በእጃችን የተገኘበት ጊዜ በአንጻሩ እምብዛም ነበር፤ ቢሆንም በመንፈሴ የተፈተንሁት አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤ ይኸውም ጌታ ጸሎታችንን የማይመለከት የመሰለበት የመጀመሪያው ጊዜ በሆነው በሴፕቴምበር 18 ቀን 1838 ነበር። ነገር ግን በዚያን ጊዜ እርዳታን በላከ ጊዜ፣ እንዲህ እጅግ ዝቅ ያልነው ሥራውን ስለ ተወው ሳይሆን እምነታችን እንዲፈተን ብቻ መሆኑን ባየሁ ጊዜ፣ ነፍሴ እጅግ ስለ ጸናችና ስለ ተበረታታች፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ጌታን እንድጠራጠር አልተተውሁም ብቻ ሳይሆን፣ በከፋ ድህነት ውስጥ በነበርሁ ጊዜ እንኳ ተስፋ አልቈረጥሁም።»

ቀዳሚ ቀጣይ