ምዕራፍ 6 · 10 ደቂቃ ንባብ · 13 ደቂቃ ማዳመጥ
ሀብታችንንና ንብረታችንን በጥበብና በሃይማኖት የመጠቀምን ታላላቅ ግዴታዎችና ታላላቅ ጥቅሞች የሚገልጥ
የክርስትና ቅድስና የሕይወትን ሁኔታና ሥራ ሁሉ ለእግዚአብሔር እንደሚቀድስ፥ ሁሉንም ነገር እንደ እግዚአብሔር አገልጋዮች እያደረግንና እየተጠቀምን ፍጹም መታዘዝን እንድንሻ እንደሚጠይቀን፥ እንዲሁ ይህን ሃይማኖታዊ ጥንቃቄ በሀብታችንና በንብረታችን አጠቃቀም ለመጠበቅ ይበልጥ ግዴታ አለብን።
ሀብታችን እንደ ዓይኖቻችን ወይም እንደ እጆቻችን የእግዚአብሔር ስጦታ እንደ ሆነ፥ ዓይኖቻችንን እንደ ፈለግን ልናወጣ ወይም አካላችንን እንደ ወደድን ልንጥል እንደማይገባን ሁሉ እርሱንም እንደ ፈቀድን ልንቀብረው ወይም ልንጥለው እንደማይገባ ብቻ ብናስብ፥ የዚህ ምክንያት እጅግ ግልጽ ሆኖ በታየ ነበር።
ነገር ግን ከዚህ አሳብ በተጨማሪ በሀብታችን አጠቃቀም ሃይማኖታዊ ጥንቃቄ ልናደርግ የሚገባን ሌሎች ብዙ ታላላቅና አስፈላጊ ምክንያቶች አሉ።
አንደኛ፥ ገንዘባችንን የምንጠቀምበት ወይም ሀብታችንን የምናወጣበት መንገድ በየዕለቱ ሥራችን ውስጥ እጅግ ስለሚገባና የዕለት ኑሮአችንን ታላቅ ክፍል ስለሚይዝ፥ የዕለት ኑሮአችን ሀብታችንን ከምናወጣበት የተለመደ መንገዳችን ጋር በአብዛኛው አንድ ዓይነት መሆኑ የግድ ነው። በዚህ ነገር ምክንያትና ሃይማኖት ቢገዙን፥ ምክንያትና ሃይማኖት አጥብቀው ይዘውናል፤ ነገር ግን ሀብታችንን የምናወጣበት መለኪያ ስሜት፥ ትዕቢትና ምኞት ቢሆኑ፥ ስሜት፥ ትዕቢትና ምኞት የሕይወታችንን ታላቅ ክፍል ይመሩታል።
ሁለተኛ፥ ሀብታችንን ሁሉ ለትክክለኛ ጥቅም የምንሰጥበት ሌላው ታላቅ ምክንያት ይህ ነው፤ ለእጅግ መልካም ዓላማዎች ሊውል የሚችልና መልካም ለማድረግ እጅግ ታላቅ መሣሪያ ስለ ሆነ ነው። ብናባክነው ጥቂት ዋጋ ያለውን ኢምንት ነገር አናባክንም፤ ነገር ግን ለዕውር ዓይን፥ ለመበለት ባል፥ ለድሀ አደጉ አባት ሊሆን የሚችለውን እናባክናለን፤ በጭንቅ ላሉት ዓለማዊ መጽናናትን እንድናገለግል የሚያስችለንን ብቻ ሳይሆን በሰማይ ለራሳችን የዘላለም መዝገብ ሊገዛልን የሚችለውን እናባክናለን። ስለዚህ ገንዘባችንን በሞኝነት መንገድ ብንለቅቀው፥ ወገኖቻችንን የምናጽናናበትንና ራሳችንን ለዘላለም ብፁዓን የምናደርግበትን ታላቅ ኃይል እንለቅቃለን።
መልካም ከማድረግ የሚከብር ነገር ከሌለ፥ እግዚአብሔርን እንድንመስል የሚያደርገን እንደ እርሱ ያለ ነገር ከሌለ፥ እንግዲያስ በገንዘባችን አጠቃቀም ሁሉንም በፍቅርና በበጎነት ሥራ ከማዋል፥ ለወገኖቻችን ሁሉ ወዳጆችና አባቶች ረዳቶችም ራሳችንን ከማድረግ፥ መለኮታዊውን ፍቅር ከመምሰልና ኃይላችንን ሁሉ ለሚያስፈልጋቸው ወደ ልግስና፥ ወደ እንክብካቤና ወደ ቸርነት ሥራ ከመለወጥ የበለጠ የሚከብር ምንም ነገር ሊኖር አይችልም።
አንድ ሰው ለሚያጡት ሊሰጣቸው የሚችል ዓይኖች፥ እጆችና እግሮች ቢኖሩት፥ ዕውሮችና አንካሶች ለሆኑት ወንድሞቹ ከመስጠት ይልቅ በሣጥን ቢቈልፍባቸው ወይም በማያስፈልግና በሚያስቅ ጥቅም ራሱን ቢያስደስትባቸው፥ ጨካኝ ጐስቋላ ብለን በትክክል አንቈጥረውምን? ዓይንና እጅ ላጡት በመስጠት ለራሱ የዘላለም ዋጋ መብት ከማግኘት ይልቅ ቤቱን በእነዚያ ነገሮች በማስጌጥ ራሱን ማዝናናትን ቢመርጥ፥ እብድ ብለን በትክክል አንቈጥረውምን?
ገንዘብም የዓይንንና የእግርን ባሕርይ እጅግ ይመስላል፤ ድሆችና የተጨነቁ ለአስፈላጊ ፍላጎታቸው ሲሹት እኛ በሣጥን ብንቈልፍበት ወይም ለራሳችን በማያስፈልግና በሚያስቅ ወጪ ብናባክነው፥ ሌሎች ራቁታቸውን በረሀብ ሲያልቁ በሚያስቅ የልብስ ጌጥ ብንጨርሰው፥ ዓይንንና እጅን ለሚያጡት ከመስጠት ይልቅ ቤቱን በእነርሱ ማስጌጥን ከሚመርጥ ሰው ጭካኔ ብዙ አንርቅም። ገንዘባችንን በመልካም በማዋል ለራሳችን የዘላለም ዋጋ መብት ከማግኘት ይልቅ እውነተኛ ጥቅም በሌላቸው፥ እውነተኛ ፍላጎትን በማያረኩ ውድ ደስታዎች ራሳችንን ማስደሰትን ብንመርጥ፥ ዓይንንና እጅን ለሚያጡት በመስጠት ራሱን ለዘላለም ብፁዕ ከማድረግ ይልቅ መቈለፍን የሚመርጠውን ሰው እብደት እንካፈላለን። የራሳችንን ልከኛና ምክንያታዊ ፍላጎት ካረካን በኋላ የቀረው ገንዘባችን ሁሉ እንደ ትርፍ ዓይን ወይም እጅ ብቻ ነውና፤ በአጠቃቀሙ ሞኞች ሳንሆን ለራሳችን ልናስቀረው የማንችለው፥ ለሚያጡት በመስጠት ብቻ በመልካም ሊውል የሚችል ነገር ነው።
ሦስተኛ፥ ገንዘባችንን ብናባክን እግዚአብሔር የሰጠንን መክሊት በማባከን ብቻ አይደለም ጥፋተኞች የምንሆነው፥ መልካም ለማድረግ ያን ያህል ኃይለኛ መሣሪያ የሆነውን የማይጠቅም በማድረግ ብቻም አይደለም፤ ነገር ግን ይህን ጠቃሚ መክሊት ራሳችንን ለማበላሸት ወደ ኃይለኛ መሣሪያ በመለወጥ በራሳችን ላይ ተጨማሪ ጉዳት እናደርሳለን፤ በስሕተት በወጣበት መጠን በዚያው መጠን አንዳች ክፉ ዝንባሌን ለመደገፍ፥ ከንቱና ምክንያት የሌለውን ምኞት ለማርካት፥ እንደ ክርስቲያኖችና ምክንያታውያን ሰዎች ልንክዳቸው የሚገቡንን የዓለምን ልማዶችና ትዕቢት ለመከተል ይወጣልና።
ብልህነትና መልካም ተሰጥኦ ለመንፈሳዊነት በጥብቅ ካልተሰጡ በከንቱ ተበትነው ብቻ የሚጠፉ ሳይሆኑ ባለቤቶቻቸውን ወደ ታላቅ ሞኝነት እንደሚጥሉ፥ እንዲሁ ገንዘብም በምክንያትና በሃይማኖት መሠረት በጥብቅ ካልዋለ በከንቱ መበተን ብቻ ሳይሆን ሰዎችን ወደ ታላቅ ሞኝነት አሳልፎ ይሰጣቸዋል፤ ያለ እርሱ ሊኖሩ ከሚችሉት ይልቅም የባሰ ቂልና ልክ ያለፈ ሕይወት ያኖራቸዋል። ስለዚህ ገንዘባችሁን ለሌሎች መልካም በማድረግ ካላወጣችሁት ራሳችሁን ለመጉዳት ማውጣታችሁ አይቀርም። ራሱ ደሙን ሳያነድድ ሊጠጣው የማይችለውን ነገር ልብን የሚያበረታ መድኃኒት አድርጎ ለታመመ ወዳጁ ለመስጠት እንደሚከለክል ሰው ትሆናላችሁ። የትርፍ ገንዘብ ነገር እንዲህ ነውና፤ ለሚያጡት ብትሰጡት ልብን የሚያበረታ መድኃኒት ነው፤ ለማያስፈልጋችሁ ነገር ለራሳችሁ ብታወጡት ግን አእምሮአችሁን ያነድዳል ያውካልም፤ ያለ እርሱ ከምትሆኑት ይልቅም የባሳችሁ ያደርጋችኋል።
ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን ምሳሌ ደግሞ አስቡ፤ ትርፍ ዓይንንና እጅን በትክክል የማይጠቀም ሰው ራሱ ሊጠቀምባቸው ዘወትር በመሞከር የገዛ ዓይኑንና እጁን ቢያበላሽ፥ ከዚያ የሚበልጥ እብደት እንዳደረገ በትክክል ልንከሰው እንችላለን።
ለራሳችን በከንቱና በማያስፈልግ ወጪ የሚወጣ ሀብት ነገር በእውነት እንዲህ ነው፤ እውነተኛ ጥቅም በሌላቸውና እኛም እውነተኛ ፍላጎት በሌለን ቦታ ልንጠቀምባቸው ስንሞክር፥ ምክንያት የሌለውን ምኞት በመፍጠር፥ ክፉ ዝንባሌን በመመገብ፥ ስሜታችንን በማስደሰትና ዓለማዊና ከንቱ አስተሳሰብን በመደገፍ ለታላቅ ጉዳታችን ብቻ እንጠቀምባቸዋለን። ቅንጡ መብልና መጠጥ፥ ያማረ ልብስና ያማሩ ቤቶች፥ ግርማና ሠረገላ፥ ፈንጠዝያና መዝናኛዎች ሁሉ በተፈጥሮአቸው ልባችንን ይጎዳሉ ያውካሉምና፤ የባሕርያችን ሞኝነትና ድካም ሁሉ ምግብና መመገቢያ ናቸው፤ በዝንባሌዎቻችንም ከንቱና ዓለማውያን የሚያደርጉን የተረጋገጡ መንገዶች ናቸው። ሁሉም ሊደገፍ የማይገባውን ነገር የሚደግፉ ናቸው፤ መለኮታዊ ነገሮችን የሚያጣጥመውን የልብ ልከኝነትና መንፈሳዊነት ይቃወማሉ፤ አሳባችንንና ፍቅራችንን ወደ ላይ ወዳሉት ነገሮች ለማንሣት አቅማችንን የሚያሳንሱና ፈቃዳችንን የሚቀንሱ በአእምሮአችን ላይ እንዳሉ ብዙ ሸክሞች ናቸው።
ስለዚህ እንዲህ የወጣ ገንዘብ የባከነ ወይም የጠፋ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ለክፉ ዓላማና ለጐስቋላ ውጤት፥ ልባችንን ለማበላሸትና ለማወክ፥ የወንጌልንም ከፍ ያለ ትምህርት ተከትለን ለመኖር አቅማችንን ለማሳነስ የወጣ ነው። ለራሳችን መርዝ ለመግዛት ገንዘብን ከድሆች እንደ መከልከል ብቻ ነው።
በልብስ ከንቱነት የወጣው ያህል ከንቱነትን በአእምሮአችን ለመትከል የወጣ ተብሎ ሊቈጠር ይችላልና። ለሥራ ፈትነትና ለቅንጦት የወጣው ያህል ልባችንን ደንዛዛና ሥጋዊ ለማድረግ የተሰጠ ተብሎ ሊቈጠር ይችላል። ለግርማና ለሠረገላ የወጣው ያህል የገዛ ዓይናችሁን ለማደንዘዝና የገዛ ምናባችሁ ጣዖት ሊያደርጋችሁ የወጣ ተብሎ ሊቈጠር ይችላል። በሁሉም ነገር እንዲሁ ነው፤ ከምክንያታዊ ፍላጎት ስትወጡ መልካም ክርስቲያን ሁሉ እንዲክደው የተጠራበትን አንዳች ምክንያት የሌለው ዝንባሌ፥ አንዳች አስተሳሰብ ብቻ ትደግፋላችሁ።
ስለዚህ በሁሉም ረገድ፥ ሀብታችንን እንደ መክሊትና ከእግዚአብሔር እንደ ተሰጠ አደራ ብንመለከት፥ ወይም እንድናደርግ የሚያስችለንን ታላቅ መልካም ነገር፥ ወይም በከንቱ ቢወጣ በራሳችን ላይ የሚያደርሰውን ታላቅ ጉዳት ብንመለከት፥ በእነዚህ ሁሉ ታላላቅ ምክንያቶች ሀብታችንን ሁሉ ለመጠቀም ምክንያትንና ሃይማኖትን ጥብቅ ሕግ ማድረግ ፈጽሞ አስፈላጊ እንደ ሆነ ይታያል።
እግዚአብሔር እንዲረኩ የሚወድዳቸውን ፍላጎቶች ብቻ እያረካን ጠቢባንና ምክንያታውያን እንድንሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ያለ ምክር ሁሉ፥ የባሕርያችንን የከበረ ለውጥ እየተከተልን መንፈሳውያንና ሰማያውያን እንድንሆን ያለ ምክር ሁሉ፥ ባልንጀራችንን እንደ ራሳችን እንድንወድድ፥ እግዚአብሔር እንደ ወደዳቸው የሰውን ልጆች ሁሉ እንድንወድድ ያለ ምክር ሁሉ በገንዘባችን አጠቃቀም ጥብቅ ሃይማኖተኞች እንድንሆን የሚያዝ ትእዛዝ ነው። በሀብታችን ሁሉ አጠቃቀም ወንድማዊ ፍቅርንና እግዚአብሔርን የሚመስል ምጽዋትን እያሳየን ጠቢባንና ምክንያታውያን፥ መንፈሳውያንና ሰማያውያን ካልሆንን ከእነዚህ ዝንባሌዎች አንዱንም ልንፈጽም አንችልምና። እነዚህ ዝንባሌዎችና ይህ የዓለማዊ ሀብታችን አጠቃቀም የአዲስ ኪዳን ሁሉ ትምህርት ከመሆኑ የተነሣ ስለ እርሱ አንዳች ሳትማሩ አንድ ምዕራፍ እንኳ ማንበብ አትችሉም። ስለዚህ የሀብታችንን ሁሉ ሃይማኖታዊ አጠቃቀም በተመለከተ የተናገርሁትን ሁሉ ለማጽደቅ የሚበቃ አንድ ታላቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ብቻ አቀርባለሁ።
«የሰው ልጅ በክብሩ በሚመጣበት ጊዜ ከእርሱም ጋር ቅዱሳን መላእክቱ ሁሉ፥ በዚያን ጊዜ በክብሩ ዙፋን ይቀመጣል፤ አሕዛብም ሁሉ በፊቱ ይሰበሰባሉ፤ እረኛም በጎቹን ከፍየሎች እንደሚለይ እርስ በርሳቸው ይለያቸዋል፥ በጎችን በቀኙ ፍየሎችንም በግራው ያቆማቸዋል። ንጉሡም በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል። እናንተ የአባቴ ቡሩካን፥ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ። ተርቤ አብልታችሁኛልና፥ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛልና፥ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛልና፥ ታርዤ አልብሳችሁኛልና፥ ታምሜ ጠይቃችሁኛልና፥ ታስሬ ወደ እኔ መጥታችኋልና። . . . በዚያን ጊዜ በግራው ያሉትን ደግሞ ይላቸዋል። እናንተ ርጉማን፥ ለሰይጣንና ለመላእክቱ ወደ ተዘጋጀ ወደ ዘላለም እሳት ከእኔ ሂዱ። ተርቤ አላበላችሁኝምና፥ ተጠምቼ አላጠጣችሁኝምና፥ እንግዳ ሆኜ አልተቀበላችሁኝምና፥ ታርዤ አላለበሳችሁኝምና፥ ታምሜ ታስሬም አልጠየቃችሁኝምና። እነዚያም ወደ ዘላለም ቅጣት፥ ጻድቃን ግን ወደ ዘላለም ሕይወት ይሄዳሉ።» [ማቴዎስ 25፥31-46]
ይህን ክፍል በረጅሙ የጠቀስሁት የዓለምን መንገድ የሚመለከት ሰው ክርስቲያኖች ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ከቶ አንብበውት እንደ ሆነ ለማሰብ ስለሚያዳግተው ነው። በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ መዳናቸው በእነዚህ መልካም ሥራዎች ላይ የተመሠረተ የሚያስመስል ምን አለ? ነገር ግን የእነርሱ አስፈላጊነት እዚህ እጅግ ከፍ ባለ መንገድ ተረጋግጧል፤ የፍርድንም ቀን ክብርና ግርማ በሚያሳይ ሕያው መግለጫ በላያችን ተጭኖአል።
አንዳንድ ሰዎች፥ በጎ ምግባር ያላቸው ክርስቲያኖች ተብለው ሊቈጠሩ ከሚችሉትም እንኳ፥ ይህን ቃል አልፎ አልፎ ለሚደረግ የምጽዋት ሥራ እንደ ተሰጠ ጠቅላላ ምክር ብቻ ይመለከቱታል፤ ነገር ግን የሚያሳየው አልፎ አልፎ የሚደረገውን ምጽዋት አስፈላጊነት ብቻ ሳይሆን ልናደርገው የምንችለውን የምጽዋት ሥራ ሁሉ ያለማቋረጥ የሚለማመድ ፍጹም የምጽዋት ሕይወት አስፈላጊነትን ነው።
እነዚህን መልካም ሥራዎች ቸል ብትሉ የመዳን መብት እንደሌላችሁ ታምናላችሁ፤ ቸል ያሉአቸው ሰዎች በመጨረሻው ቀን በግራ ይቆማሉና፥ «እናንተ ርጉማን፥ ከእኔ ሂዱ» ተብለውም ይሰደዳሉና። ስለዚህ እነዚህን መልካም ሥራዎች ከመፈጸም በቀር መዳን የለም። እንግዲያስ እነዚህን መልካም ሥራዎች ፈጽሟል ሊባል የሚችል ማን ነው? አንድ ጊዜ እስረኛን የረዳ ወይም ድሀውን ወይም በሽተኛውን ያሳረፈ ነውን? ይህ አንድ ጊዜ የጸለየ ሰው የመሰጠትን ግዴታ ፈጽሟል እንደ ማለት የማይረባ ነው። እንግዲያስ እነዚህን የምጽዋት ሥራዎች ብዙ ጊዜ ያደረገ ነውን? ብዙ ጊዜ የፍትሕ ሥራ ያደረገ ሰው እውነተኛ ጻድቅ ሰው ነው ሊባል እንደማይችል ይህም ሊባል አይችልም። እንግዲያስ እነዚህን መልካም ሥራዎች የመፈጸም ሕግ ወይም መለኪያ ምንድር ነው? ሰው እንደሚገባ እንደሚፈጽማቸው እንዴት ሊተማመን ይችላል?
ሕጉም እጅግ ግልጽና ቀላል ነው፤ ለምጽዋት ብቻ ሳይሆን ለሌላው በጎ ምግባር ወይም መልካም ዝንባሌ ሁሉ የጋራ ነው። ትሑቱ፥ ወይም የዋሁ፥ ወይም ለእግዚአብሔር የተሰጠው፥ ወይም ጻድቁ፥ ወይም ታማኙ ሰው ማን ነው? ብዙ ጊዜ የትሕትና፥ የየዋህነት፥ የመሰጠት፥ የፍትሕ ወይም የታማኝነት ሥራ ያደረገ ነውን? አይደለም፤ ነገር ግን እነዚህን በጎ ምግባሮች ዘወትር እየተለማመደ የሚኖር ነው። እንደዚሁም እነዚህን የምጽዋት ሥራዎች ፈጽሟል ሊባል የሚችለው እስከ ኃይሉ ጥግ ድረስ ዘወትር እየተለማመዳቸው የሚኖር ብቻ ነው። የመለኮታዊ ፍቅርን ግዴታ የፈጸመ እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ በፍጹም አሳቡ በፍጹም ኃይሉም የሚወድድ ብቻ ነው። የእነዚህንም መልካም ሥራዎች ግዴታ የፈጸመ በፍጹም ልቡ በፍጹም አሳቡ በፍጹም ኃይሉም ያደረጋቸው ብቻ ነው። መልካም ለማድረግ ከኃይላችን በቀር ሌላ መለኪያ የለምና።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ብሩክ መድኃኒታችንን ይህን ጥያቄ ጠየቀው፤ «ጌታ ሆይ፥ ወንድሜ ቢበድለኝ ስንት ጊዜ ልተውለት? እስከ ሰባት ጊዜን? ኢየሱስ እንዲህ አለው። እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት እንጂ እስከ ሰባት ጊዜ አልልህም።» [ማቴዎስ 18፥21፣ 22] ይህ ከዚህ ቍጥር በደል በኋላ ሰው ይቅር ማለትን ሊተው ይችላል ማለት አይደለም፤ ነገር ግን ሰባ ጊዜ ሰባት የሚለው አባባል ይቅርታችንን በማናቸውም የበደል ቍጥር እንዳንወስን፥ ይልቁንም በእኛ ላይ እጅግ የተደጋገመውን በደል እንኳ ይቅር ማለትን እንድንቀጥል ሊያሳየን ነው። እንዲሁ መድኃኒታችን በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል፤ «በቀንም ሰባት ጊዜ እንኳ ቢበድልህ በቀንም ሰባት ጊዜ። ተጸጸትሁ እያለ ወደ አንተ ቢመለስ፥ ይቅር በለው።» [ሉቃስ 17፥4] እንግዲህ ሰው ወንድሙን ብዙ ጊዜ ይቅር ስላለው ይቅር ማለትን ቢተው፥ ሌሎችን ብዙ ሰዎች ይቅር ስላለ ይህን ሰው ይቅር ከማለት ራሱን ቢያገልል፥ እንዲህ ያለው ሰው ወንድምን ይቅር ስለ ማለት የተሰጠውን ይህን የክርስቶስ ሕግ ይጥሳል።
እንግዲህ የይቅርታ ሕግ የመስጠትም ሕግ ነው፤ ለሰባት ጊዜ ሳይሆን ለሰባ ጊዜ ሰባት ልትሰጡ ወይም መልካም ልታደርጉ ይገባችኋል። ለአንዱ ሰው ወይም ለሌሎች ሰዎች ብዙ ጊዜ ስለ ሰጣችሁ መስጠትን ልታቋርጡ አይገባችሁም፤ ነገር ግን አንድ ወይም ሁለት ጊዜ ልትረዱአቸው ግዴታ እንደ ነበረባችሁ፥ በችግር የሚቀጥሉትንም መርዳትን ልትቀጥሉ በዚያው መጠን ግዴታ እንዳለባችሁ ራሳችሁን ቍጠሩ። በእጃችሁ ባይሆን ኖሮ አንድን ሰው አንድ ጊዜ እንኳ ከመርዳት ነጻ በሆናችሁ ነበር፤ ነገር ግን ሰዎችን ብዙ ጊዜ መርዳት በእጃችሁ ቢሆን፥ አልፎ አልፎ ብቻ የሚችሉት ሌሎች አልፎ አልፎ ማድረጋቸው ግዴታቸው እንደ ሆነ፥ ብዙ ጊዜ ማድረግ የዚያኑ ያህል ግዴታችሁ ነው። ይቅርታ በሚያስፈልገው ቍጥር ወንድሙን ሁሉ ይቅር ለማለት ያልተዘጋጀ እንደ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር ይቅር አይልም። አንዳች ሊሰጠው የሚሻውን ወንድም ሁሉ ለመስጠት ያልተዘጋጀም እንደ ክርስቶስ ደቀ መዝሙር አይሰጥም። እስከ ሰባ ጊዜ ሰባት ይቅር ማለትና ለሚሻው ሁሉ ይህን ይቅር ባይ ዝንባሌ ዘወትር እየተለማመዱ መኖር አስፈላጊ እንደ ሆነ፥ ለሰባ ጊዜ ሰባት መስጠትና እስከ ኃይላችን ጥግ ድረስ መልካም ሥራዎችን ሁሉ ያለማቋረጥ እየተለማመዱ መኖርም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ ነውና።
የዚህ ሁሉ ምክንያት እጅግ ግልጽ ነው፤ በአንድ ጊዜ እንደ ሌላው ጊዜ እንዲህ መጽዋች የመሆን ያው በጎነት፥ ያው ብልጫ፥ ያው አስፈላጊነት አለና። በማናቸውም ጊዜ የገንዘባችን የተሻለ አጠቃቀም እንደ ሆነ ሁሉ ሁልጊዜ በእርሱ መልካም ማድረግም የተሻለ አጠቃቀሙ ነው፤ ስለዚህ ለአንድ የምጽዋት ሥራ ምክንያት የሆነው ለምጽዋት ሕይወትም እንደዚያው ያለ ምክንያት ነው። አንድን በደል ይቅር ለማለት ምክንያት የሆነው በደልን ሁሉ ይቅር ለማለትም ያው ምክንያት ነው። እንዲህ ያለ ምጽዋት ዛሬ የሚያስመሰግነው ነገም የሚያስመሰግነው ያው ነገር ብቻ ነውና፤ በሌላ ጊዜ ቸል እንዳላችሁት ያንኑ ኃጢአት ሳትሠሩ በአንድ ጊዜ ቸል ልትሉት አትችሉም።
ስለዚህ እነዚህ የምጽዋት ሥራዎች ለመዳን አስፈላጊ እንደ ሆኑ በእርግጥ፥ እንዲሁ እስከ ኃይላችን ጥግ ድረስ ልናደርጋቸው እንደሚገባን በእርግጥ ነው፤ ዛሬ ወይም ነገ ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ዘመን ሁሉ። ስለዚህ ለሚያጡት የምንሰጠው እንዲኖረን በማናቸውም ጊዜ ራሳችንን ከማያስፈልግ ወጪ መከልከል፥ ልከኞችና ቈጣቢዎች መሆን ግዴታችን ከሆነ፥ የበለጠ መልካም ለማድረግ እንድንችል ሁልጊዜ እንዲሁ ማድረግ የዚያኑ ያህል ግዴታችን ነው። በማናቸውም ጊዜ የማያስፈልገውንና ከንቱውን ወጪ ከምጽዋት ሥራ ማስበለጥ ኃጢአት ከሆነ ሁልጊዜም ኃጢአት ነውና፤ ምጽዋት ከማያስፈልገውና ከከንቱው ወጪ ሁሉ በአንድ ጊዜ እንደሚበልጥ በሌላ ጊዜም ይበልጣልና። ስለዚህ እነዚህን የምጽዋት ሥራዎች መጠንቀቅና በተወሰነ መጠን ልናደርጋቸው የምንችል መሆናችንን ማረጋገጥ መቼም ለመዳናችን አስፈላጊ ከሆነ፥ በሕይወታችን ክፍሎች ሁሉ ልናደርጋቸው እስከምንችለው ድረስ ብቁ እንድንሆን መጠንቀቅም የዚያኑ ያህል ለመዳናችን አስፈላጊ ነው።
ስለዚህ ወይ ከእነዚህ መልካም ሥራዎች አንዱንም ከቶ ማድረግ አያስፈልገኝም እስክትሉ ድረስ ክርስትናችሁን መካድ አለባችሁ፤ ወይም በሕይወታችሁ ሁሉ በምትችሉት እጅግ ከፍተኛ መጠን ልታደርጓቸው እንደሚገባችሁ ማመን አለባችሁ። በትዕቢትና በትሕትና፥ ወይም ራስን በመግዛትና ራስን ባለመግዛት መካከል መካከለኛ መንገድ እንደሌለ ሁሉ በዚህም የሚያዝ መካከለኛ መንገድ የለም። የምጽዋት ሥራዎችን ሁሉ ለመፈጸም ባትተጉ፥ በእጃችሁ ካሉት አንዱን ቸል ብትሉ፥ ልትሰጡት የምትችሉትን ለሚያጡት እርዳታ ብትከለክሉ፥ መቼም ይሁን የትም ይሁን፥ ራሳችሁን የክርስቲያን ምጽዋት ከጐደላቸው ጋር ትቈጥራላችሁ። በምትበሉትና በምትጠጡት ሁሉ ልከኞች መሆን ግዴታችሁ እንደ ሆነ፥ ባላችሁ ሁሉ መልካም ማድረግና በመልካም ሥራዎች ዘወትር እየተለማመዳችሁ መኖር የዚያኑ ያህል ግዴታችሁ ነውና።
ከዚህም የተነሣ የሰው ልጆች ትዕቢትና ሞኝነት በዓለም እንዲህ የተለመዱና የዘመኑ ልማድ ያደረጓቸውን እነዚያን የሞኝነትና ምክንያት የሌላቸውን ወጪዎች ሁሉ መተው አስፈላጊ እንደ ሆነ ደግሞ ይታያል። በምትችሉት መጠን መልካም ሥራ መሥራት አስፈላጊ ከሆነ፥ የምጽዋት ሥራ ለመሥራት የማትችሉ የሚያደርጓችሁን እነዚያን የማያስፈልጉ የገንዘብ ማውጫ መንገዶች መተውም የዚያኑ ያህል አስፈላጊ መሆን አለበትና።
ስለዚህ ለዓለም ክፋቶች ልትስማሙ እንደማይገባችሁ ለእነዚህ የዓለም መንገዶችም ልትስማሙ አይገባችሁም፤ ከሰካራሞች ጋር ልትጠጡ ወይም ከሆዳሞች ጋር ራሳችሁን ልታስደስቱ እንደማይገባችሁ፥ ስሜታቸው እንደ መራቸው ገንዘባቸውን በከንቱ ከሚያባክኑ ጋርም ልታወጡ አይገባችሁም፤ በመጠጥ ልክ ማለፍ ከልከኛ ሕይወት ጋር እንደማይስማማ እንዲህ ያለ የወጪ አካሄድም ከምጽዋት ሕይወት ጋር አይስማማምና። ስለዚህ ማንም ውድ ልብስ መልበስ እንደሚፈቀድ ወይም ራሳችሁን በውድ ደስታዎች ማስደሰት ነውር እንደሌለበት ቢነግራችሁ፥ ያው ሰው የምጽዋት ሥራ መሥራት አያስፈልጋችሁም፥ ክርስቶስም ለእርሱ እንደምታደርጉ ለድሆች ወንድሞቻችሁ መልካም እንድታደርጉ አይጠይቃችሁም ብሎ እንደሚነግራችሁ ብቻ አስቡ፤ ያን ጊዜ የእንዲህ ያለውን ምክር ክፋት ታያላችሁ። በመልካም ሥራዎች እየተለማመዳችሁ ለመኖር የማይቻላችሁ በሚያደርግ ወጪ ልትኖሩ እንደምትችሉ መንገር፥ ስለ እነዚያ መልካም ሥራዎች ራሳቸው ምንም ጥንቃቄ ማድረግ አያስፈልጋችሁም ብሎ ከመንገር ጋር አንድ ነውና።