ምዕራፍ 17 · 14 ደቂቃ ንባብ · 19 ደቂቃ ማዳመጥ
የዓለም አጠቃላይ መንፈስና ዝንባሌ የትሕትናን ልምምድ እንዴት አስቸጋሪ እንደሚያደርገው የሚያሳይ። ክርስትና ከዓለም በተቃራኒ እንድንኖር እንዴት እንደሚጠይቀን
ማንኛውም ሰው ይህን የትሕትና በጎ ምግባር ለመለማመድ በመጀመሪያ ራሱን ሲሰጥ፥ ቀደም ብዬ እንዳልሁት ራሱን እንደ ተማሪ ሊቈጥር ይገባዋል፤ ይኸውም ከቀድሞ የአእምሮው ዝንባሌዎችና ልማዶች ተቃራኒ የሆነውን፥ በዕለት ዕለትና በማያቋርጥ ልምምድ ብቻ የሚገኘውን ነገር የሚማር ነው።
አዲስ ጥበብ ወይም ዕውቀት እንደሚማር ሰው ብዙ የሚሠራው ነገር ያለው ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን ደግሞ የሚረሳው ብዙ ነገር አለው፤ ለረጅም ጊዜ ሲጸናና ሲቀረጽ የቆየውን የገዛ መንፈሱን ሊረሳና ሊተወው ይገባዋል፤ የዓለም ልማድ፥ ዝናና መንፈስ ለእርሱ ተፈጥሮአዊ ያደረጓቸውን እጅግ ብዙ ምኞቶችና አስተያየቶች ሊረሳና ከእነርሱ ሊለይ ይገባዋል።
የገዛ መንፈሱን ሊተው ይገባዋል፤ በኃጢአት እንደ ተወለድን እንዲሁ በትዕቢትም ተወልደናልና፤ ትዕቢትም እንደ ራስ ወዳድነት ለእኛ ተፈጥሮአዊ ነው፥ ዘወትርም ከእርሱ ይመነጫል። ክርስትና ብዙ ጊዜ እንደ አዲስ ልደትና እንደ አዲስ መንፈስ የሚገለጥበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው።
ከዓለም የተቀበላቸውን አስተያየቶችና ምኞቶች ሊተው ይገባዋል፤ የነገሮችን ዋጋ በትክክል ለመፍረድ ከመቻላችን በፊት እንደ ጐርፍ የወሰደን የዓለም ዝናና ልማድ በብዙ መንገድ የትሕትና ተቃራኒ ነውና፤ ስለዚህ በትሕትና መንፈስ ልንመራ ከመቻላችን በፊት የዓለም መንፈስ ያስተማረንን ልንረሳ ይገባናል።
ዲያብሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ የዚህ ዓለም ገዥ ተብሎ ይጠራል፤ በዓለም ውስጥ ታላቅ ኃይል አለውና፥ ብዙዎቹ የዓለም ደንቦችና መሠረታውያን ሕጎች ከእግዚአብሔር ሊለዩንና ወደ ደስታ እንዳንመለስ ሊከለክሉን በዚህ ክፉ መንፈስ፥ በውሸትና በሐሰት ሁሉ አባት፥ የተፈጠሩ ናቸውና።
እንግዲህ ሁላችንም የተበላሸ አየሩን በተነፈስነው በዚህ ዓለም መንፈስና ዝና መሠረት ታላቅና የተከበረ፥ እጅግም የሚወደድ ተደርገው የሚቈጠሩ ብዙ ነገሮች አሉ፤ ነገር ግን እነርሱ እንዲህ ከመሆን እጅግ የራቁ ናቸው፤ የባሕርያችን እውነተኛ ታላቅነትና ክብር እነርሱን ባለመመኘት ነውና።
በሀብት መትረፍረፍ፥ ያማሩ ቤቶችና ውድ ልብሶች እንዲኖሩን፥ በድምቀትና በሠረገላ መታጀብ፥ በመልካችን ውብ መሆን፥ የማዕረግ ስሞች እንዲኖሩን፥ ከወገኖቻችን በላይ መሆን፥ የሌሎች ሰዎችን ስግደትና እጅ መንሣት ማዘዝ፥ በአድናቆት መታየት፥ ጠላቶቻችንን በኃይል ማሸነፍ፥ የሚቃወሙንን ሁሉ ማስገዛት፥ በምንችለው ድምቀት ሁሉ ራሳችንን ማሳየት፥ በከፍተኛ ኑሮና በግርማ መኖር፥ እጅግ ውድ በሆነ መንገድ መብላት፥ መጠጣትና ራሳችንን ማስደሰት፤ እነዚህ የዓለም መንፈስ የሰዎችን ሁሉ ዓይን የሚያዞርባቸው ታላላቅ፥ የተከበሩና የሚወደዱ ነገሮች ናቸው። ብዙ ሰውም ያው ዓለም ሞኝ አድርጎ እንዳይቈጥረው ፈርቶ ዝም ብሎ ለመቆምና እነዚህን ነገሮች ከመከተል ለመራቅ ይፈራል።
የወንጌል ታሪክ በዋናነት ክርስቶስ በዓለም መንፈስ ላይ ያገኘው ድል ታሪክ ነው። የእውነተኛ ክርስቲያኖች ቍጥርም የክርስቶስን መንፈስ ተከትለው ከዚህ የዓለም መንፈስ በተቃራኒ የኖሩት ሰዎች ቍጥር ብቻ ነው።
«የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።» ደግሞም፦ «ከእግዚአብሔር የተወለደ ሁሉ ዓለምን ያሸንፋልና።» «በላይ ያለውን አስቡ እንጂ በምድር ያለውን አይደለም። ሞታችኋልና፥ ሕይወታችሁም በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአልና።» [ሮሜ 8፥9፤ 1ኛ ዮሐንስ 5፥4፤ ቆላስይስ 3፥2, 3] የአዲስ ኪዳን ሁሉ ቋንቋ ይህ ነው፤ የክርስትና ምልክት ይህ ነው፤ ሞታችሁ ልትኖሩ ይገባችኋል፤ ይኸውም ለዓለም መንፈስና ዝንባሌ ሞታችሁ በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ አዲስ ሕይወት ልትኖሩ ይገባችኋል።
ነገር ግን ዓለምን እንዲህ የሚክዱት እነዚህ ትምህርቶች ግልጥና ቀላል ቢሆኑም፥ ብዙዎቹ ክርስቲያኖች ለዓለም ልማዶችና ዝንባሌ ባሪያዎች ሆነው ይኖራሉ፥ ይሞታሉም።
በዓለም ስለሚደነቁ ብቻ እንጂ ፈጽሞ ዋጋ ሊሰጧቸው በማያውቋቸው ነገሮች ምክንያት ስንት ሰዎች በትዕቢትና በከንቱነት ይታበያሉ!
ዓለም ከሁሉ ይልቅ በስድስት ፈረሶች የሚሳብ ሠረገላን እንደሚያደንቅ ባያውቅ ኖሮ፥ በሠረገላው ላይ ሁለት ፈረሶችን ለመጨመር ሰው ዐሥር ተጨማሪ ዓመታት በሥራ ይደክም ነበርን? ዓለም ከምንም እንዳይቈጥራቸውና ከተዋረዱና ከወራዳ ሰዎች ጋር እንዳይመድባቸው በሚል በዚህ ምክንያት ብቻ ብዙ ሰዎች ቤታቸው በድህነት የተዘጋጀ ወይም ራሳቸው የተናቀ ልብስ የለበሱ እንዳይሆኑ ምንኛ ይፈራሉ!
በዓለም አስተያየት እንዲህ ያለ ደካማ መንፈስ ያለው ሰው ተደርጎ ለመቈጠር ባይፈራ ኖሮ፥ ሰው ለሌሎች ትዕቢትና ክፉ ጠባይ ስንት ጊዜ እሺ ባለና የሚገዛ ዝንባሌ ባሳየ ነበር!
ብዙ ሰው ቢያደርገው ዓለም ይቅር እንደማይለው ባይፈራ ኖሮ፥ ብዙ ጊዜ ቂሙን በተወና ስድብን ይቅር ባለ ነበር።
ዓለም በእንዲህ ያለ ሕይወት ላይ የሚሰጠው ነቀፋ ባይኖር ኖሮ፥ ስንቶች የክርስትናን ራስን መግዛትና ልከኝነት በፍጹምነቱ ጫፍ ይለማመዱ ነበር!
ሌሎች እንደ ክርስትና ፍጹምነት ደንቦች ለመኖር ብዙ ጊዜ ያስባሉ፤ ነገር ግን ዓለም ስለ እነርሱ ምን እንደሚል በማሰብ ከዚህ ይሸበራሉ።
በዓለም ከመኖራችን የተቀበልናቸው ስሜቶች አእምሮአችንን እንዲሁ ባሪያ ያደርጉታል፤ በዓለም ዓይን ትንሽ እንዳንሆን በመፍራት በእግዚአብሔርና በቅዱሳን መላእክት ፊት የላቅን ለመሆን አንደፍርም።
የትሕትና ታላቁ ችግር የሚነሣው ከዚህ ወገን ነው፤ ትሕትና ለዓለም በሞተና የዓለምን ታላቅነትና ክብር የመደሰትን ምኞት ሁሉ በተወ መጠን ብቻ እንጂ በማንኛውም አእምሮ ውስጥ ሊኖር አይችልምና። ስለዚህ በእውነት ትሑት ለመሆን፥ በሕይወትህ ዘመን ሁሉ ከዚህ ከተበላሸው የዓለም መንፈስ ስትማራቸው የኖርሃቸውን እነዚያን አሳቦች ሁሉ ልትረሳ ይገባሃል።
የዓለምን ኃይል በአንተ ላይ እስክታቆምና ለሕጎቹ ዕውር መታዘዝን ለመቃወም እስክትወስን ድረስ፥ የትዕቢትን ጥቃቶች ልትቋቋም አትችልም፤ የትሕትና የዋህ ስሜቶችም በነፍስህ ውስጥ ስፍራ ሊያገኙ አይችሉም።
በዓለማዊ ልማዶችና አስተያየቶች ጐርፍ ውስጥ ጸንተህ ለመቆምና በዓለም እጅግ የሚደነቁትንና የሚከበሩትን ነገሮች ዋጋና ጥቅም ለመመርመር እስክትችል ድረስ አንድ ጊዜ ከተራመድህ ግን፥ ነጻነትህን በማግኘት ረጅም መንገድ ሄደሃል፥ ለልብህም መታረም መልካም መሠረት ጥለሃል።
የዓለም ኃይል ምንም ያህል ታላቅ ቢሆን ሁሉም በዕውር መታዘዝ ላይ የተሠራ ነውና፤ ከኃይሉም ለመላቀቅ ዓይኖቻችንን መክፈት ብቻ ያስፈልገናል።
የተማረም ይሁን ያልተማረ የፈለግኸውን ጠይቅ፤ የዓለም አጠቃላይ ዝንባሌና መንፈስ ከፈቃድ፥ ከሞኝነትና ከመረን መልቀቅ በቀር ሌላ ምንም እንዳልሆነ ሁሉም የሚያውቅና የሚያምን ይመስላል።
የፍልስፍና ጥበብና የሃይማኖት መንፈሳዊነት ሁልጊዜ በጥቂት ሰዎች ብቻ የተወሰኑ እንደ ነበሩ የማይቀበል ማን ነው? ይህስ የዓለም የተለመደው መንፈስና ዝንባሌ በፍልስፍና ጥበብም በሃይማኖት መንፈሳዊነትም መሠረት እንዳልሆነ በግልጥ መቀበልና ማመን አይደለምን?
ስለዚህ የሚያስብ ሰው ተመሳሳይ ፍርድ እንዲኖረው እጅግ ቀላል እስኪሆን ድረስ ዓለም በራሱ እንኳ በበቂ የተፈረደበት ይመስላል።
ስለዚህ ትሑት ለመሆን ለሽቅርቅሮችና ለተሽቀርቃሪ ሴቶች ሕግ ከሚሰጠው ከዚያ ተራ መንፈስ መታዘዝህን ልታስወግድና ፍርድህን በፍልስፍና ጥበብና በሃይማኖት መንፈሳዊነት መሠረት ልትቀርጽ ይገባሃል ማለቴን ከባድ ንግግር አድርገህ እንደማትቈጥረው ተስፋ አደርጋለሁ። እንዲህ ያለውን ለውጥ ለማድረግ ማን ይፈራል?
ደግሞም፥ ለዓለም አስተያየት ያለህን ፍርሃትና ግምት ለመቀነስ ዓለም ምን ያህል ፈጥኖ ቸል እንደሚልህ፥ በጕድጓድ ውስጥ ከሞተው እጅግ ምስኪን እንስሳ የበለጠ ስለ አንተ ምንም አሳብና ግድ እንደማይኖረው አስብ።
ወዳጆችህ ቢችሉ በተወሰነ ክብር ይቀብሩህ ይሆናል፥ ትውልድም ዐፈርህ ከእንዲህ ያለ ድንጋይ በታች እንደ ተኛ እንዲያይ የመታሰቢያ ሐውልት ያቆሙ ይሆናል፤ ይህ ከተፈጸመ በኋላ ሁሉ ተፈጸመ። ስፍራህ በሌላ ይሞላል፥ ዓለም በፊት እንደ ነበረ በዚያው ሁኔታ ነው፥ አንተ ከዓይኑ ተደምስሰሃል፥ ከቶ የእርሱ እንዳልነበርህ ያህልም በዓለም ተረስተሃል።
ታላቅ ስም ያተረፉትንና በዓለም ዘንድ በከፍተኛ ግምት የነበሩትን ባለ ጠጎች፥ ታላላቆችና የተማሩ ሰዎች አስብ፤ ብዙዎቹ በዘመንህ ሞተዋል፤ ነገር ግን ሰጥመዋል፥ ጠፍተዋል፥ ሄደዋልም፤ ብዙ የውኃ አረፋዎች ብቻ እንደ ነበሩ ያህልም ዓለም ቸል ብሎአቸዋል።
ደግሞም ያለ እነርሱ ልክ እንደ ቀድሞው ደህና እንደ ሆነ ለሚያስብና እነርሱ በውስጡ በነበሩ ጊዜ እንደ ነበረው ዛሬም ደስ ለሚለው ዓለም ስላቀረቡት አገልግሎትና አክብሮት፥ ስንት ምስኪን ነፍሳት መንግሥተ ሰማያትን አጥተው አሁን የጐስቋላ ዘላለምን እየጠበቁ እንደ ተኙ አስብ።
እንግዲህ እንደ ዓለም ያለውን እንዲህ ያለውን ክፉ ጌታና ሐሰተኛ ወዳጅ ደስ ለማሰኘት ብለህ ከበጎ ምግባር ትንሹን ደረጃ እንኳ ማጣት ይገባሃልን?
ባሪያዎቹን ሁሉ የገዛ ዘላለማዊነቱ ተካፋዮች የሚያደርገውን ያንን ታላቅ፥ ቅዱስና ኃያል እግዚአብሔርን ከማገልገል ይልቅ፥ እንዲህ ፈጥኖ አንተን የሚመለከትበት ዓይንም፥ ጆሮም፥ ልብም ለማይኖረው እንደዚህ ላለ ጣዖት መንበርከክ ይገባሃልን?
ለአንተ ምንም ፍቅር የሌለው የሐሰተኛ ዓለም ፍርሃት፥ ለዘላለም ሊወድድህና ሊባርክህ ብቻ ከፈጠረህ ከዚያ እግዚአብሔር ፍርሃት እንዲከለክልህ ትፈቅዳለህን?
በመጨረሻም፥ የክርስትና ቃል ኪዳን ዓለምን በተመለከተ ከአንተ ምን ዓይነት አካሄድ እንደሚጠይቅ ልታስብ ይገባሃል።
ይህም በእነዚህ ቃላት በግልጥ ተነግሮአል፦ «ክፉ ከሆነ ከአሁኑ ዓለም ያድነን ዘንድ ስለ ኃጢአታችን ራሱን ሰጠ።» [ገላትያ 1፥4] ስለዚህ ክርስትና ከዚህ ዓለም መዳንን ያመለክታል፤ ክርስትናን የሚቀበልም ለዚህ ክፉ ዓለም ልዩ ከሆነው ነገር ሁሉና ከዝንባሌ ሁሉ በተቃራኒ ለመኖር ቃል ይገባል።
ቅዱስ ዮሐንስ ይህን ከዓለም ጋር ያለውን ተቃውሞ እንዲህ ብሎ ይገልጣል፦ «እነርሱ ከዓለም ናቸው፤ ስለዚህ ከዓለም የሆነውን ይናገራሉ ዓለሙም ይሰማቸዋል። እኛ ከእግዚአብሔር ነን።» [1ኛ ዮሐንስ 4፥5, 6] የክርስቶስ ተከታዮች መግለጫ ይህ ነው፤ በልባቸውና በዝንባሌአቸው የዚህ ዓለም የሆኑ ሰዎች በእውነት ክርስቲያኖች ተብለው ሊቈጠሩ እንደማይገባ ይህ በቂ ማስረጃ ነው። ያው ሐዋርያ «ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን» ይላል። [1ኛ ዮሐንስ 5፥19] ስለዚህ ክርስቲያኖች የዓለም እንዳልሆኑ፥ ማለትም እንደ ዓለም መንገድና መንፈስ እንደማይኖሩ በሚያውቁት መጠን ብቻ እንጂ ከእግዚአብሔር እንደ ሆኑ ሊያውቁ አይችሉም። የዓለም መንገዶች፥ መርሖዎች፥ ፖለቲካና ዝንባሌዎች ሁሉ በክፉ ተይዘዋልና። ከእግዚአብሔር የሆነ፥ ወይም በክርስቶስ ኢየሱስ ከእግዚአብሔር የተወለደ፥ ይህን ዓለም ያሸነፈ ብቻ ነው፤ ይኸውም በእምነት ለመኖርና ተግባሩን ከእግዚአብሔር በክርስቶስ ኢየሱስ በተገለጠ ጥበብ መሠረታውያን ሕጎች ለመምራት የመረጠ ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ ክርስቲያኖች ከእንግዲህ በዚህ ዓለም እንደሚኖሩ ሊቈጠሩ እንደማይገባ ለክርስቲያኖች በሚገባ የታወቀ እርግጥ ነገር አድርጎ ይወስደዋል፤ ስለዚህም የአይሁድን ሕግ ሥርዓቶች ስለ መሻር ከማይካድ መሠረታዊ ሕግ እንደሚነሣ ሆኖ እንዲህ ይከራከራል፦ «ከክርስቶስ ጋር ለዓለም መጀመሪያ ትምህርት ከሞታችሁ፥ በዓለም እንደምትኖሩ ስለ ምን ለትእዛዛት ትገዛላችሁ?» [ቆላስይስ 2፥20]። ክርስቲያኖች የእምነት ቃላቸው የዓለምን ዝንባሌዎችና ምኞቶች ሁሉ እንዲተዉ፥ እንደ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ዜጎች እንዲኖሩና ኑሮአቸው በሰማይ እንዲሆን እንደሚጠይቃቸው ያውቁ እንደ ነበር ሐዋርያው የማይካድ አድርጎ ባይወስደው ኖሮ በዚህ ውስጥ ምንም ክርክር ባልኖረ ነበር።
ብሩክ ጌታችን ራሱ ይህን ጕዳይ በእነዚህ ቃላት ፈጽሞ ወስኖታል፦ «እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም።» [ዮሐንስ 17፥16] ክርስትና ከዚህ ዓለም ጋር ያለው ሁኔታ ይህ ነው። እንዲህ ከዓለም ውጭና የዓለም ተቃራኒ ካልሆንህ፥ የክርስትና መለያ ምልክት ይጐድልሃል፤ እርሱ ከዓለም ውጭ እንደ ነበረ ከዓለም ውጭ በመሆን ካልሆነ በቀር የክርስቶስ አይደለህም።
ብንፈልግ በእነዚህ ቃላት ላይ በሚሰጡ ከንቱና አለዝበው በሚያቀርቡ ትርጓሜዎች ራሳችንን ልናታልል እንችላለን፤ ነገር ግን ብሩክ ጌታችን በተናገራቸው በዚያው መንፈስ በሚያነባቸው ሁሉ በመጀመሪያ ቀላልነታቸውና ግልጽነታቸው ይረዳሉ፥ ወደ ፊትም ይረዳሉ። በማንኛውም ዝቅ ባለና ትርጉሙ ባነሰ መንገድ መረዳታቸውም ሥጋዊ ጥበብ ራሱ የሚጠፋበትን ያንን ትምህርት ተርጕሞ እንዲያስወግደው መፍቀድ ነው።
ክርስቲያን በዓለም ላይ ያለው ታላቅ ድል ሁሉ በመስቀል ላይ ባለው በክርስቶስ ምሥጢር ውስጥ ይገኛል። ክርስቲያኖች ሁሉ እንዴት ከዓለም ወጥተው እንደሚያሸንፉት፥ ደቀ መዛሙርቱም ለመሆን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ያስተማራቸው በዚያ፥ ከዚያም ነው። የወንጌልም ትምህርቶች፥ ምሥጢራትና ሥርዓቶች ሁሉ የዚህ ታላቅ ምሥጢር ትርጉም ማብራሪያዎችና የጥቅሙ ተግባራዊ መግለጫዎች ብቻ ናቸው።
የክርስትና ሁኔታም ክርስቶስ በመስቀል ላይ ራሱን በሠዋበት ምሥጢራዊ መሥዋዕት ላሳየው መንፈስ ሙሉና ፍጹም መምሰልን እንጂ ሌላ ምንም አያመለክትም።
ስለዚህ ማንኛውም ሰው ከዚህ የክርስቶስ መንፈስ በሚካፈለው መጠን ብቻ ክርስቲያን ነው። ቅዱስ ጳውሎስን እንዲህ በጽኑ ስሜት እንዲናገር ያደረገው ይህ ነው፦ «ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ»፤ ነገር ግን ስለ ምን ይመካል? ክርስቶስ በእርሱ ፋንታ መከራ ስለ ተቀበለና ከመከራ ነጻ ስላደረገው ነውን? አይደለም፥ በፍጹም። ነገር ግን የክርስትና ቃል ኪዳኑ ክርስቶስ በመስቀል ላይ እንዳደረገው ከክርስቶስ ጋር መከራ ወደ መቀበል ክብርና በነቀፋና በንቀት ለዓለም ወደ መሞት ስለ ጠራው ነው። ወዲያውም «ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት» ብሎ ይጨምራልና። [ገላትያ 6፥14] እንግዲህ እንደምታየው፥ በክርስቶስ መስቀል የሚመካበት ምክንያት ይህ ነበር፤ ለዓለም ወደሚመሳሰል የሞትና የመሰቀል ሁኔታ ጠርቶታልና።
እንግዲህ በቅዱስ ጳውሎስ ዘመን የክርስቶስ መስቀል የክርስቲያኖች ክብር ነበር፤ የተሰቀለውን ጌታ ለማመን አለማፈራቸውን ስለሚያመለክት አይደለም፤ ነገር ግን ከመስቀል ትምህርት በቀር ሌላ ባልሆነ ሃይማኖት መመካታቸውን ስለሚያመለክት ነው፤ ይህም ሃይማኖት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ወዳሳየው ወደዚያው መከራን የሚቀበል መንፈስ፥ ወደዚያው ራስን መሠዋት፥ ወደዚያው ዓለምን መካድ፥ ወደዚያው ትሕትናና የዋህነት፥ ጉዳትን፥ ነቀፋንና ንቀትን በትዕግሥት ወደ መሸከም፥ ለዚህም ዓለም ታላቅነት፥ ክብርና ደስታ ሁሉ ወደ መሞት የጠራቸው ነው።
ስለ ክርስትና እውነተኛ ግንዛቤ እንዲኖረን፥ ብሩክ ጌታችንን በእኛ ፋንታ መከራ እንደ ተቀበለ አድርገን ልንቈጥረው አይገባም፤ ነገር ግን በስማችን እንደሚሠራ ወኪላችን፥ ከእርሱ ጋር መተባበራችንን በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ የሚያደርግ ልዩ ብቃትም እንዳለው አድርገን ልንቈጥረው ይገባናል።
መከራችንና ራሳችንን መሠዋታችን በእግዚአብሔር ለመቀበል የተገባ እንዲሆን እርሱ መከራን ተቀበለ፥ መሥዋዕትም ሆነ። እኛም ከክርስቶስ ጋር መከራ ልንቀበል፥ ልንሰቀል፥ ልንሞትና ልንነሣ ይገባናል፤ አለዚያ መሰቀሉ፥ ሞቱና ትንሣኤው አንዳች አይጠቅመንም።
ክርስቶስ ስለ እኛ ያደረገውንና መከራ የተቀበለበትን ሁሉ የመምሰል አስፈላጊነት ከመጽሐፍ ቅዱስ አጠቃላይ ቃል እጅግ ግልጥ ነው።
በመጀመሪያ፥ ስለ መከራው፦ በእርሱ ለመዳናችን ያለው ብቸኛው ቅድመ ሁኔታ ይህ ነው፤ ከእርሱ ጋር «ብንጸና፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ እንነግሣለን።» [2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥12]
ሁለተኛ፥ ስለ መሰቀሉ፦ «አሮጌው ሰዋችን ከእርሱ ጋር እንደ ተሰቀለ እናውቃለን» [ሮሜ 6፥6 ወዘተ] እዚህ ክርስቶስ በእኛ ፋንታ እንዳልተሰቀለ ታያለህ፤ ነገር ግን አሮጌው ሰዋችን በእውነት ከእርሱ ጋር ካልተሰቀለ፥ የክርስቶስ መስቀል አንዳች አይጠቅመንም።
ሦስተኛ፥ ስለ ክርስቶስ ሞት ቅድመ ሁኔታው ይህ ነው፦ «ከእርሱ ጋር ከሞትን፥ ከእርሱ ጋር ደግሞ በሕይወት እንኖራለን» ብለን እናምናለን። [2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥11] ስለዚህ ክርስቶስ ብቻውን ቢሞት፥ እኛ ከእርሱ ጋር ካልሞትን፥ ከእርሱ ጋር በሕይወት እንደማንኖር ከዚህ መጽሐፍ በእርግጥ እናውቃለን።
በመጨረሻም፥ ስለ ክርስቶስ ትንሣኤ መጽሐፍ ቅዱስ ከጥቅሙ እንዴት እንደምንካፈል ያሳየናል፦ «እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችሁ፥ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ።» [ቆላስይስ 3፥1]
እንግዲህ መጽሐፍ ቅዱስ ብሩክ ጌታችንን በስማችን እንደሚሠራና መከራ እንደሚቀበል ወኪላችን፥ ስለ እኛ ያደረገውንና መከራ የተቀበለበትን ሁሉ እንድንመስል እንደሚያስገድደን አድርጎ ምን ያህል በግልጥ እንደሚያቀርበው ታያለህ።
ቅዱሱ ኢየሱስ ስለ ደቀ መዛሙርቱ፥ በእነርሱም ስለ እውነተኛ አማኞች ሁሉ «እኔ ከዓለም እንዳይደለሁ ከዓለም አይደሉም» ያለው ስለዚህ ምክንያት ነበር። [ዮሐንስ 17፥14] እውነተኛ አማኞች ሁሉ የክርስቶስን መከራ፥ መሰቀል፥ ሞትና ትንሣኤ በመምሰል ከእንግዲህ እንደዚህ ዓለም መንፈስና ዝንባሌ አይኖሩምና፤ ነገር ግን ሕይወታቸው በእግዚአብሔር ከክርስቶስ ጋር ተሰውሮአል።
ሁሉም ዓይነት ክርስቲያኖች የተጠሩበት ከዓለም የመለየት ሁኔታ ይህ ነው። በእውነትና በርግጥ ከክርስቶስ ጋር እንደ ተሰቀሉ፥ እንደ ሞቱና እንደ ተነሡ እስኪያሳዩ ድረስ ዓለማዊ ዝንባሌዎችን ሁሉ ሊክዱ፥ በሌላውም ሕይወት ነገሮች ሊመሩ ይገባቸዋል። ክርስቶስ ለመዳናችን መከራ ሊቀበል፥ ሊሞትና ሊነሣ አስፈላጊ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ ክርስቲያኖች ሁሉ ይህን ታላቅ የመንፈስ ለውጥ እንዲመስሉ፥ እንዲህም በክርስቶስ አዲስ ፍጥረት እንዲሆኑ አስፈላጊ ነው።
የክርስትና ሕይወት ከዚህ ዓለም መንገዶች በላይ ምን ያህል ከፍ ብሎ እንደ ተቀመጠ ቅዱስ ጳውሎስ በእነዚህ ቃላት በሚያስደንቅ ሁኔታ ገልጦታል፦ «ስለዚህ እኛ ከአሁን ጀምሮ ማንንም በሥጋ እንደሚሆን አናውቅም፤ ክርስቶስንም በሥጋ እንደ ሆነ ያወቅነው ብንሆን እንኳ፥ አሁን ግን ከእንግዲህ ወዲህ እንደዚህ አናውቀውም። ስለዚህ ማንም በክርስቶስ ቢሆን አዲስ ፍጥረት ነው፤ አሮጌው ነገር አልፎአል፤ እነሆ፥ ሁሉም አዲስ ሆኖአል።» [2ኛ ቆሮንቶስ 5፥16, 17]
የእነዚህን ቃላት ኃይልና መንፈስ የሚሰማው ሰው ማንኛውንም ሰዋዊ ትርጓሜ ሊታገሥ አይችልም። ከአሁን ጀምሮ ይላል፤ ይኸውም ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ወዲህ የክርስትና ሁኔታ እጅግ የከበረ ሁኔታ ሆኖአል፤ ስለዚህ ክርስቶስን ራሱን እንኳ በምድር ላይ በሥጋ እንዳለ አድርገን አንቈጥረውም፥ ነገር ግን በሰማይ እንዳለ የክብር አምላክ እንቈጥረዋለን፤ ራሳችንንም በሥጋ እንዳሉ ሰዎች ሳይሆን ልባችንን ሁሉ፥ ዝንባሌዎቻችንንና ኑሮአችንን በሰማይ ሊያደርጉ እንደሚገባቸው የአዲስ ማኅበር ብልቶች አድርገን እናውቃለን፥ እንቈጥራለንም።
ክርስትና ከዓለም ውጭና ከዓለም በላይ ያስቀመጠን እንዲህ ነው፤ በዓለም ዝንባሌዎች ውስጥ እንደ ወደቅን ወዲያውኑ ከጥሪያችን እንወድቃለን።
እንግዲህ ብሩክ ጌታችንን በመስቀል ላይ የቸነከረው የዓለም መንፈስ እንደ ነበረ፥ እንዲሁ የክርስቶስ መንፈስ ያለውና እርሱ እንዳደረገው ዓለምን የሚቃወም ሰው ሁሉ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ በእርግጥ በዓለም ይሰቀላል።
ክርስትና ክርስቶስ በኖረበት በዚያው ዓለም አሁንም ይኖራልና፤ እነዚህ ሁለቱም የጨለማው መንግሥት ፈጽሞ እስኪያከትም ድረስ ፍጹም ጠላቶች ይሆናሉ።
ከመድኃኒታችን ጋር እንደ እውነተኛ ደቀ መዝሙሩ ኖረህ ቢሆን ኖሮ፥ እርሱ እንደ ተጠላ አንተም ትጠላ ነበር፤ አሁንም በመንፈሱ ብትኖር፥ ዓለም በዚያን ጊዜ ለእርሱ እንደ ነበረው አሁን ለአንተ ያው ጠላት ይሆናል።
ብሩክ ጌታችን «ከዓለምስ ብትሆኑ ዓለም የራሱ የሆነውን ይወድ ነበር፤ ነገር ግን እኔ ከዓለም መረጥኋችሁ እንጂ ከዓለም ስለ አይደላችሁ ስለዚህ ዓለም ይጠላችኋል» ይላል። [ዮሐንስ 15፥19]
እነዚህን ቃላት በዚያን ጊዜ የመድኃኒታችንና የደቀ መዛሙርቱ ሁኔታ የነበረውን ነገር የሚገልጡ ታሪካዊ መግለጫ ብቻ አድርገን በመቍጠር እውነተኛ ትርጉማቸውን ልናጣ እንችላለን። ነገር ግን ይህ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ሙት ፊደል ማንበብ ነው፤ እነርሱ በዚህ ዘመንና በሌሎችም ዘመናት ሁሉ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የእውነተኛ ክርስቲያኖችን ሁኔታ በትክክል ይገልጣሉና።
እውነተኛ ክርስትና ከክርስቶስ መንፈስ በቀር ሌላ ምንም እንዳልሆነ፥ እንዲሁ ያ መንፈስ በክርስቶስ ራሱ ወይም በሐዋርያቱ ወይም በማንኛውም ዘመን ባሉ ተከታዮቹ ቢገለጥ አንድ ነገር ነው፤ መንፈሱ ያለው ሁሉ እርሱ እንደ ተጠላ በዓለም ይጠላል፥ ይናቃል፥ ይፈረድበታልም።
ዓለም ሁልጊዜ የራሱን ይወዳልና፥ ከራሱም በቀር ማንንም አይወድም፤ ይህ እንደ ብርሃንና እንደ ጨለማ ተቃራኒነት እርግጥና የማይለወጥ ነው።
ቅዱሱ ኢየሱስ «ዓለም ቢጠላችሁ» ሲል፥ ለማጽናናት ብሎ አንድ ጊዜ ጥላቻውን ሊተው እንደሚችል ወይም ሁልጊዜ እንደማይጠላቸው አይጨምርም፤ ነገር ግን ሊታገሡት የሚገባበትን ምክንያት ብቻ ይሰጣል፦ «ከእናንተ በፊት እኔን እንደ ጠላኝ እወቁ»፤ [ዮሐንስ 15፥18] ይህም ከዓለም ጋር ባለው ተቃራኒነት ምክንያት በዚያን ጊዜ የተጠላውና ሁልጊዜም የሚጠላው እርሱ፥ ማለትም መንፈሱ፥ እንደ ሆነ የሚያመለክት ነው።
ምናልባት ዓለም አሁን ክርስቲያን ሆኖአል፥ ቢያንስ እኛ የምንኖርበት ክፍሉ ሆኖአል፤ ስለዚህ ዓለም አረማዊ በነበረ ጊዜ እንደ ነበረው ከክርስትና ጋር በተቃውሞ ሁኔታ ላይ እንዳለ አሁን ሊቈጠር አይገባም ትል ይሆናል።
ዓለም አሁን ክርስትናን እንደሚያምን የታወቀ ነው። ነገር ግን ይህ ክርስቲያናዊ ዓለም የክርስቶስ መንፈስ አለው የሚል ማን ነው? አጠቃላይ ዝንባሌዎቹ የክርስቶስ ዝንባሌዎች ናቸውን? የሥጋዊነት፥ የራስ ወዳድነት፥ የትዕቢት፥ የስስት፥ የክብር ምኞትና የከንቱ ውዳሴ ምኞቶች በአረማውያን መካከል ከነበሩበት ጊዜ ይልቅ አሁን በክርስቲያኖች መካከል ስላሉ ለወንጌል መንፈስ ያነሰ ተቃራኒ ናቸውን? ወይስ የአረማዊው ዓለም ዝንባሌዎችና ምኞቶች ጠፍተዋል፥ ሄደዋልም ትላለህን?
ሁለተኛ፥ ዓለም ስትል ምን ማለት እንዳለብህ አስብ። ይህም በቅዱስ ዮሐንስ ፈጽሞ ተገልጦልናል፦ «በዓለም ያለው ሁሉ፥ የሥጋ ምኞትና የዓይን ምኞት የኑሮም ትዕቢት» [1ኛ ዮሐንስ 2፥16] ይህ የዓለም ትክክለኛና ሙሉ መግለጫ ነው። እንግዲህ ይህ ዓለም ክርስቲያን ሆኖአል ትላለህን? ይህ ሁሉ አሁንም ካለ ግን፥ ያው ዓለም አሁን አለ፤ በቅዱስ ዮሐንስ ዘመን እንደ ነበረውም ለክርስትና ያው ጠላት ነው።
ቅዱስ ዮሐንስ ከአብ ያልሆነ ብሎ የፈረደበት ይህን ዓለም ነበር፤ ስለዚህ ክርስትናን በውጭ ቢያምን ወይም በግልጥ ቢያሳድድ፥ ለወንጌል እውነተኛ መንፈስና ቅድስና አሁንም በዚያው የተቃራኒነት ሁኔታ ላይ ነው።
በእርግጥም ዓለም ክርስትናን በማመኑ ከቀድሞው ያነሰ አደገኛ ጠላት ከመሆን እጅግ የራቀ ነው፤ በሞገሱ ከማንኛውም ጭካኔ የተሞላ ስደት ይልቅ እጅግ ብዙ ክርስቲያኖችን አጥፍቶአልና።
ስለዚህ ዓለምን በወንጌል የመጀመሪያ ዘመናት ከነበረው ይልቅ ለክርስትና ያነሰ ጠላትነትና ተቃውሞ እንዳለው አድርገን ከመቍጠር እጅግ ልንርቅ ይገባናል፤ ይልቁንም በዚያን ዘመን ከነበረው ይልቅ አሁን የሚበልጥና ይበልጥ አደገኛ ጠላት እንደ ሆነ ልንጠበቀው ይገባናል።
በስደቱ እሳትና ቍጣ ከነበረው ኃይል ይልቅ በሞገሱ፥ በሀብቱ፥ በክብሩ፥ በሽልማቱና በጥበቃው በክርስቲያኖች ላይ የሚበልጥ ኃይል ስላለው የሚበልጥ ጠላት ነው።
የጠላትነት መልኩን በማጣቱ ይበልጥ አደገኛ ጠላት ነው። ክርስትናን በውጭ ማመኑ ከእንግዲህ እንደ ጠላት እንዳይቈጠር ያደርገዋል፤ ስለዚህ ብዙዎቹ ሰዎች በእርሱ ለመገዛትና ለመመራት ራሳቸውን አሳልፈው እንዲሰጡ በቀላሉ ይሳባሉ።
በክርስቲያናዊው ዓለም ሥልጣን ሥር ኃጢአት ስለሚሠሩ ብቻ እንጂ በሌላ ምንም መሠረት ላይ ሳይሆን ስንት ሕሊናዎች በጸጥታ ይኖራሉ!
በክርስቲያናዊው ዓለም ዘንድ ቸል የተባሉ ስለሚመስሉ ብቻ ስንት የወንጌል ትእዛዛት ቸል ተብለው ተቀምጠዋል፥ እያንዳንዱ ሰውም ያለ ምንም ግድ ምንኛ ያነባቸዋል!
ሰዎች ያለ ምንም ማመንታትና ጸጸት ለክርስቲያናዊው ዓለም ስንት ነገር ይታዘዛሉ! እነዚህም በአረማውያን ብቻ ተጠይቀውባቸው ቢሆን ኖሮ ለክርስትና ቅድስና ተቃራኒ ናቸው ተብለው ውድቅ ይደረጉ ነበር!
ክርስቲያናዊው ዓለም እንደሚኖረው እንደሚኖር ባያይ ኖሮ፥ ሕይወቱ ለወንጌል ምን ያህል ተቃራኒ እንደ ሆነ እያየ ማን ሊረካ ይችል ነበር?
የዓለም ሥልጣን ይህን የመስቀል ትምህርት ባያባርረው ኖሮ፥ ወንጌልን የሚያነብ ማን ስለ ታላቅ ራስን መካድ፥ ትሕትናና የመንፈስ ድህነት አስፈላጊነት ማሳመን ያስፈልገው ነበር?
ስለዚህ ጥሩ ክርስቲያን ከክርስቲያናዊው ዓለም ሥልጣን ይበልጥ ሊጠራጠረው ወይም ዘወትር ሊጠበቀው የሚገባ ምንም ነገር የለም።
ዓለምን የክርስትና ተቃራኒ አድርገው የሚያቀርቡ፥ እንደ ዓመፃ ገንዘብ፥ እንደ ኃጢአት ጭራቅ ከእርሱ እንድንለይ የሚጠይቁ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ሁሉ ለአሁኑ ዓለምም በዚያው ጥብቅ ትርጉም ሊወሰዱ ይገባቸዋል።
ዓለም ያለፈበት ለውጥ ሃይማኖትን የማጥፋት ዘዴዎቹን ብቻ ለወጠ እንጂ ኃይሉን አልቀነሰምና።
ክርስቲያኖች ከአረማዊው ዓለም ሕይወታቸውን ከማጣት በቀር የሚፈሩት ምንም ነገር አልነበረም፤ ወዳጅ የሆነው ዓለም ግን ሃይማኖታቸውን ማዳን አስቸጋሪ ያደርግባቸዋል።
ትዕቢት፥ ሥጋዊነት፥ ስስትና የክብር ምኞት የአረማዊውን ዓለም ሥልጣን ብቻ በያዙ ጊዜ፥ ክርስቲያኖች በዚህ ምክንያት ተቃራኒ በሆኑት በጎ ምግባራት ላይ ይበልጥ ይተጉ ነበር። ትዕቢት፥ ሥጋዊነት፥ ስስትና የክብር ምኞት የክርስቲያናዊውን ዓለም ሥልጣን ሲይዙ ግን፥ እያንዳንዱ ክርስቲያን የወንጌልን መንፈሳዊነት ከመለማመድ በኀፍረት ከመገለል ብቻ ሳይሆን የመንፈሳዊነቱን ግንዛቤ እንኳ ከማጣት እጅግ ታላቅ አደጋ ላይ ነው።
ስለዚህ የአሁኑን ዓለም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚገልጠው ለእውነተኛ ቅድስና ሁሉ ያው ክፉ ጠላት አድርገህ በመቍጠርና ዓለም አረማዊ በነበረ ጊዜ እንደ ነበረው አሁን ክርስቲያን ሆኖም ዝንባሌዎቹንና ምኞቶቹን መምሰል አደገኛ እንደ ሆነ ራስህን በማረጋገጥ ካልሆነ በቀር ራስህን ከእርሱ ለማዳን ምንም ዕድል የለም ማለት ይቻላል።
ራስህን ብቻ ጠይቅ፤ የክርስቲያናዊው ዓለም መንፈሳዊነት፥ ትሕትናና ልከኝነት የክርስቲያናዊው መንፈስ መንፈሳዊነት፥ ትሕትናና ልከኝነት ነውን? ካልሆነ፥ ክርስቲያናዊ የሆነውን ከመምሰል ይልቅ በማንኛውም ዓለም እንዴት ይበልጥ ልትጠፋ ትችላለህ?
ሰው ለክብር ስስታምና የክብር ፈላጊ ከመሆን የበለጠ ነፍሱን ለእግዚአብሔር ምሕረት የማትገባ ለማድረግ ሌላ ማድረግ ያስፈልገዋልን? ነገር ግን አሁን የምትኖርበትን የዓለም መንፈስና ዝንባሌ ሳይክድ ሰው ይህን ዝንባሌ እንዴት ሊክድ ይችላል?
ለገንዘብ ከሚሰጥ የተሳሳተ ግምት ይበልጥ ሰውን ለክርስቶስ መንፈስ የማይበቃ የሚያደርገው ምንድር ነው? ነገር ግን የክርስቲያናዊውን ዓለም ሥልጣን ከመከተል ይልቅ ለገንዘብ በሚሰጠው ግምት እንዴት ይበልጥ ሊሳሳት ይችላል?
እንዲያውም በማንኛውም የሕይወት ወገንና ደረጃ፥ የትምህርትም ይሁን የሥራ፥ በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በመንግሥት፥ ከአንተ ጋር በአንድ ወገንና ሥራ ያሉትን ሰዎች እጅግ የተለመደውን ዝንባሌና አካሄድ ሳትክድ እንደ ሃይማኖት መንፈስ ልትሠራ አትችልም።
የሰው ጥንቃቄ ከሌሎች ተለይቶ ላለመታየት ስላለው አስፈላጊነት እጅግ በጥበብ የሚናገር ቢመስልም፥ ከሌሎች ተለይቶ ለመታየት እስከሚሆን ድረስ ደካማ ለመሆን የማይደፍር ሰው ግን የክርስትና መንፈሳዊነትን እጅግ ዋና ዋና ግዴታዎች ለማስወገድ ብዙ ጊዜ ይገደዳል።
እነዚህ አሳቦች የዓለም ሥልጣንና ልማድ በክርስትና ትሕትና ልምምድ ላይ ያስነሣቸውን እነዚያን ችግሮች ሰብረህ እንድታልፍና እነዚያን ፈተናዎች እንድትቋቋም ይረዱሃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።