ለአምልኮታዊና ለቅዱስ ሕይወት የቀረበ ከባድ ጥሪ
ስለ ዝማሬ፥ ማለትም በግል መሰጠታችን መዝሙራትን ስለ መዘመር። የዚህ ዓይነቱ መሰጠት ልዕልናና ጥቅም። በልባችን ላይ የሚያደርገው ታላቅ ውጤት። በተሻለ ሁኔታ የሚፈጸምበት መንገድ

ምዕራፍ 15 · 21 ደቂቃ ንባብ · 27 ደቂቃ ማዳመጥ

ስለ ዝማሬ፥ ማለትም በግል መሰጠታችን መዝሙራትን ስለ መዘመር። የዚህ ዓይነቱ መሰጠት ልዕልናና ጥቅም። በልባችን ላይ የሚያደርገው ታላቅ ውጤት። በተሻለ ሁኔታ የሚፈጸምበት መንገድ

ባለፈው ምዕራፍ መሰጠታችሁን ለማነሣሣትና ለማሻሻል ምን ዓይነት መንገዶችንና ዘዴዎችን መጠቀም እንዳለባችሁ፥ ጸሎታችሁን ምን ያህል ማልዳችሁ መጀመር እንዳለባችሁ፥ በማለዳም የመጀመሪያ መሰጠታችሁ ርእስ ምን መሆን እንዳለበት አይታችኋል።

ገና የቀረ አንድ ነገር አለ፤ ይህም ተገቢና ትክክለኛ ስለ ሆነ ብቻ ሳይሆን ቢዘነጋ በመሰጠታችሁ ላይ ታላቅ ጉዳት የሚያመጣ ስለ ሆነ እንድትጠብቁት የሚገባ ነው፤ እርሱም ጸሎታችሁን ሁሉ በመዝሙር መጀመር ነው።

ይህ እጅግ ትክክል፥ ለመሰጠትም እጅግ ጠቃሚ፥ በልባችንም ላይ እጅግ ታላቅ ኃይል ያለው ስለ ሆነ ለሰዎች ሁሉ እንደ የጋራ ደንብ አጥብቀን ልናቀርበው እንችላለን።

መዝሙርን እንድታነቡት ማለቴ አይደለም፤ ነገር ግን በተለምዶ የንባብ መዝሙራት ከምንላቸው መዝሙራት አንዱን በዜማ እንድታዜሙት ወይም እንድትዘምሩት ነው። ለእግዚአብሔር በተሰጠ ልብ መለመን የጸሎት ሥርዓት ተገቢ አጠቃቀም እንደ ሆነ ሁሉ መዘመርም የመዝሙር ተገቢ አጠቃቀም ነውና፤ የተነበበ ብቻ መዝሙርም እንዲሁ በዓይን ብቻ እንደ ታየ ጸሎት ነው።

በኮሌጆች፥ በዩኒቨርሲቲዎችና በአንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት እንደሚደረገው መዝሙርን በዜማ የማዜም ዘዴ ሰዎች ሁሉ ሊያደርጉት የሚችሉት ነው። በዚህ ዓይነት መዝሙርን ሲያዜሙ የድምፅ ለውጡ እጅግ ጥቂትና ተፈጥሮአዊ ስለ ሆነ ሁሉም ሊያደርገው ይችላል፤ ቢሆንም የልባችንን ደስታ ለማነሣሣትና ለመጠበቅ በቂ ነው።

ስለዚህ ይህን መዝሙርን ማዜም ለመሰጠታችሁ አስፈላጊ መጀመሪያ አድርጋችሁ ልትቈጥሩት ይገባል፤ በውስጣችሁ ያለውን መልካምና ቅዱስ ነገር ሁሉ የሚቀሰቅስ፥ መንፈሳችሁን ወደ ተገቢ ተግባሩ የሚጠራ፥ በሰማይ ፊት በተሻለ አቋማችሁ የሚያቆማችሁ፥ የነፍሳችሁንም ኃይላት ሁሉ ለአምልኮና ለስግደት የሚያስተካክል ነገር ነውና።

ለጸሎታችሁ መንገድን እንደ እነዚህ የምስጋና መዝሙሮች የሚጠርግ፥ የልብን ድንዛዜ የሚበትን፥ ነፍስን ከደካማና ከጥቃቅን ምኞቶች የሚያነጻ፥ ሰማይን የሚከፍት ወይም ልባችሁን ወደ እርሱ እጅግ የሚያቀርብ ምንም ነገር የለምና።

በእግዚአብሔር የመደሰትን ስሜት ይፈጥራሉ፤ ቅዱስ ምኞቶችን ያነቃሉ፤ እንዴት መለመን እንዳለባችሁ ያስተምራሉ፤ እግዚአብሔርም እንዲሰጥ ያሸንፋሉ። ቅዱስ ነበልባልን ያቀጣጥላሉ፤ ልባችሁን መሠዊያ፥ ጸሎታችሁንም ዕጣን ያደርጋሉ፤ እንደ መልካም መዓዛም ወደ ጸጋው ዙፋን ያደርሱታል።

መዝሙርን በመዘመርና በማንበብ መካከል ያለው ልዩነት የምትወዱትን አንድ ተራ ዘፈን በማንበብና በመዘመር መካከል ያለውን ልዩነት ብታስቡ በቀላሉ ይገባችኋል። ስታነቡት ብቻ ትወዱታላችሁ እንጂ ከዚያ አያልፍም፤ ልክ እንደ ዘመራችሁት ግን ትደሰቱበታላችሁ፥ ደስታውም ይሰማችኋል፤ ይይዛችኋል፥ ስሜታችሁም አብሮት ይራመዳል፥ በቃላቱ ውስጥ ያለ የሚመስለውም ያው መንፈስ በውስጣችሁ ይሰማችኋል።

እንዲህ ያለ ዘፈን ያለውን ሰው መዘመር እንደማያስፈልገው፥ ማንበቡ ብቻ እንደሚበቃው ብትነግሩት ምን ማለታችሁ እንደ ሆነ ይደነቃል፤ መልካም መሆኑን ለማየት ምግቡን ብቻ መመልከት እንዳለበት እንጂ መብላት እንደማያስፈልገው እንደ ነገራችሁት ያህል ሞኞች አድርጎ ይቈጥራችኋል፤ ያልተዘመረ የምስጋና መዝሙር ጥቅም ላይ እንዳልዋለ እንደ ማንኛውም መልካም ነገር ነውና።

ምናልባት መዘመር ለተወሰኑ ሰዎች ብቻ የተሰጠ ልዩ መክሊት ነው፥ እኔም ዜማ ለማውጣት ድምፅም ጆሮም የለኝም ትሉ ይሆናል።

መዘመር የሁሉ የጋራ መክሊት ነው፥ ሰዎችም በሌሎች ነገሮች ሁሉ እንደሚለያዩ በእርሱም ይለያያሉ ብትሉ ኖሮ እጅግ የበለጠ እውነት ተናግራችሁ ነበር።

ለሰዎች ሁሉ የጋራ በሆነውና የሰው ተፈጥሮ ዋና ባሕርይ በሚመስለው በማሰብ መክሊት ሰዎች ምን ያህል ይለያያሉ! አንዳንዶች በሁሉ ነገር ላይ ምን ያህል በቀላሉ ያመዛዝናሉ! ሌሎች ደግሞ በማንኛውም ነገር ላይ ለማመዛዘን ምን ያህል ይቸገራሉ! አንዳንዶች እጅግ ጥልቅ በሆኑ ጉዳዮች ላይ ምን ያህል በግልጥ ይናገራሉ! ሌሎች ደግሞ እጅግ ቀላል በሆኑ ርእሶች ላይ ምን ያህል በተደበላለቀ ሁኔታ ይናገራሉ!

ሆኖም ማንም ሰው እነዚህ መክሊቶች አንዳንዶች እንዳላቸው ስለሌሉት ከማሰብ፥ ከማመዛዘን ወይም ከመናገር ነጻ እንዲሆን አይመኝም። ነገር ግን አንድ ሰው እነዚህ መክሊቶች በላቀ ደረጃ ስለሌሉት ስለ እግዚአብሔር ከማሰብ፥ ለእርሱ ስላለበት ግዴታ ከማመዛዘን ወይም ስለ መዳን መንገዶች ከመነጋገር ነጻ እንደ ሆነ ቢያስብ፥ ይህ ልክ አንድ ሰው ጥሩ ጆሮ ወይም የዜማ ድምፅ ስለሌለው የእግዚአብሔርን ምስጋና ከመዘመር ነጻ እንደ ሆነ እንደሚያስብ ያህል ትክክል ነው።

በጸሎት የሚፈለገው ውብ አነጋገር ሳይሆን መናገር እንደ ሆነ፥ የስግደትም ተገቢ ክፍል ያማረ አጐንብሶ ሳይሆን ማጐንበስ እንደ ሆነ፥ እንዲሁም እግዚአብሔርን ለማመስገን የሚፈለገው መንገድ የጥበብና ያማረ ዝማሬ ሳይሆን መዘመር ነውና።

አንድ ሰው በድምፁ ውስጥ እንግዳ ቃና ስላለበት መጸለይን ቢተው፥ ድምፁን ጥቂት ብቻ ስለሚቈጣጠር መዝሙራትን ከመዘመር የሚቈጠብ ሰው ያለውን ያህል ምክንያት ይኖረው ነበር። አንድ ሰው ጸሎቱን በእንግዳ ቃና ቢናገረውም የራሱን መሰጠት ዓላማዎች ሁሉ በበቂ ሁኔታ ሊፈጽም እንደሚችል፥ እንዲሁ አንድ ሰው መዝሙርን እጅግ በዜማ ባይዘምረውም በእግዚአብሔር የመደሰትንና እርሱን የማመስገንን ዓላማዎች ሁሉ በበቂ ሁኔታ ሊፈጽም ይችላል።

ሁለተኛ፥ ሌሎች ሰዎችን ለማዝናናት እንድትዘምሩ ብትጠየቁ ይህ ተቃውሞ የተወሰነ ክብደት ይኖረው ነበር፤ ነገር ግን የግል መሰጠታችሁ ክፍል አድርጋችሁ የእግዚአብሔርን ምስጋና ብቻ እንድትዘምሩ በተጠየቃችሁበት በዚህ ጉዳይ ተቀባይነት የለውም።

እጅግ መጥፎ ድምፅና ደካማ አነጋገር ያለው ሰው የጉባኤ አፍ እንዲሆን ቢጠየቅ ለጸሎት የሚስማማ ድምፅ ወይም አነጋገር የለኝም ማለቱ ተገቢ ምክንያት ይሆንለታል። በዚሁ ምክንያት ግን የራሱን የግል መሰጠት ቢተው እጅግ ሞኝ ይሆናል።

የመዝሙራትን መዘመር ጉዳይም ልክ እንዲሁ ነው፤ ሌሎች ሰዎችን ለማዝናናት የሚያስችል የዝማሬ መክሊት ላይኖራችሁ ይችላል፥ ስለዚህም ከዚያ ራሳችሁን ማግለላችሁ ምክንያታዊ ነው፤ በዚያ ምክንያት ግን ከዚህ እግዚአብሔርን የማመስገኛ መንገድ ራሳችሁን ብታገሉ በታላቅ ሞኝነት ትከሰሳላችሁ፤ ጸሎት ስለያዛቸው ውብ ቃላት እንደማይፈለግ ሁሉ መዘመርም ስለሚያወጣው ዜማ አይፈለግምና፤ የሚፈለገው በእግዚአብሔር ደስ የሚለው ልብ ተፈጥሮአዊና ተገቢ መግለጫ ስለ ሆነ ነው።

ብሩክ መድኃኒታችንና ሐዋርያቱ መዝሙር ዘመሩ፤ ነገር ግን ውብ ዜማ ከማውጣት ይልቅ በእግዚአብሔር ደስ ብሏቸው ነበር ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው።

ልባችሁ በእውነት በእግዚአብሔር ደስ እንዲለው፥ በእግዚአብሔርም ምስጋና እንዲነካ ሆናችሁ ብቻ ኑሩ፤ ያን ጊዜ ይህ የልባችሁ ሁኔታ ለመዝሙር ዜማ ለማግኘት ድምፅም ሆነ ጆሮ እንደማያጣ ታገኛላችሁ። ሁሉም ሰው በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ በተወሰነ ደረጃ መዘመር እንደሚችል ራሱን ያገኘዋል፤ ሰዎች ሁሉ ስሜታቸውን በአንድ ዓይነት ዜማ ለመግለጥ የሚዘጋጁባቸው የደስታ ጊዜያትና አጋጣሚዎች አሉ። የሚሰማቸው ደስታ ድምፃቸው በእርሱ ድርሻ እንዲኖረው ያስገድዳቸዋል።

ስለዚህ መዝሙርን ለመዘመር ድምፅ ወይም ጆሮ የለኝም የሚል ሰው ጉዳዩን ተሳስቶአል፤ የጐደለው በእውነት በእግዚአብሔር ደስ የሚለው መንፈስ ነው፤ ድንዛዜው በጆሮው ሳይሆን በልቡ ነው፤ ልቡ በእግዚአብሔር እውነተኛ ደስታ ሲሰማው፥ በመዝሙራት የተገለጠውንም ሙሉ በሙሉ ሲጣፍጠው፥ የድምፁ እንቅስቃሴዎች የልቡን እንቅስቃሴዎች እንዲገልጡ ማድረግ እጅግ ደስ የሚያሰኝ ሆኖ ያገኘዋል።

በእርግጥ መዘመር ወደ ጥበብነት ሲሻሻል፥ — ድምፅን በእንዲህና በእንዲያ ባለ የኖታ ስፋት ማስኬድንና በተጠና የለውጦች ብዛት ምት መጠበቅን ሲያመለክት፥ ተፈጥሮአዊ አይደለም፥ የማንኛውም ተፈጥሮአዊ የአእምሮ ሁኔታ ውጤትም አይደለም፤ ስለዚህ በዚህ ትርጉም ውብ ጭፈራን የሚያደርጉት እንግዳና ፈጠራ እንቅስቃሴዎች ለሰዎች ሁሉ የጋራ እንዳልሆኑ ሁሉ ለሰዎች ሁሉ የጋራ አይደለም።

ነገር ግን መዘመር ለልብ እንቅስቃሴዎች የሚስማማ የድምፅ እንቅስቃሴን፥ በምንናገራቸውም ቃላት ትርጉም መሠረት ቃናውን መለወጥን ሲያመለክት፥ ሰዎች በቍጣ ሲያስፈራሩ ከፍ አድርገው መናገራቸው ወይም ሲያዝኑና ይቅርታ ሲለምኑ ዝቅ አድርገው መናገራቸው ተፈጥሮአዊና ለሁሉ የጋራ እንደ ሆነ ሁሉ ለሰዎች ሁሉ ተፈጥሮአዊና የጋራ ነው።

ስለዚህ ሰዎች ሁሉ እንደሚያስቡ፥ እንደሚናገሩ፥ እንደሚስቁና እንደሚያለቅሱ በዚያው መንገድ ሰዎች ሁሉ ዘማሪዎች ናቸው። ኀዘንና ደስታ ፈጠራዎች እንዳልሆኑ ሁሉ መዘመርም ፈጠራ አይደለምና።

እያንዳንዱ የልብ ሁኔታ ሰውነትን በተፈጥሮ ለእርሱ በሚስማማና ለሌሎች ሰዎች ለማሳየት በሚያገለግል ሁኔታ ውስጥ ያደርገዋል። አንድ ሰው ቢቈጣ ወይም ቢንቅ እነዚህን ስሜቶች በድምፁ ቃና እንዴት እንደሚገልጣቸው ማንም ሊያስተምረው አያስፈልግም። የልቡ ሁኔታ ድምፁን በተገቢው እንዲጠቀም ያዘጋጀዋል።

ስለዚህ የመለኮታዊ መዝሙራት ዘማሪዎች ጥቂቶች ቢሆኑ፥ ሰዎችም ለዚህ የመሰጠት ክፍል መመከር ቢያስፈልጋቸው፥ ይህ የሆነው በእግዚአብሔር ምስጋና የደስታና የሐሴት እንቅስቃሴ እንዲሰማቸው ልባቸው እስከዚያ የመንፈሳዊነት ከፍታ የተነሣ ጥቂቶች ብቻ ስለ ሆኑ ነው።

በቀይ ባሕር ውስጥ ሲመራ ከሙሴ ጋር እንደ ነበራችሁ፥ ውኆች ሲከፈሉና በሁለቱም ወገን እንደ ክምር ሲቆሙ እንዳያችሁ፥ እስክታልፉም ድረስ ተይዘው ቆይተው ከዚያም በጠላቶቻችሁ ላይ ሲወድቁ እንዳያችሁ በልባችሁ አስቡ፤ ያን ጊዜ ከሙሴ ጋር «ኃይሌና ዝማሬዬ እግዚአብሔር ነው፥ እርሱም መድኃኒት ሆነልኝ» ወዘተ. ብላችሁ ለመዘመር ድምፅ ወይም ጆሮ ያጣችሁ ይመስላችኋልን? [ዘፀአት 15፥2] በእንዲህ ያለ አጋጣሚ ሰዎች ሁሉ ዘማሪዎች ይሆኑ እንደ ነበር የራሳችሁ ልብ እንደሚነግራችሁ አውቃለሁ። ስለዚህ የእግዚአብሔርን ምስጋና ለመዘመር ድምፅን የሚያስተካክለው ልብ እንደ ሆነ ይህ ያስተምራችሁ፤ ያንኑ ቃል አሁን በደስታ መዘመር ካልቻላችሁ፥ አይሁድ በቀይ ባሕር በመዳናቸው እንደ ተነኩ ወይም እናንተ ራሳችሁ ትነኩ እንደ ነበረ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ በሆነው በዓለም መዳን ስላልተነካችሁ ነው።

በማንኛውም ዓይነት ዝማሬ ለመደሰት የሚያዘጋጀው የልብ ሁኔታ እንደ ሆነ ስለ ሰው ተፈጥሮ ከብዙ ዓይነት ምልከታዎች በቀላሉ ሊረጋገጥ ይችላል። አንድ ያረጀ ሴሰኛ መዝሙርን ወይም በጎ ምግባርን የሚያወድስ ዘፈንን ብቻ ብትዘምሩለት፥ በዓለም አነጋገር ድምፅም ጆሮም የሌለው ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን የቀድሞ ሴሰኝነቱን የሚያወድስ ነገር በቀላል ዜማ ብትዘምሩለት፥ በአፉ ውስጥ ጥርስ ባይኖረውም በእንዲህ ያለ ዜማ ለመተባበር ድምፅም ጆሮም እንዳለው ያሳያችኋል። ያን ጊዜ ልቡን ትቀሰቅሳላችሁ፤ ደስ ሲለው እንደሚስቅ ሁሉ ለእንዲህ ያሉ ቃላትም በተፈጥሮ ይዘምራል። ልብን በሚነካ በማንኛውም ዘፈን ይህ እንዲሁ ይሆናል፤ የማንኛውንም ሰው ልብ የሚገዛውን ምኞት ብታወድሱ፥ ከእናንተ ጋር እንዲተባበር ድምፁን ታስተካክላላችሁ።

እንዲሁም የሚገዛው ዝንባሌው መሰጠት የሆነ፥ ልቡም በእግዚአብሔር የተሞላ ሰው ብታገኙ፥ ለሌላ ዜማ ድምፅም ጆሮም ባይኖረውም፥ የልቡ ደስታ የሆነውን ያን እግዚአብሔርን በሚያከብሩ በእነዚያ የምስጋና መዝሙሮች ድምፁ ደስ ይለዋል። ስለዚህ ይህን የመሰጠት ክፍል በደስታ መፈጸም ብትፈልጉ፥ ልባችሁን ከማዘጋጀት ይልቅ ዜማ መማር ወይም ኖታዎችን መለማመድ እምብዛም አያስፈልግም፤ ብሩክ ጌታችን «ከልብ ክፉ አሳብ፥ መግደል» ወዘተ. «ይወጣልና» እንዳለ፥ [ማቴዎስ 15፥19] እንዲሁ ከልብ ቅዱስ ደስታ፥ ምስጋናና ውዳሴ እንደሚወጡ እኩል እውነት ነውና። ከዳዊት ጋር አንድ ጊዜ «አቤቱ፥ ልቤ የጸና ነው፥ ልቤ የጸና ነው» ማለት ብትችሉ፥ እርሱ እንዳደረገው «እቀኛለሁ፥ እዘምርማለሁ» ወዘተ. ብሎ መጨመር እጅግ ቀላልና ተፈጥሮአዊ ይሆናል። [መዝሙር 57፥7]

ሁለተኛ፥ እንግዲህ ለዚህ ዓይነቱ መሰጠት ሌላ ምክንያት እንመልከት። መዘመር በልብ ውስጥ ያለ የደስታ ተፈጥሮአዊ ውጤት እንደ ሆነ ሁሉ ልብን ደስ የማሰኘት ተፈጥሮአዊ ኃይልም አለው።

ነፍስና ሥጋ እጅግ የተዋሐዱ ስለ ሆኑ በተግባራቸው እያንዳንዳቸው በሌላው ላይ ኃይል አላቸው። በነፍስ ውስጥ ያሉ አንዳንድ አሳቦችና ስሜቶች በሥጋ ውስጥ እንዲህና እንዲያ ያሉ እንቅስቃሴዎችንና ተግባሮችን ያስገኛሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንድ የሥጋ እንቅስቃሴዎችና ተግባሮች በነፍስ ውስጥ እንዲህና እንዲያ ያሉ አሳቦችንና ስሜቶችን የማነሣሣት ያው ኃይል አላቸው። ስለዚህ መዘመር በአእምሮ ውስጥ ያለ የደስታ ተፈጥሮአዊ ውጤት እንደ ሆነ ሁሉ በአእምሮ ውስጥ ደስታን የሚያነሣሣ እውነተኛ ተፈጥሮአዊ ምክንያትም ነው።

የልብ መሰጠት በተፈጥሮ ወደ ውጫዊ የጸሎት ተግባሮች እንደሚገነፍል ሁሉ ውጫዊ የጸሎት ተግባሮችም የልብን መሰጠት የሚያነሣሡ ተፈጥሮአዊ መንገዶች ናቸው።

በአእምሮ ሁኔታዎችና ዝንባሌዎች ሁሉ እንዲሁ ነው፤ የአእምሮ ውስጣዊ ሁኔታ ለእርሱ የሚስማሙ ውጫዊ ተግባሮችን እንደሚያስገኝ ሁሉ እነዚያ ውጫዊ ተግባሮችም ለእነርሱ የሚስማማ ውስጣዊ የአእምሮ ሁኔታን የማነሣሣት ተመሳሳይ ኃይል አላቸው። ቍጣ የቍጣ ቃላትን እንደሚያስገኝ ሁሉ የቍጣ ቃላትም ቍጣን ያበዛሉ።

ስለዚህ የሰውን ተፈጥሮ ብቻ ብንመለከት፥ ጸሎት የመሰጠትን መንፈስ በውስጣችን ለማነሣሣት ተገቢና አስፈላጊ እንደ ሆነ ሁሉ መዝሙራትን መዘመር ወይም ማዜም ልባችንን በእግዚአብሔር ወደ መደሰት ለማንሣት እንዲሁ ተገቢና አስፈላጊ እንደ ሆነ እናገኛለን። ለአንዱ ያለው ምክንያት ሁሉ በሁሉም ረገድ ለሌላውም እኩል ብርቱ ምክንያት ነው።

ስለዚህ መዝሙራትን የመዘመርን ምክንያትና አስፈላጊነት ማወቅ ብትፈልጉ፥ እግዚአብሔርን የማመስገንንና በእርሱ የመደሰትን ምክንያትና አስፈላጊነት ልታስቡ ይገባችኋል፤ ጸሎት የመሰጠት መንፈስ እውነተኛ ልምምድና ድጋፍ እንደ ሆነ ሁሉ መዝሙራትን መዘመርም የምስጋና መንፈስ እውነተኛ ልምምድና ድጋፍ ነውና። ያለ ጸሎት እንደሚገባ ለእግዚአብሔር የተሰጣችሁ መሆን እንደምትችሉ ማሰብ፥ ያለ መዝሙራት ዝማሬም እንደሚገባ በእግዚአብሔር መደሰት እንደምትችሉ ከማሰብ አይለይም፤ ጸሎት የመሰጠት ተፈጥሮአዊ ቋንቋ እንደ ሆነ ሁሉ ይህ ዝማሬም የውዳሴና የምስጋና ተፈጥሮአዊ ቋንቋ ነውና።

የነፍስና የሥጋ መዋሐድ አካላት ሲዋሐዱና ሲደባለቁ እንደምናየው የባሕርያቸው መደባለቅ አይደለም፤ ነገር ግን እርስ በርሳቸው በሚሠሩበት በጋራ ኃይል ብቻ የተመሠረተ ነው።

ሁለት ሰዎች እርስ በርሳቸው እንዲህ ባለ የመደጋገፍ ሁኔታ ቢኖሩ፥ አንዳቸውም ሌላውን በዚያው ሁኔታ ውስጥ ሳያስገቡ ምንም ነገር ሊሠሩ፥ ሊንቀሳቀሱ፥ ሊያስቡ፥ ሊሰማቸው፥ ሊሠቃዩ ወይም ሊመኙ ባይችሉ፥ ባሕርያቸው አንድ ላይ ባይዋሐድም በጥብቅ መዋሐድ ሁኔታ ውስጥ ናቸው ማለት ተገቢ ነው።

የነፍስና የሥጋ መዋሐድም ይህ ነው፤ የአንዱ ባሕርይ ከሌላው ጋር ሊደባለቅ ወይም ሊዋሐድ አይችልም፤ ነገር ግን የአንዱ ተግባሮችና መከራዎች ሁሉ በዚያው ጊዜ የሌላውም ተግባሮችና መከራዎች እስኪሆኑ ድረስ በእንዲህ ያለ የመዋሐድ ሁኔታ አብረው ተይዘዋል። ሥጋ የማይካፈልበት የነፍስ አሳብ ወይም ስሜት የለም፤ በተወሰነ ደረጃ ነፍስን የማይነካ የሥጋ ተግባር ወይም እንቅስቃሴ የለም።

በዓለም ላይ የምታዩአቸው ኃይላትና ውጤቶች ሁሉ ምክንያትና መንሥኤ የእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ እንደ ሆነ፤ ፀሐይ ብርሃንንና ሙቀትን የምትሰጠው ይህን የማድረግ ተፈጥሮአዊ ኃይል ስላላት እንዳልሆነ፤ በአንድ ስፍራ ጸንታ የምትኖረውና ሌሎች አካላት በዙሪያዋ የሚንቀሳቀሱት ፀሐይ ቆማ መኖር ባሕርይዋ ስለ ሆነ፥ በዙሪያዋ መንቀሳቀስም የሌሎቹ አካላት ባሕርይ ስለ ሆነ ሳይሆን በእንዲህ ያለ ሁኔታ እንዲኖሩ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ ብቻ እንደ ሆነ፤ ዓይን የማየት ብልት ወይም መሣሪያ የሆነው የዓይን ቆዳዎች፥ ሽፋኖችና ፈሳሾች ማየትን የመስጠት ተፈጥሮአዊ ኃይል ስላላቸው እንዳልሆነ፤ ጆሮዎችም የመስማት ብልቶች ወይም መሣሪያዎች የሆኑት የጆሮ አሠራር በድምፆች ላይ ተፈጥሮአዊ ኃይል ስላለው ሳይሆን ማየትና መስማት በዚህ መንገድ እንዲገኙ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ሆነ ብቻ እንደ ሆነ፤ እንዲሁም በዚያው ዓይነት በነፍስና በሥጋ መካከል ላለው ለዚህ መዋሐድ መንሥኤው የሰው ነፍስ ወይም ሥጋ ባሕርይ ሳይሆን የእግዚአብሔር ፈቃድ ብቻ ነው።

ይህን ስለ ነፍስና ሥጋ መዋሐድ የቀረበ አጭር ማብራሪያ በትክክል ብትረዱት፥ የሃይማኖትን ውጫዊ ክፍሎች ሁሉ ምክንያትና አስፈላጊነት በብዙ ታስተውላላችሁ።

ይህ የነፍሳችንና የሥጋችን መዋሐድ በራሳችን ላይ እጅግ ጥቂትም እጅግ ብዙም ኃይል ያለን የመሆኑ ምክንያት ነው። በነፍሳችን ላይ እጅግ ጥቂት ኃይል ያለን በዚህ መዋሐድ ምክንያት ነው፤ ውጫዊ ነገሮች በሥጋችን ላይ የሚያደርጉትን ውጤት መከልከል እንደማንችል፥ ውጫዊ መንሥኤዎችንም ማዘዝ እንደማንችል ሁሉ የአእምሮአችንን ውስጣዊ ሁኔታ ሁልጊዜ ማዘዝ አንችልምና፤ ውጫዊ ነገሮች ያለ ፈቃዳችን በሥጋችን ላይ እንደሚሠሩ ሁሉ ሥጋችንም በነፍስና በሥጋ መዋሐድ ሕግጋት በአእምሮአችን ላይ ይሠራልና፤ በዚህም በራሳችን ላይ እጅግ ጥቂት ኃይል ያለን በዚህ መዋሐድ ምክንያት እንደ ሆነ ታያላችሁ።

በሌላ በኩል ደግሞ በራሳችን ላይ እጅግ ብዙ ኃይል ያለን በዚህ መዋሐድ ምክንያት ነው። ነፍሳችን በአብዛኛው በሥጋችን ላይ እንደምትደገፍ፥ በሥጋችንም ላይ ታላቅ ኃይል እንዳለን፥ ውጫዊ ተግባሮቻችንን ማዘዝና በነፍስ ውስጥ በተፈጥሮ ልማዶችን የሚያስገኙ የሕይወት ልማዶችን በራሳችን ላይ ማስገደድ እንደምንችል፥ ሥጋችንንም መግደልና ምኞቶቻችንን ከሚያቀጣጥሉ ነገሮች ራሳችንን ማራቅ እንደምንችል፥ እንዲሁ በነፍሳችን ውስጣዊ ሁኔታ ላይ ታላቅ ኃይል አለን። ደግሞም የውጫዊ ተግባሮቻችን ጌቶች እንደ ሆንን፥ ራሳችንንም ወደ ውጫዊ የማንበብ፥ የመጸለይ፥ የመዘመርና የመሳሰሉት ተግባሮች ማስገደድ እንደምንችል፥ እነዚህ የሥጋ ተግባሮች ሁሉ በነፍስ ላይ ውጤት እንዳላቸው፥ በልባችንም ውስጥ እንዲህና እንዲያ ያሉ ዝንባሌዎችን በተፈጥሮ እንደሚያበጁ፥ እንዲሁ የእነዚህ ውጫዊ የሥጋ ተግባሮች ጌቶች በመሆናችን በልብ ውስጣዊ ሁኔታ ላይ ታላቅ ኃይል አለን፤ በዚህም በራሳችን ላይ እጅግ ብዙ ኃይል ያለን በዚህ መዋሐድ ምክንያት ነው።

ከዚህም መዝሙራትን የመዘመርንና የሃይማኖትን ውጫዊ ተግባሮች ሁሉ አስፈላጊነትና ጥቅም ደግሞ ልታዩ ትችላላችሁ፤ ሥጋ በነፍስ ላይ እንዲህ ያለ ታላቅ ኃይል ካለው፥ ነፍስን የሚነኩ እንዲህ ያሉ የሥጋ ተግባሮች ሁሉ በሃይማኖት ውስጥ ታላቅ ክብደት እንዳላቸው የተረጋገጠ ነው። ይህም በተግባሮቹ ራሳቸው ውስጥ እውነተኛ አምልኮ ወይም መንፈሳዊነት ስላለ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር እውነተኛ አምልኮ የሆነውን ያን መንፈስ ለማነሣሣትና ለመደገፍ የሚስማሙ ስለ ሆኑ ነው።

ስለዚህ የሃይማኖት መቀመጫ ልብ ቢሆንም፥ ሥጋችን በልባችን ላይ ኃይል ስላለው፥ ውጫዊ ተግባሮችም ከልብ ስለሚወጡና ወደ ልብ ስለሚገቡ፥ ውጫዊ ተግባሮች በልብ ውስጥ በተቀመጠው በዚያ ሃይማኖት ላይ ታላቅ ኃይል እንዳላቸው ግልጥ ነው።

ስለዚህ በልባችን ውስጥ የመንፈሳዊነትን ልማዶች ለማስገኘትና ለማጽናት ውስጣዊ ማሰላሰልን እንደምንጠቀም ሁሉ ውጫዊ ረዳቶችንም ልንጠቀም ይገባናል።

ይህ ትምህርት በቀላሉ ከልክ በላይ ሊወሰድ ይችላል፤ እጅግ ብዙ ውጫዊ የአምልኮ መንገዶችን በማስገባት ወደ አጉል እምነት ሊወርድ ይችላልና፤ በሌላ በኩል ደግሞ አንዳንዶች ወደ ተቃራኒው ጽንፍ ወድቀዋል። ሃይማኖት በትክክል በልብ ውስጥ የተቀመጠ ስለ ሆነ፥ አንዳንዶች ያን አሳብ እስከዚያ ድረስ ገፍተው በድምፅ የሚደረግ ጸሎትንና ሌሎች ውጫዊ የአምልኮ ተግባሮችን ክደዋል፤ ሃይማኖትንም ሁሉ በጸጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ወደሚደረግ ጸጥተኛነት ወይም ምሥጢራዊ ግንኙነት ለውጠውታል።

እንግዲህ እነዚህ ሁለቱ ጽንፎች ለእውነተኛ ሃይማኖት እኩል ጎጂዎች ናቸው፤ በውስጣዊም ሆነ በውጫዊ አምልኮ ላይ እንደ ተቃውሞ ሊቀርቡ አይገባቸውም። ሃይማኖትን በልብ ውስጥ በማኖሬ ያንን የጸጥታ ትምህርት (ኩዌቲዝም) አበረታታለሁ ልትሉ እንደማይገባችሁ፥ እንዲሁም የውጫዊ የአምልኮ ሥራዎችን ጥቅም በማሳየቴ አጉል እምነትን አበረታታለሁ ልትሉ አይገባችሁም።

እኛ ሁለንተናችን ነፍስ ወይም ሁለንተናችን ሥጋ ስላልሆንን፥ ከሥራዎቻችንም አንዱ ስንኳ ለብቻው የነፍስ ወይም ለብቻው የሥጋ ስላልሆነ፥ ከነፍሳችንና ከሥጋችን ሥራዎች በአንድነት የሚወለዱ እንጂ ሌላ ልማድ ስለሌለን፥ የመሰጠትን ወይም በእግዚአብሔር ደስ የመሰኘትን ልማድ ለማግኘት ብንፈልግ፥ ነፍሳችንን ማሰላሰልና ማለማመድ ብቻ ሳይሆን፥ ሥጋችንንም ከእነዚህ ውስጣዊ ዝንባሌዎች ጋር በሚስማሙ ውጫዊ ሥራዎች ሁሉ ማሠልጠንና ማለማመድ እንዳለብን የተረጋገጠ ነው።

ነፍሳችንን በእውነት በእግዚአብሔር ፊት ልናዋርድ ብንፈልግ፥ ሥጋችንን የትሕትና አቋም እንዲይዝ ልናለማምደው ይገባናል፤ እውነተኛ የመሰጠት ትኩሳትን ብንሻ፥ ጸሎትን የከንፈሮቻችን ዘወትር የሚደክሙበት ሥራ ልናደርገው ይገባናል። ትዕቢትንና ቍጣን ሁሉ ከልባችን ልናስወግድ ብንፈልግ፥ ራሳችንን ወደ ትዕግሥትና የዋህነት ውጫዊ ሥራዎች ሁሉ ልናስገድድ ይገባናል። በእግዚአብሔር ያለውን ውስጣዊ የደስታና የሐሤት እንቅስቃሴ ልንሰማው ብንፈልግ፥ የእርሱን ውጫዊ ሥራዎች ሁሉ ልንለማመድና ድምፃችን ልባችንን እንዲጠራ ልናደርግ ይገባናል።

እንግዲህ የመዝሙራትን መዘመር ምክንያትና አስፈላጊነት በግልጥ ልታዩ ትችላላችሁ፤ ይህም ውጫዊ ሥራዎች ውስጣዊ ዝንባሌዎችን ለመደገፍ አስፈላጊ ስለ ሆኑ ነው፤ ስለዚህ ውጫዊው የደስታ ሥራ የአእምሮን ውስጣዊ ደስታ ለማስነሣትና ለመደገፍ አስፈላጊ ነው።

አንዳንድ ሰዎች የልባቸው እንቅስቃሴ ከሚናገሩት ቃል ጋር ሲስማማ እምብዛም ስለማያገኙ ጸሎትን ቢተዉ፥ ታላቅ ሞኝነት እንደ ፈጸሙ ትከሷቸዋላችሁ። ይልቁንም የልባቸውን ድንዛዜና የመሰጠት ጕድለት ለማስወገድ እጅግ ተስፋ የሚሰጠው መንገድ ስለ ሆነ፥ ጸሎታቸውን እንዲቀጥሉና የጸሎትን ጊዜያት ሁሉ በጥብቅ እንዲጠብቁ ማድረጋቸው እጅግ ተገቢ እንደ ሆነ ታስባላችሁ።

እንግዲህ መዝሙራትን የመዘመር ጉዳይም እንዲሁ ነው፤ ሰዎች ብዙ ጊዜ ከሚናገሩት ቃል ጋር የሚስማማ ውስጣዊ ደስታ ሳያገኙ ይዘምራሉ፤ ስለዚህ ቸል ይሉታል ወይም ፈጽመው ይተዉታል፤ ልቡ በጸሎት በበቂ ሁኔታ ስላልተነካ ጸሎትን እንደሚተው ሰው ያህል በሞኝነት እንደሚሠሩ አያስቡም። ጸሎት መሰጠትን ለማስነሣት የተፈጥሮ መንገድ እንደ ሆነ፥ ይህም መዘመር በአእምሮ ውስጥ የደስታን ስሜት ለማስነሣት የተፈጥሮ መንገድ እንደ ሆነ የተረጋገጠ ነው።

ለእውነተኛ ሃይማኖት ካለው ታላቅ ጠቀሜታ የተነሣ በዚህ ርእስ ላይ ረዘም ብዬ ቆይቻለሁ። እንደ እግዚአብሔርን የማመስገን ሁኔታ ያለ እንዲህ ቅዱስ፥ እንዲህ የላቀና እንዲህ በእውነት ፍጹም የሆነ የአእምሮ ሁኔታ የለምና፤ ስለዚህ ይህን የአእምሮ ልማድ ከሚያለማምደውና ከሚያሻሽለው ነገር በላይ በሃይማኖት ውስጥ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነ ነገር የለም።

ደንዛዛ፥ ዕረፍት የሌለውና የሚያማርር መንፈስ፥ ይህም አንዳንድ ጊዜ ለሃይማኖት የሚጠነቀቁ የሚመስሉ ሰዎች መንፈስ ነው፥ ከዝንባሌዎች ሁሉ ይልቅ ለሃይማኖት እጅግ ተቃራኒ ነው፤ የሚያመልከው መስሎ የሚታየውን ያንኑ እግዚአብሔርን ይክዳልና። እግዚአብሔርን ወሰን የሌለው በጎነት ያለው አካል አድርጎ የማያመልከው ሰው በበቂ ሁኔታ ክዶታልና።

አንድ ሰው ዓለም ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቤተ ሰብ እንደ ሆነች፥ በዚያም አንዳች ነገር በአጋጣሚ እንደማይሆን፥ ነገር ግን ሁሉ ለፍጥረታቱ ሁሉ ፍቅርና በጎነት ብቻ በሆነው አካል ጥንቃቄና መለኮታዊ አሠራር እንደሚመራና እንደሚቀናበር ባያምን፥ አንድ ሰው ይህን ከልቡ ባያምን፥ በእውነት በእግዚአብሔር ያምናል ሊባል አይችልም። ይህ እምነት ያለው ግን ዓለምን ለማሸነፍና ሁልጊዜ እግዚአብሔርን ለማመስገን የሚበቃ እምነት አለው። ሁሉ ለበጎ እንደሚደርስበት የሚያምን ሰው የተሻለ ነገር ስላጣ ሊያማርር ፈጽሞ አይችልምና።

እንግዲህ የሕይወትን አጋጣሚዎች ሁሉ እየከሰሳችሁ በማጕረምረምና በማማረር የምትኖሩ ከሆነ፥ ይህ የሆነው ደካማና ድውይ ፍጡር ስለ ሆናችሁ አይደለም፤ ነገር ግን የሃይማኖት የመጀመሪያው መሠረት፥ — በእግዚአብሔር ላይ ያለ ትክክለኛ እምነት ስለ ጐደላችሁ ነው። አመስጋኝነት እግዚአብሔር ለእናንተ ያለውን በጎነት በግልጥ መመስከር እንደ ሆነ፥ እንዲሁ ቅሬታና ማማረርም እግዚአብሔር ለእናንተ በጎነት እንደ ጐደለው የሚያቀርቡ ግልጥ ክሶች ናቸውና።

በሌላ በኩል ደግሞ፥ በዓለም ውስጥ ከሁሉ የሚበልጥ ቅዱስ ማን እንደ ሆነ ማወቅ ትወዳላችሁን? እርሱ አብዝቶ የሚጸልይ ወይም አብዝቶ የሚጦም አይደለም፤ አብዝቶ ምጽዋት የሚሰጥ ወይም ራስን በመግዛት፥ በንጽሕና ወይም በፍትሕ የታወቀ አይደለም፤ ነገር ግን ሁልጊዜ እግዚአብሔርን የሚያመሰግን፥ እግዚአብሔር የሚፈቅደውን ሁሉ የሚፈቅድ፥ ሁሉንም ነገር የእግዚአብሔር በጎነት ምልክት አድርጎ የሚቀበልና ስለ እርሱም እግዚአብሔርን ለማመስገን ሁልጊዜ የተዘጋጀ ልብ ያለው ሰው ነው።

ጸሎትና መሰጠት ሁሉ፥ ጾምና ንስሐ፥ ማሰላሰልና ገለልተኝነት፥ ምሥጢራትና ሥርዓቶች ሁሉ፥ ነፍስን እንዲህ መለኮታዊና ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የምትስማማ ለማድረግ፥ ከእግዚአብሔርም ስለሚመጣው ነገር ሁሉ በምስጋናና በውዳሴ ለመሙላት የተሰጡ መንገዶች ብቻ ናቸው። ይህ የበጎ ምግባራት ሁሉ ፍጹምነት ነው፤ ወደዚህ የማያደርሱ ወይም ከዚህ የማይመነጩ በጎ ምግባራት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር ያልተመለሰች ነፍስ የሐሰት ጌጦች ብቻ ናቸው።

እንግዲህ በመሰጠታችሁ ሁሉ መዝሙርን በመዘመር ላይ ይህን ያህል ማጽናቴ አሁን ሊያስደንቃችሁ አይገባም፤ ይህ መንፈሳችሁን የመለኮታዊና የቅዱስ ሕይወት ከፍተኛ ፍጹምነት ወደ ሆነው ወደዚያ ደስታና ለእግዚአብሔር ወደሚደረግ አመስጋኝነት ለመቅረጽ እንደ ሆነ ታያላችሁና።

ማንም ወደ ደስታ ሁሉና ወደ ፍጹምነት ሁሉ የሚያደርሰውን እጅግ አጭሩንና እርግጠኛውን መንገድ ቢነግራችሁ፥ ስለሚደርስባችሁ ነገር ሁሉ እግዚአብሔርን ለማመስገንና ለማክበር ለራሳችሁ ደንብ እንድታደርጉ ሊነግራችሁ ይገባዋል። ምንም ዓይነት መከራ የሚመስል ነገር ቢደርስባችሁ፥ ስለ እርሱ እግዚአብሔርን ብታመሰግኑና ብታከብሩ ወደ በረከት እንደምትለውጡት የተረጋገጠ ነውና። ስለዚህ ተአምራትን ማድረግ ብትችሉ እንኳ፥ በዚህ የአመስጋኝነት መንፈስ ከምታደርጉት በላይ ለራሳችሁ ልታደርጉ አትችሉም፤ በአንድ ቃል ይፈውሳልና፥ የሚነካውንም ሁሉ ወደ ደስታ ይለውጣልና።

እንግዲህ ይህን አመስጋኝነት የሃይማኖታችሁ ሁሉ ፍጻሜ አድርጋችሁ እስክታስቀምጡ ድረስ ለዘላለማዊ ጥቅማችሁ ታማኞች ብትሆኑ፤ በመሰጠታችሁ ሁሉ ልትደርሱበት የሚገባችሁ ሁኔታ ይህ እንደ ሆነ በአእምሮአችሁ ብቻ ብታጸኑ፤ ያን ጊዜ በሥራችሁ ሁሉ የምትመላለሱበት ግልጥና የሚታይ ነገር ይኖራችኋል፤ ያን ጊዜ የበጎ ምግባራችሁን ፍሬ በቀላሉ ታያላችሁ፥ በመንፈሳዊነትም ያደረጋችሁትን እድገት በእርግጥ ልትፈርዱ ትችላላችሁ። የራስ ወዳድነትን ዝንባሌዎችና የራሳችሁን ፈቃድ እንቅስቃሴዎች ሁሉ በካዳችሁ መጠንና የሚደርስባችሁን ነገር ሁሉ በምስጋና ከመቀበል በቀር ሌላ ደስታ ባልፈለጋችሁ መጠን፥ በዚያው መጠን በመንፈሳዊነት እንደ ገፋችሁ በእርግጥ ልትቈጠሩ ትችላላችሁና።

ይህ ልትደርሱበት የምትችሉት እጅግ ከፍተኛው ዝንባሌ ቢሆንም፥ ታላቁ ቅዱስ ለእግዚአብሔር ሊያቀርበው የሚችለው እጅግ የከበረው መሥዋዕት ቢሆንም፥ በማንኛውም ጊዜ ወይም ስፍራ ወይም ታላቅ አጋጣሚ የታሰረ አይደለም፤ ነገር ግን ሁልጊዜ በእጃችሁ ያለ ነው፤ የየዕለቱም ልምምድ ሊሆን ይችላል። የየዕለቱ የተለመዱ ሁኔታዎች ይህን ዝንባሌ ለመግለጥና ለማለማመድ በቂ ናቸውና፥ በሥራችሁም ሁሉ በዚህ የአመስጋኝነት መንፈስ ምን ያህል እንደምትመሩ በግልጥ ሊያሳዩአችሁ ይችላሉና።

በዚህም ምክንያት ቀን ሁሉ የምስጋና ቀን እንዲሆን፥ የእግዚአብሔርንም ምስጋና በመዘመር ብዙ ጊዜ በተጠመደ ልብ ውስጥ የማጕረምረምና የቅሬታ መንፈስ መግባት እንዳይችል፥ በመሰጠታችሁ ይህን መንገድ እንድትከተሉ እመክራችኋለሁ።

ምናልባት ከዚህ ሁሉ በኋላ እንዲህ የሚል ተቃውሞ ሊቀርብ ይችላል፤ የዚህ ልምምድ ታላቅ ጥቅምና መልካም ውጤት እጅግ ግልጥ ቢሆንም፥ መሰጠታችንን ለሌሎች ሰዎች ይፋ ሳናደርግ ልንፈጽመው ስለማንችል ለግል መሰጠት ፈጽሞ የሚስማማ አይመስልም፤ በጸሎታችንም ጊዜ መለከት እንደ መንፋት ያለ ክስ የሚያስከትል ይመስላል።

ስለዚህ እንዲህ ብለን እንመልሳለን፤ በመጀመሪያ፥ ብዙ ሰዎች እንደ ፈለጉ ለብቻቸው መሆን ይችላሉ፤ ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ከዚህ ምክንያት ውጭ ናቸው፤ ለሌሎች ምክንያት ቢሆንም እንኳ ለእነርሱ ግን ምክንያት አይሆንም። ስለዚህ የዚህን መልካም መሰጠት ጥቅም እንውሰድ።

ሁለተኛ፥ ብዙ ሰዎች እንደ አገልጋዮች፥ እንደ ተለማማጆች፥ እንደ እስረኞችና በትንንሽ ቤቶች እንደሚኖሩ ቤተ ሰቦች ከሁኔታቸው አስፈላጊነት የተነሣ ሁልጊዜ በአንድ ሰው ፊት ወይም ዓይን እንዲሆኑ ይገደዳሉ።

እንግዲህ እንደነዚህ ያሉ ሰዎች ሳይታዩ መጸለይ ስለማይችሉ ጸሎታቸውን ሊተዉ ይገባቸዋልን? ይልቁንስ ሌሎች የቸልተኝነታቸው ምስክሮች እንዳይሆኑና በምሳሌአቸውም እንዳይበላሹ በጸሎታቸው ይበልጥ ጥንቁቆች ሊሆኑ አይገደዱምን?

እንግዲህ ስለ መሰጠት እዚህ የተነገረው፥ የመሰጠት አንድ ክፍል ብቻ ስለ ሆነው መዝሙርን በዜማ ስለ ማንበብም በእርግጥ ሊነገር ይችላል።

ደንቡ ይህ ነው፤ በሰዎች ዘንድ እንድትታዩ አትጸልዩ፤ ነገር ግን መታሰራችሁ ሁልጊዜ በሌሎች ዓይን ፊት እንድትሆኑ የሚያስገድዳችሁ ከሆነ፥ ወደ ጸሎት ስትሄዱ ከመታየት ይልቅ ጸሎትን ቸል ስትሉ መታየትን አብዝታችሁ ፍሩ።

ሦስተኛ፥ የነገሩ አጭሩ ይህ ነው፤ ሰዎች በዚህ ልምምድ ሰሚ እስከማይኖራቸው ድረስ ለብቻቸው መሆን ይችላሉ ወይም አይችሉም። ቢችሉ፥ ይህ ተቃውሞ ለእነርሱ ይጠፋል፤ ባይችሉ ግን መታሰራቸውንና የሁኔታቸውን አስፈላጊነት እንደ ወኅኒ መታሰር አድርገው ሊቈጥሩት ይገባቸዋል፤ ያን ጊዜም የሚከተሉት መልካም ምሳሌ አላቸው፥ — በወኅኒ ውስጥ እግዚአብሔርን በዜማ ያመሰገኑትን ቅዱስ ጳውሎስንና ሲላስን ሊመስሉ ይችላሉ፤ እስረኞቹም ያደምጡአቸው እንደ ነበር በግልጥ ተነግሮናል። ስለዚህ በሌሎች እንዳይሰሙ ፈርተው ከዚህ ዓይነቱ መሰጠት አልተከለከሉም። እንግዲህ ማንም በወኅኒም ሆነ ከወኅኒ ውጭ በዚያው ዓይነት ችግር ውስጥ ቢሆን፥ ይህን ምሳሌ ከመከተል የተሻለ ምን ሊያደርግ ይችላል?

ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሳላልፍ፥ ይህን መዝሙራትን የመጠቀም ልማድ እንድንይዝ እዚህ እንዴት አጥብቀን እንደ ተጠራን፥ የእነዚህም የሁለቱ ታላላቅ ቅዱሳን ልምምድ እንዴት ያለ ታላቅ ምክር እንደ ሆነ መንፈሳዊውን አንባቢ እንዲያስተውል ሳልለምን ማለፍ አልችልም።

በዚህ በታላቁ ጭንቃቸው፥ በወኅኒ ውስጥ፥ በሰንሰለት ታስረው፥ በግርፋት ቍስል እየተሠቃዩ፥ በሌሊት ድንጋጤ ውስጥ ሆነው፥ ሊያደርጉት የቻሉት እጅግ መለኮታዊውና እጅግ ቅዱሱ ነገር ለእግዚአብሔር ምስጋና መዘመር ነበር።

እንግዲህ ከዚህ በኋላ ወደዚህ ቅዱስ ልምምድ የሚያነሣሣ ምክር ያስፈልገናልን? እነርሱ በሌሊት ቸል ያላሉትን እንዲህ ያለ ምስጋና ሳናቀርብ ቀኑን እናሳልፈዋለንን? ወኅኒ፥ ሰንሰለትና ጨለማ ለእነርሱ የውዳሴ መዝሙሮችን ካስገኙላቸው፥ እኛ በእልፍኞቻችን ውስጥ ምንም ዝማሬ አይኖረንምን?

ደግሞም እነዚህ ሁለቱ ቅዱሳን ሰዎች መላእክት በመንግሥተ ሰማያት የሚያደርጉትን በምድር ላይ እያደረጉ እጅግ ከፍ ባለው የመሰጠት ክፍል በዚህ ሁኔታ ተጠምደው ሳሉ፥ የወኅኒው መሠረት እንደ ተናወጠ፥ ደጆቹ ሁሉ እንደ ተከፈቱና የሁሉም እስራት እንደ ተፈታ ደግሞ ይታሰብ። [የሐዋርያት ሥራ 16፥26]

እንግዲህ በክርክር ፈንታ በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ታላቅ ኃይሉን የሚያስረዱን እንደነዚህ ያሉ ተአምራት እዚህ ሳሉልን፥ ወደዚህ መለኮታዊ ልምምድ የሚገፋፉ ምክንያቶችን አሁን እንጠይቃለንን?

እግዚአብሔር እነዚህን የሚጠቀሙትን እንዴት እንደሚሰማቸው፥ እንደሚያድናቸውና እንደሚከፍላቸው በዚህ መንገድ ከማሳየቱ በላይ፥ ከሰማይ በሚመጣ ድምፅ ወደነዚህ የውዳሴ መዝሙሮች ይበልጥ በግልጥ ሊጠራን ይችል ነበርን?

ይህ ግን በመንገድ ላይ የተነገረ ነው። አሁን ወደ ያዝነው ተቃውሞ እመለሳለሁ፤ በአራተኛም እንዲህ እመልሳለሁ፤ የጸሎታችን ምሥጢራዊነት የሚጠፋው ምስክሮች ስላሉን ሳይሆን ምስክሮችን ስለምንፈልግ ነው።

ስለዚህ ልትለዩአቸው ከማትችሉት ሰዎች በቀር ማንም ባይሰማችሁ፥ እናንተ በስውር ናችሁ፤ በስውር የሚያይ አባታችሁም በእርሱ ብቻ እንደ ታያችሁ ያህል ስለ ምሥጢራዊነታችሁ በእውነት ይከፍላችኋል።

አምስተኛ፥ የግል ጸሎት በሕዝብ ፊት ከሚደረግ ጸሎት ጋር ሲነጻጸር፥ ማንም ምስክር ሊኖረው እንደማይገባ አያመለክትም። ባሎችና ሚስቶች፥ ወንድሞችና እኅቶች፥ ወላጆችና ልጆች፥ ጌቶችና አገልጋዮች፥ መምህራንና ተማሪዎች፥ በእውነትና በትክክል የግል ሊባል የሚችለውን እንዲህ ያለውን መሰጠት እርስ በርሳቸው ሊመሰክሩ ይገባቸዋልና። እንዲህ ያለውን መሰጠት ከእንደነዚህ ያሉ የቅርብ ዘመዶች መሰወር ግዴታ ከመሆን እጅግ የራቀ ነው።

ስለዚህ እንደነዚህ ያሉ ዘመዶች አንዳንድ ጊዜ በግል በአንድነት፥ አንዳንድ ጊዜም ለብቻቸው በሚጸልዩባቸው በእነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች፥ መዝሙርን በዜማ በማንበብ ላይ ምንም ተቃውሞ ሊቀርብ አይችልም።

ብሩክ ጌታችን ስንጦም፥ በስውር ላለው አባታችን እንጂ ለሰዎች ጦመኞች ሆነን እንዳንታይ ራሳችንን እንድንቀባና ፊታችንን እንድንታጠብ ያዝዘናል።

ይህ ግን ጾማችንን በዓለም ፊት በይፋ ልንታይበት አይገባንም ማለት ብቻ ነው።

ምስክር ከሌለው ሰው በቀር ማንም በግል የማይጦም ወይም በግል ይጦማል የማይባል ቢሆን ኖሮ፥ ለብቻው ከሚኖር ሰው በቀር ማንም የግል ጾም ሊጠብቅ ባልቻለም ነበር፤ — ቤተ ሰብ ሁሉ በውስጡ ማን እንደሚጦም ማወቁ አይቀርምና። ስለዚህ የጾም ምሥጢራዊነት ማንንም እንዳያውቅ የሚከለክል ምሥጢራዊነትን አያመለክትም፥ ነገር ግን በውጭ እንዲታወቅ የማይፈልግ ምሥጢራዊነትን ነው እንጂ።

መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ምጽዋት ያደርግ ወደ እግዚአብሔርም ሁልጊዜ ይጸልይ እንደ ነበር የሚናገርለት እግዚአብሔርን የሚያመልከው የመቶ አለቃ ቆርኔሌዎስ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዲህ አለው፤ «የዛሬ አራት ቀን እስከዚች ሰዓት ድረስ እጦም ነበር።» [የሐዋርያት ሥራ 10፥30]

ይህ ጾም በበቂ ሁኔታ ምሥጢራዊና በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደ እንደ ነበር፥ ቅዱሱ ሰው በዚያን ጊዜ ከተባረከበት የመልአክ ራእይ ይታያል።

ነገር ግን ሌሎች ፈጽሞ እስከማያውቁት ድረስ ምሥጢራዊ እንዳልነበረ፥ እዚህ ከተነገረው ታሪክ፥ እንዲሁም በሌላ ስፍራ «ከሎሎዎቹ ሁለቱን፥ ከማይለዩትም ጭፍሮቹ እግዚአብሔርን የሚያመልክ አንዱን ወታደር ጠርቶ» ከተባለው ይታያል። [ቍጥር 7] ስለዚህ የቆርኔሌዎስ ጾም ለቤተ ሰቡ የማይታወቅ ከመሆን እጅግ የራቀ ነበር፤ ወታደሮቹና የቤቱ ሰዎች ዘወትር እርሱን በማገልገል፥ ማለትም መልካም ሥራዎቹን በማየትና በእነርሱ በመካፈል፥ እነርሱ ራሳቸው እግዚአብሔርን የሚያመልኩ ሆኑ።

የነገሩ ሁሉ ድምር ይህ ነው። ብዙው የዓለም ክፍል እንደ ፈለገ ለብቻው መሆን ይችላል፤ ስለዚህ ይህን መልካም መሰጠት በእግዚአብሔርና በራሳቸው መካከል ይጠቀሙበት።

እንግዲህ የጾም ምሥጢራዊነት ወይም ልዕልና በአንዳንድ ሰዎች በመታወቁ እንደማይጠፋ፥ እንዲሁ መዝሙርን በዜማ በማንበባችሁ ከቤተ ሰባችሁ አንዳንዶቹ ቢሰሟችሁም እንኳ የመሰጠታችሁ ምሥጢራዊነት ወይም ልዕልና አይጐዳም።

ሌላው ታላቅ የዓለም ክፍል ደግሞ ለብዙዎቹ መሰጠቶቹ ምስክሮች ሊኖሩት ግድ ነው፥ ይገባዋልም፤ ስለዚህ ጸሎታቸውን ቸል እንደማይሉ አብረዋቸው ለሚኖሩት ሰዎች ሊታወቅ በሚገባው በእንደነዚህ ያሉ ጊዜያት መዝሙርን መጠቀም ቸል አይበሉ። በጸሎታችሁ ላይ እንዳላችሁ ሊታወቅ በሚገባው ጊዜ መዝሙር ስትዘምሩ መታወቃችሁ ምንም ጕዳት ሊኖረው አይችልምና።

በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ማንም እንዳይጠረጥራችሁ በመሰጠታችሁ እንዲህ ባለ ምሥጢር ውስጥ ለመሆን ብትፈልጉ፥ በዚህም ምክንያት መዝሙራችሁን ብትተዉ፥ በዚህ ላይ የምቃወመው ነገር የለኝም፤ ብቻ በታወቁት የጸሎት ሰዓታት ይህን ልምምድ ፈጽሞ አትተዉ።

ቅዱስ ጳውሎስና ሲላስ በመንፈቀ ሌሊት ቸል ያላሉትን ነገር በቀን ብዙ ጊዜ የማያደርግ ማን ነው? እንዲህ ስትዘምሩም ቅዱስ ጳውሎስ በዘመረ ጊዜ ወኅኒው እንዴት እንደ ተናወጠና ደጆቹ እንዴት እንደ ተከፈቱ ወደ አእምሮአችሁ ቢመጣ፥ በመሰጠታችሁ ላይ ምንም ጕዳት አያመጣም።

በመጨረሻም፥ ምናባችን በልባችን ላይ ታላቅ ኃይል ስላለው፥ በሚሥላቸውም ሥዕሎች እጅግ ሊነካን ስለሚችል፥ በመሰጠታችሁ መጀመሪያ ልባችሁን ያን ጊዜ ለእግዚአብሔር ልታቀርቡት ካሰባችሁት ጸሎት ጋር ወደሚስማማ ዝንባሌ የሚያሞቅና የሚያግል አንዳንድ እንዲህ ያሉ ሥዕሎችን ለራሳችሁ ብትሥሉ እጅግ ይጠቅማችኋል።

ለምሳሌ እንዲህ፤ በእግዚአብሔር የምስጋናና የሐሤት መዝሙራችሁን ከመጀመራችሁ በፊት ምናባችሁን እንዲህ ተጠቀሙበት።

ጸጥ በሉ፥ ሰማያት ተከፍተው፥ በእግዚአብሔርም ዙፋን ዙሪያ የኪሩቤልንና የሱራፌልን የክብር መዘምራን እንዳያችሁ ለራሳችሁ አስቡ። የነበረውንና ያለውን የሚመጣውንም ክብር ለመዘመር ቀንና ሌሊት የማያቋርጡትን የእነዚያን የመላእክት ድምፆች ዜማ እንደምትሰሙ አስቡ።

ምናባችሁን እንደሚከተሉት ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እርዱት፤—

«ከዚህ በኋላ አየሁ፥ እነሆም፥ አንድ እንኳ ሊቆጥራቸው የማይችል ከሕዝብና ከነገድ ከወገንም ከቋንቋም ሁሉ እጅግ ብዙ ሰዎች ነበሩ፤ ነጭ ልብስም ለብሰው የዘንባባንም ዝንጣፊዎች በእጆቻቸው ይዘው በዙፋኑና በበጉ ፊት ቆሙ፤ በታላቅም ድምፅ እየጮሁ። በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው ለአምላካችንና ለበጉ ማዳን ነው አሉ።»

«መላእክቱም ሁሉ በዙፋኑና በሽማግሌዎቹ በአራቱም እንስሶቹ ዙሪያ ቆመው ነበር፤ በዙፋኑም ፊት በግምባራቸው ተደፉ፥ ለእግዚአብሔርም እየሰገዱ። አሜን፥ በረከትና ክብር ጥበብም ምስጋናም ውዳሴም ኃይልም ብርታትም ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ለአምላካችን ይሁን፤ አሜን አሉ።» [የዮሐንስ ራእይ 7፥9-12]

ምናባችሁ ከደመናት በላይ እስኪወስዳችሁ ድረስ፥ በእነዚያ ሰማያውያን ፍጥረታት መካከል እስኪያኖራችሁና በዘላለማዊ ዜማቸውም ድርሻ እንዲኖራችሁ እስኪያስናፍቃችሁ ድረስ ይህን አሰላስሉ።

ራሳችሁን በዚህ መንገድ ብቻ ብታለማምዱ፥ ምናባችሁም እንደነዚህ ባሉ ሥዕሎች ላይ እንዲቆይ ብትፈቅዱ፥ ይህ በውስጣችሁ የመሰጠትን መንፈስ ለማስነሣት መልካም መንገድ እንደ ሆነ ብዙም ሳትቆዩ ታገኙታላችሁ።

ስለዚህ መዝሙራችሁን ወይም የምስጋና ቅኔአችሁን ሁልጊዜ በእነዚህ አሳቦች ጀምሩ፤ በእያንዳንዱም ስንኝ በእነዚያ ሰማያውያን ባልንጀሮች መካከል እንዳላችሁ፥ ድምፃችሁም በድምፃቸው ላይ እንደ ተጨመረ፥ መላእክትም ከእናንተ ጋር እናንተም ከእነርሱ ጋር እንደ ተባበራችሁ፥ እነርሱ በመንግሥተ ሰማያት የሚዘምሩትን እናንተ በደካማና በዝቅተኛ ድምፅ በምድር ላይ እንደምትዘምሩ አስቡ።

ደግሞም፥ አንዳንድ ጊዜ ብሩክ መድኃኒታችን መዝሙር በዘመረ ጊዜ ከእርሱ ጋር ከተባበሩት አንዱ እንደ ነበራችሁ አስቡ። በምን ዓይነት ግርማ እንደ ተመለከተ ለራሳችሁ ለመሣል ጣሩ፤ በክብሩ ተከብባችሁ በአጠገቡ እንደ ቆማችሁ አስቡ። ከእግዚአብሔር ልጅ ጋር ስትዘምሩ ልባችሁ እንዴት እንደሚቃጠል፥ ያን ጊዜ ምን ዓይነት የደስታ ተመስጦ እንደሚሰማችሁ አስቡ። ይህ በእውነት የእናንተ ብፁዕ ሁኔታ ቢሆን ኖሮ ያን ጊዜ በምን ዓይነት ደስታና መሰጠት እንደምትዘምሩ፥ ያን ጊዜ ዝም ማለታችሁንም እንዴት ያለ ቅጣት አድርጋችሁ እንደምትቈጥሩት ደግማችሁ ደጋግማችሁ አስቡ፤ ይህም በመዝሙራትና በምስጋና ቅኔዎች እንዴት መነካት እንዳለባችሁ ያስተምራችሁ።

ደግሞም፥ አንዳንድ ጊዜ ቅዱሱ ዳዊት እጆቹን በበገናው ላይ አድርጎ ዓይኖቹንም ወደ ሰማይ አቅንቶ፥ ፍጥረትን ሁሉ፥ ፀሐይንና ጨረቃን፥ ብርሃንንና ጨለማን፥ ቀንንና ሌሊትን፥ ሰዎችንና መላእክትን፥ የሰማይን ጌታ በማመስገን ከተመሰጠች ነፍሱ ጋር እንዲተባበሩ በሐሤት ሲጠራ እንዳያችሁት ለራሳችሁ አስቡ።

ከዚህ መለኮታዊ ዘማሪ ጋር እንደምትዘምሩ እስኪሰማችሁ ድረስ በዚህ አሳብ ላይ ቆዩ፤ እንዲህ ያለ ባልንጀራም በሚከተለው መዝሙር ልባችሁን ወደ እግዚአብሔር ከፍ ከፍ እንድታደርጉ ያስተምራችሁ፤ ይህንም ዘወትር፥ በመጀመሪያ በማለዳ ልትጠቀሙበት ትችላላችሁ፤—

መዝሙር 145። «አምላኬ ንጉሤ ሆይ፥ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ፤ ስምህንም ለዘላለም ዓለም አመሰግናለሁ፤» ወዘተ።

እንደ 34ኛው፥ 96ኛው፥ 103ኛው፥ 111ኛው፥ 146ኛውና 147ኛው ያሉት የሚከተሉት መዝሙራት የእግዚአብሔርን ክብር በሚያስደንቅ ሁኔታ የሚገልጡ ናቸው፤ ስለዚህ በማንኛውም በተወሰነ ሰዓት እንደ ወደዳችሁ ከእነርሱ አንዱን ልትይዙ ትችላላችሁ፤ ወይም ከማንኛውም መዝሙራት እጅግ ያማሩትን ክፍሎች ወስዳችሁ በአንድነት በማጣመር ለራሳችሁ መሰጠት ይበልጥ የሚስማሙ ልታደርጓቸው ትችላላችሁ።

ጨርሰዋል፦ ስለ ዝማሬ፥ ማለትም በግል መሰጠታችን መዝሙራትን ስለ መዘመር። የዚህ ዓይነቱ መሰጠት ልዕልናና ጥቅም። በልባችን ላይ የሚያደርገው ታላቅ ውጤት። በተሻለ ሁኔታ የሚፈጸምበት መንገድ

ቀዳሚ ቀጣይ